አርሜንያ -አዘርባጃን ግጭት፡ ሩሲያ በናጎርኖ ካራባህ ጉዳይ የሰላም ውይይት ልታዘጋጅ ነው

የአርሜንያ መከላከያ ሃይል

የፎቶው ባለመብት, EPA

ሩሲያ በናጎርኖ-ካራባህ ግዛት ይገባኛል ወደ ግጭት ያመሩት የቀድሞ የሶቪየት ሪፐብሊክ አካል በነበሩት አርሜንያና አዘርባጃን መካከል ያለውን ግጭት ለማስቆም የሰላም ውይይት ልታዘጋጅ መሆኑን አስታወቀች።

የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰረጌ ላቭሮቭ ለሁለቱ አገራት መንግሥታት ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤ መሥሪያ ቤታቸው እንደገለፀው ሚኒስትሩ፤ አገራቱ 'ለጦርነት መቋመጣቸውን' እንዲያቆሙ አሳስበዋል።.

ረቡዕ ዕለት የሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ መሥሪያ ቤት እንደገለፀው፤ ሩሲያ የሰላም ውይይቱን ለማዘጋጀት ፈቃደኛ መሆኗን ለመግለፅ የሁለቱን አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጠርተው ነበር።

የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲንም ግጭቱን አስመልክተው ከፈረንሳዩ ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በስልክ ተወያይተዋል። ሁለቱ መሪዎች የተኩስ አቁም ጥሪ አቅርበዋል።

ሩሲያ ከአርሜንያ ጋር የጦር ሕብረት ያላት ሲሆን በአገሪቷም የጦር ሰፈር አላት። ይሁን እንጅ ከአዘርባጃን መንግሥት ጋርም የቅርብ ግንኙነት እንዳላት ይነገራል።

አርሜንያ ራስገዝ የሆነችውን ናጎርኖ- ካራባክህን የምትደግፍ ቢሆንም ይፋዊ እውቅና ግን አላገኘችም።

በሁለቱ አገራት መካከል እሁድ እለት በተቀሰቀሰው ግጭት ከ100 በላይ ሰዎች የሞቱ ሲሆን፤ በዓመታት ውስጥ በግዛቷ ሳቢያ የተቀሰቀሰው ከባድ ግጭት ነውም ተብሏል።

የአዘርባጃን አካል እንደሆነች የምትታወቀው ናጎርኖ-ካራባህ የምትተዳደረው ግን በአርሜንያ ነው።

አርሜንያና አዘርባጃን በግዛቷ ሳቢያ ከጎርጎሮሳዊያኑ 1988-1994 ድረስ ተዋግተዋል። አሁንም ዓለም አቀፍ ኃይሎች በግጭቱ ጣልቃ ይገባሉ የሚል ስጋት እየጨመረ መጥቷል።

ሰሞኑን የተቀሰቀሰው ግጭት መነሻው ግልፅ አይደለም። ረቡዕ ዕለት የአዘርባጃኑ ፕሬዚደንት ኢልሃም አሊየቭ የአርሜንያ ወታደሮች ግዛቷን ለቀው እስኪወጡ ድረስ እንደሚዋጉ ዝተዋል።

" አንድ ቅድመ ሁኔታ ብቻ ነው ያለን፤ ይህም የአርሜንያ ወታደሮች ያለምንም ማቅማማት፣ ሙሉ ለሙሉ እና በአፋጣኝ መሬታችንን ለቀው መውጣት አለባቸው" ሲሉ ነበር ፕሬዚደንቱ የተናገሩት።

አዘርባጃን በበኩሏ ሁለት የጠላት የጦር ታንኮች መውደማቸውን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ያጋራች ሲሆን፤ የአርሜንያ ብርጌድ በቶናሸን መንደር ያለውን አካባቢ ጥለው መውጣታቸውን ገልፃለች።

ረቡዕ ዕለት አዘርባጃን በማርታከርት ከተማ ላይ በፈፀመችው የአየር ድብደባ ሦስት ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን የአርመኒያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የመንግሥት የዜና ወኪሉ 'አርመንፕረስ' ደግሞ ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ ሰባት ሰላማዊ ሰዎች እና 80 ወታደሮች ተገድለዋል ብሏል።

በሌላ በኩል የአርሜንያ መከላከያ ሚኒስቴር በቱርክ ኤፍ-16 ተመትቶ እንደተጣለ የተነገረው የአርመኒያ ኤስዩ-25 የጦር ጀትን ምስል አውጥቷል። የአዘርባጃን ታማኝ ወዳጅ የሆነችው ቱርክ ግን የቀረበባትን ክስ 'ርካሽ ፕሮፖጋንዳ' ስትል ውድቅ አድርገዋለች።

ይሁን እንጅ አንድ ተዋጊ ባለፈው ሳምንት ከሰሜን ሶሪያ እንደተመለመለ እና ለውጊያው በቱርክ በኩል እንደተላከ ለቢቢሲ አረብኛ ተናግሯል። የቱርክ ፕሬዚደንት ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን አማካሪ ኢልኑር ሴቪክ ግን ዘገባውን 'ሙሉ ለሙሉ መሰረተ ቢስ' ብለውታል።

ግጭቱ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት -ኔቶ አባል አገራት በሆኑት ፈረንሳይና ቱርክ መካከል ውጥረትን ፈጥሯል።

ፈረንሳይ ለበርካታ አርሜንያዊያን መኖሪያ ስትሆን ቱርክ ደግሞ በአዘርባጃን የሚገኙ ቱርካዊያንን ትደግፋለች።

ረቡዕ ዕለት የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒሰተር ሜቭሉት ካቩሶግሉ ፈረንሳይ "አርሜንያዊያንን ትደግፋለች" ሲሉ ከሰዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳነት ኢማኑኤል ማክሮንም ለዚህ የአፀፋ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ከቱርክ የሚመጡ 'ጦርነት ቀስቃሽ' መልዕክቶችን ተችተዋል።

ፕሬዚደንት ፑቲንና ማክሮን በስልክ ውይይት ካደረጉ በኋላ ቀጣይ እርምጃዎች ላይ መነጋገራቸውንና የአውሮፓ የፀጥታና ትብብር ድርጅት-ሚንስክ ግሩፕ ግጭቱን ለመፍታት እንደሚሞክር የፑቲን መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ሚንስክ ግሩፕ በጎርጎሮሳዊያኑ 1992 የተመሰረተ ሲሆን የሚመራው በፈረንሳይ፣ ሩሲያ እና አሜሪካ ነው።