የሴቶች መብት፡ በቡድን ተደፍራ የተገደለችው ህንዳዊት ያለ ቤተሰቧ እውቅና ተቀበረች

የታዳጊዋን አስከሬን የያዘው አምቡላንስ

የፎቶው ባለመብት, Abhishek Mathur / BBC

በቡድን ተደፍራ የተገደለችው የ19 አመቷ ህንዳዊት ቤተሰብ ያለ ዕውቅናቸው ቀብሯ ተፈፅሟል በማለት ፖሊስን ወንጅለዋል።

በህንድ የቀብር ባህል ስነ ስርአትም መሰረትም አስከሬኗን አቃጥለውታል ብለዋል።

የአስራ ዘጠኝ አመቷ ታዳጊ በህንድ የማህበረሰብ አመዳደብ መሰረት ዝቅተኛ ስፍራ የተሰጣቸውና ዳሊት የሚባሉ ሲሆኑ በቀደመው ወቅትም የማይነኩ የማይባሉ ናቸው።

የደፈሯትም አራት ወንዶች ከላይኛው መደብ የሚመደቡ ናቸውም ተብሏል።

በሰሜናዊ ህንድ ሃትራዝ ግዛት የተደፈረችው ሴት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ሲሆን ሆስፒታል ውስጥ ለሁለት ሳምንታት ያህል ከቆየች በኋላ በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ህይወቷ አልፏል።

በቡድን መደፈሯና መገደሏ ሁኔታ በአገሪቷ በከፍተኛ ሁኔታ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን ያለ ቤተሰቦቿ እውቅና በዚህ መንገድ መቀበሯም "ኢሰብዓዊ ውሳኔ" ነው በማለት ተሟጋቾች አውግዘውታል።

ጥቃት አድርሰውባታል የተባሉት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን የፍርድ ሂደቱም በፍጥነት በቅርብ ይጀምራል ተብሏል።

የአገሪቱ ጋዜጠኛ አብህሸክ ማቱር የህንዳዊቷን ቀብር በሩቅ የተከታተለ ሲሆን ለቢቢሲ እንደተናገረው ቤተሰብም ሆነ ሚዲያ ባልተገኙበት ተቀብራለች።

አስከሬኗ ወደ ትውልድ መንደሯ ኡታር ፕራዴሽ የመጣው ሌሊት ሲሆን የጥቃቱ ሰለባ የሆነችው ወንድም እንደሚናገረው አስከሬኗን በፍጥነት እንዲያቃጥሉት በፖሊስ መጠየቃቸውን ነው።

"በአሁኑ ሰዓት አናቃጥልም፤ አንቀብርም ስንል በአምቡላንስ ይዘው ተመልሰው ሄዱና አቃጠሉዋት" ብሏል።

የግዛቲቷ ከፍተኛ ኃላፊ በበኩላቸው ይህንን አይቀበሉም የቤተሰብ ፈቃድ አግኝተናል ብለዋል።

የጥቃቱ ሰለባ እናት ልጃቸውን ወደ ቤታቸው መውሰድ ፈልገው እንደነበርና የሚያስፈልገውን ባህላዊ ስርአቶች እንዲፈፀም ቢጠይቁም አልተፈቀደላቸውም።

የቀብር ስርአቱ በሚፈፀምበትም አካባቢ ፖሊስ አካባቢውን ከቦ ቤተሰብ፣ ሚዲያም ሆነ ለተቃውሞ የመጡ ሰዎች በመካነ መቃብሩ ዝር እንዳይሉም ሲከላከሉ ነበር በማለት ወንድምዬው አሳውቋል።

ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ የፖሊስ ኃላፊዎችም ቤተሰቡን አመናጭቀዋልም ብሏል።

"አስከሬኗን ያለ ቤተሰባችን ፈቃድ ወስደው አቃጠሉት፤ ለመጨረሻ ጊዜ ለማየት እድል እንኳን አልተሰጠንም" በማለትም በኃዘን በተሰበረ ልቡ ተናግሯል።

ቤተሰቦቿ አስከሬኗን ለማየትም ሲጠይቁ ሴቶች የቤተሰብ አባላትን ጨምሮ በፖሊስ ድብደባ ተፈፅሞባቸዋልም ብሏል።