ታኩ ሴኪን፡ ጃፓናዊው ሼፍ የቀረበበትን ወሲባዊ ትንኮሳ ውንጀላ ተከትሎ ራሱን አጠፋ

ታኩ ሴኪን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዝነኛው ጃፓናዊው ሼፍ ታኩ ሴኪን በፈረንሳይ ሁለት እውቅ ምግብ ቤቶች አሉት።

በምግብ አቅርቦታቸውም ሽልማትን ተቀዳጅተዋል። ምርጥ ምግብ ቤት የሚል ስያሜም አግኝተዋል።

'ደርሶ' የሚል ስያሜ ያለው መግብ ቤቱ ከአራት ዓመታት በፊት ነበር የተከፈተው። 'ዘ ቤስት ኢን ፍራንስ' የተሰኘውን ሽልማት ያገኘውም በዚያው ዓመት ነው።

ባለፈው ዓመትም ' ቼቫል ዲኦር' የተባለ የተለያዩ የእስያ አገራት ምግቦች የሚዘጋጁበት ምግብ ቤት የከፈተ ሲሆን፤ ይህም ሽልማትን ተቀዳጅቷል።

የ39 ዓመቱ ታኩ፤ ከፈረንሳዩ እውቅ ሼፍ አሌን ዱካሴ ጋር በቶክዮ እንዲሁም በፓሪስ በሚገኘው አቴኔ ፕላዛ አብረው ሰልጥነዋል።

ታዲያ አሁን የመሞቱ ዜና ተሰምቷል።

ጃፓናዊው ሼፍ የቀረበበትን ወሲባዊ ትንኮሳ ውንጀላ ተከትሎ ሰኞ ዕለት ራሱን ማጥፋቱን ቤተሰቦቹ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

በእርግጥ በታኩ ላይ የቀረበ ይፋዊ ክስም አልነበረም ፤ በፖሊስም ምርመራ እየተደረገበት አልነበረም። እርሱ ግን የቀረበውን ውንጀላ አስተባብሏል።

ነገሩ ወዲህ ነው። ታኩ የተወነጀለው ባሳለፍነው የፈረንጆቹ በጋ ወራት፤ በርካታ ሴቶች ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ፈፅሟል የሚል ነው።

በኋላ ላይ አንዲት ሴት ስሙን ባልጠቀሰችው እንድ ጃፓናዊ ዝነኛ ሼፍ ወሲባዊ ትንኮሳ ደርሶባት እንደነበር በኢንስታግራም ገጿ ላይ አሰፈረች።

ይህንን ተከትሎም በዘርፉ ያሉ ሴቶችም ለዚች ሴት ድጋፋቸውን ማሰማት የጀመሩ ሲሆን፤ 'ሚቱ' የሚል እንቅስቃሴም መጀመሩን የምግብ የዜና ድረ ገፁ- ኢተር ዘግቧል።

እንደ ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ከሆነ፤ ምግብ ላይ ትኩረት የሚያደርገው 'አታቡላ' የተሰኘው የፈረንሳይ ድረ ገፅ ባሳለፍነው ነሃሴ ወር ላይ በፈረንሳይ ምግብ ቤቶች ኩሽና ስለተፈፀመ ወሲባዊ ጥቃትና ትንኮ ዘለግ ያለ የምርመራ ፅሁፍ አትሞ ነበር።

በፅሁፉ ስሙ ያልተገለፀው ዝነኛው ጃፓናዊ ሼፍ ለመድፈር ወንጀሉ ተጠያቂ እንደሚሆን አስፍሯል።

ሼፍ ታኩም ይህ ሰው ማን እንደሆነ እንደሚያጣራ ተናግሮ ነበር።

በኋላ ላይ ግን ይሄው ድረ ገፅ የተለያዩ ምንጮችን ዋቢ በማድረግ የሼፉን ስም ይዞ ወጥቷል።

ሼፍ ታኩ ይህ ውንጀላ ከተመሰረተበት በኋላ ቁጡ እና እረፍት የለሽ እየሆነ መምጣት መጀመሩን ቤተሰቦቹ ተናግረዋል። ይህ ችግር እያደገ ሄዶም ለከፍተኛ የአዕምሮ ጤና ችግር - ድብርት ተዳረገ ይላሉ ቤተሰቦቹ።

"በራሱ ክብርና ፅናት ላይ የተፈፀመው ጥቃት ጥልቅ ነበር፤ ለድብርት ችግር ከተዳረገም በኋላም፤ ታኩ ከዚህ ችግር እንዴት ሊወጣ እንደሚችል ግራ ገብቶት ነበር" ብለዋል ቤተሰቦቹ ባወጡት መግለጫ።

የሼፉን መሞት ተከትሎ የጥቃቱን ዘገባ ያወጣው ምግብ ላይ ትኩረት የሚያደርገው 'አታቡላ' የተሰኘው የፈረንሳይ ድረ ገፅ ያቀረበውን ሪፖርት ተከላክሏል።