ኮሮናቫይረስ፡ ስፔን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በማገርሸቱ የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲጣል አዘዘች

ፖሊስ በማድሪድ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የስፔን መንግሥት በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ በወረርሽኙ ክፉኛ በተጠቁት በመዲናዋ ማድሪድና አካባቢዋ የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲጣል አዘዘ።

አዲስ በተጣለው ገደብም ወሳኝ የሆነ ጉዞ ማድረግ ከሌለባቸው በስተቀር ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ጥለው እንዲወጡ አይፈቀድላቸውም።

ይሁን እንጅ የማድሪድ ክልል መንግሥት የእንቅስቃሴ ገደቡ ሕጋዊ አይደለም ብሏል።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ በስፔን በቫይረሱ ከተያዙት 133 ሺህ 604 ሰዎች መካከል ከሲሶ በላይ የሚሆነው የተገኘው በማድሪድ ነው።

በዚህም መሰረት ረቡዕ ዕለት አብዛኞቹ የስፔን የክልል ባለሥልጣናት፤ ከ100 ሺህ በላይ ነዋሪዎች የሚገኙባቸው አካባቢዎች ሦስት መመዘኛዎችን ካሟሉ ገደብ እንዲጣልባቸው ድምፅ ሰጥተዋል።

ሦስቱ መመዘኛዎች፤ ከ100 ሺህ ነዋሪዎች ውስጥ 500 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ካሉ፣ 35 በመቶ የሚሆኑት የበሽታው ታማሚዎች ፅኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ከገቡ እና ከሚደረገው ምርመራ በ10 በመቶው ላይ ቫይረሱ ከተገኘበት የሚሉ ናቸው።

በዚህ መስፈርት መሰረትም ከ100 ሺህ ነዋሪዎች 780 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ያሉባት ማድሪድ፤ መመዘኛውን አሟልታለች ተብሏል። ይሁን እንጅ አዲስ የተጣለው ገደብ መቼ ተግባራዊ እንደሚሆን አልታወቀም።

ገደቡን ለመጣል ድምፅ ያልሰጠው በወግ አጥባቂው ተቃዋሚ ፓርቲ የሚመራው የማድሪድ ክልል መንግሥት ግን የእንቅስቃሴ ገደቡ ሕጋዊ አይደለም ብሏል።

የክልሉ የጤና ኃላፊ ኢንሪኪው ሩይስ እስኩደሮ 'የማስጠንቀቂያና የሚረብሽ መልዕክት' በመላክ ማዕከላዊ መንግሥቱን ከሰዋል።

የማድሪድ መንግሥት በከተማዋና አካባቢዋ የእንቅስቃሴ ገደብ ከመጣል ይልቅ፤ በ45 ዋና ዋና የጤና ተቋማት አካባቢዎች ገደቡን በመጣል የቫይረሱን ሥርጭት ለመቆጣጠር ነበር ምርጫው ያደረገው።

ይሁን እንጅ ገደቦቹ በከተማዋ በአብዛኛው በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ነዋሪዎች ያሉባቸውን አካባቢዎችን ይበልጥ ይጎዳል በሚል አከራካሪ ነበሩ።

ከዚህ ቀደም የእንቅስቃሴ ገደቡን በመቃወም በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች አደባባይ መውጣታቸው ይታወሳል።

የስፔን ማዕከላዊ መንግሥት ግን "ከዚህ ቀደም የተጣሉት ገደቦች በቂ አልነበሩም" በማለት በመላ ከተማዋ የሚደረግ አላስፈላጊ እንቅስቃሴ እንዲቆም አሳስበዋል።

የእንቅስቃሴ ገደቡ ተግባራዊ ሲደረግ የማድሪድ ድንበሮች ወሳኝ ወይም አስፈላጊ የሆነ ጉዞ ለሌላቸው ጎብኝዎች ዝግ ይሆናሉ።

ድንበሯን እንዲያቋርጡ የሚፈቀደው ለሥራ ፣ ለሕክምና እና ለሸመታ እንደሆነም ተነግሯል።

መናፈሻዎችና የመጫወቻ ሜዳዎችም ይዘጋሉ። ከስድስት በላይ ሰዎች አንድ ላይ መሰባሰብም አይችሉም።

በስፔን ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን፤ እስካሁን ከ31 ሺህ 411 ሰዎች በላይ በቫይረሱ ሕይወታቸው አልፏል።

እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ፤ እስካሁንም ከ748 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በአውሮፓ አገራት ወረርሽኙ 'በአስጊ ሁኔታ' እየተስፋፋ መሆኑን አስታውቋል።