ጃዋር መሐመድ፡ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተጠየቀ

ጃዋር መሐመድ፣ ብርሃመነ መስቀል አበበ፣ በቀለ ገርባ

እነ አቶ ጃዋር መሐመድ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ ላይ ነጻ ሆነን የመታየት መብታችንን የሚቃረን አስተያየት በመስጠታቸው ፍርድ ቤቱ እንዲጠይቅላቸው አቤቱታ አቀረቡ።

አቶ በቀለ ገርባና ጀዋር መሐመድ የጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት በመገኘት ለጋዜጠኞች የሰጡት መግለጫ ነጻ ሆኖ የመታየት መብታቸውን የሚጻረር መሆኑን እና ለህይወታቸው አስጊ እንደሆነ ዛሬ ለተሰየመው ፍርድ ቤቱ ገልፀዋል።

"እኛ ላይ ምስክሮች እንኳ ሳይሰሙ፣ የፖለቲካ ባለስልጣናት፣ በተለይም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ፍርድ ቤቱ እኛ ላይ ውሳኔ እንዳስተላለፈ አድርገው ነበር የተናገሩት" ያሉት አቶ ጃዋር መሐመድ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መግለጫ ለህይወታቸው አስጊ መሆኑን ተናግረዋል።

"ጽንፈኞች ተብለናል፤ እንዲሁም ግርግር እንደፈጠርን እና ሰው እንደገደልን ወስነዋል" በማለት የጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞትዮስ ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲጠየቁ አቤቱታቸውን አሰምተዋል።

አቶ በቀለ ገርባም " ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ እኛ መከላከል በማንችልበት ሁኔታ ለውጪ አገር ሚዲያዎች መግለጫ ሰጥተዋል። ይህም የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ገለልተኛ መሆን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው" በማለት ዶ/ር ጌዲዮን ፍርድ ቤት ቀርበው መጠየቅ አለባቸው ሲሉ ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱም በበኩሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በሚቀጥለው ቀጠሮ ላይ በጽሑፍ ምላሽ እንዲሰጡ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

የዛሬ ችሎት ውሎ

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቶ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ በ24 ሰዎች ላይ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የከፈተውን ክስ ለተከሳሾች አንብቧል።

ፍርድ ቤቱም ከተራ ቁጥር 1 እስከ 15 ድረስ ያሉ ተከሳሾችን ብሔርን እና ሐይማኖትን መሰረት ያደረገ ሁከት በመፍጠር በአዲስ አበባ ከተማ የ13፣ በኦሮሚያ ክልል ደግሞ 167 ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ 360 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት እና 4.6 ቢሊዮን ብር በላይ የተገመተ ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን አንብቧል።

ከዚህም ውጪ ያለፈቃድ የጦር መሳሪያዎችን ይዘው በመገኘትና የቴሌኮም ማጭበርበርን መፈፀም የሚሉ ጉዳዮች ክሱ ውስጥ የተካተቱ ጉዳዮች ናቸው።

18ኛ ፣ 21ኛ፣ 6ኛ፣ 8ኛ፣ 9ኛ፣20፣7ኛ ተከሳሾች አማርኛ የማይሰሙ መሆናቸው ተገልጾ እነርሱ ላይ የቀረበውን ክስ አለመረዳታቸውን ለፍርድ ቤቱ አስታውቀዋል።

ጠበቆቻቸው ደግሞ በደንበኞቻቸው ላይ የተከፈተውን ክስ ማረሚያ ቤት በመገኘት ማሳወቅ እንደሚችሉ ለፍርድ ቤቱ ገልፀዋል።

ፍርድ ቤቱም የተከሳሽ ጠበቆችን ሁሉንም በተመሳሳይ ሰዓትና ቦታ አግኝተዋቸው እንዲወያዩ ማረሚያ ቤት ሁኔታውን እንዲያመቻች ትዕዛዝ ሰትቷል።

አቤቱታና የፍርድ ቤት ትዕዛዝ

በዛሬ የፍርድ ቤት ውሎ ተከሳሾችና ጠበቆቻቸው እንዲሁም ዐቃቤ ሕግ የተለያዩ አቤቱታቸውን ለፍርድ ቤት በማቅረብ ፍርድ ቤቱም ትዕዛዝ ሰጥቶባቸዋል።

ተከሳሾች እጃቸው በካቴና ታስሮ ረዥም ሰዓት መቆየታቸውንና እንዲፈታ ጠይቀው እምቢ መባላቸውን፤ እንዲሁም ጠዋት ቁርስ ሳይበሉ ወደ ፍርድ ቤት መወሰዳቸውን በመግለጽ አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ ለምን በካቴና እንደታሰሩ ማረሚያ ቤቱ በጽሁፍ ምላሽ እንዲሰጥ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ከዚህ በተጨማሪ ተከሳሾች ማለዳ ወደ ፍርድ ቤት ሲወሰዱ እስር ቤቱ ቁርስ እንዲያቀርበላቸው ፍርድ ቤቱ አዟል።

የተከሳሽ ጠበቆች ሸምሰዲን ጠሃ የኢሬቻ በዓል ላይ እንዲገኝ ያቀረበውን ጥያቄ ትዕዛዝ ይሰጥልን በማለት ጠይቀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ተከሳሾች የባህል ልብስ እንዲገባላቸውና የኢሬቻን በዓል እስር ቤት በጋራ እንድናከብር ይፈቀድልን ሲሉ ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱም ሸምሰዲን ጠሃ ኢሬቻ ላይ ተገኝቶ በዓሉን እንዲያከብር ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ ያደረገ ሲሆን፤ ተከሳሾች ግን የባህል ልብስ ገብቶላቸው ከዚህ በፊት የተለያዩ የእምነት በዓላት ሲከበሩ እንደቆየው እንዲያከብሩ ሁኔታዎች እንዲመቻችላቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በተጨማሪም ባህር ማዶ ቤተሰብ ያላቸው እስረኞች ቤተሰቦቻቸውን በግል ስልካቸው እንዲያገኟቸው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

ሸምሰዲን ጠሃ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት ድብደባ ስለደረሰባቸው ጆሯቸው መጎዳቱንና የሕክምና አገልግሎት እያገኙ አለመሆኑን ጠበቆቹ ጨምረው ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቱም አገልግሎቱን ለምን እንዳላገኙ ማረሚያ ቤቱ እንዲገልጽና ዛሬውኑ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በሌላ በኩል ደግሞ የደኅንነት ስጋት እንዳለባቸው የገለፁት የኦፌኮ አመራሩ ደጀኔ ጣፋ አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን በዚህ ጉዳይም ማረሚያ ቤቱ በጽሁፍ ምላሸ እንዲሰጥ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

አቶ ደጀኔ ጣፋ ከዚህ በፊት ሌላ ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን ያ ክስ መቋረጡን ዳኞች በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ ላይ ገልፀዋል።

በተጨማሪም እነ ደጀኔ ጉተማ፣ ዶ/ር ብርሃነ መስቀል አበበ፣ ፀጋዬ ረጋሳ ላይ ዐቃቤ ሕግ በጋዜጣ እንዲጠሩ ትዕዛዝ እንዲሰጥ የጠየቀ ሲሆን ፍርድ ቤቱም የጋዜጣ ጥሪ እንዲደርግ አዟል።

በስተመጨረሻም ተከሳሾች፣ ጠበቆቻቸው የክስ መቃወሚያ ጥቅምት 23/2013 ዓ.ም ለፍርድ ቤቱ ሬጂስትራር እንዲያቀርቡና እና ዐቃቤ ሕግ ምላሹን ለኅዳር 18/2013 ችሎት ይዞ እንዲቀርብ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።