የስዊዲኑ ልብስ አምራች ኤች ኤንድ ኤም (H&M) የችርቻሮ መደብሮቹን እየዘጋ ነው።

በሞስኮ የሚገኘው የኤች ኤንድ ኤም ሱቅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዓለም ግዙፍ ከሚባሉት የልብስ አምራቾች አንዱ የሆነው የስዊዲኑ ኤች ኤንድ ኤም በቅርቡ ብቻ 250 ማከፋፈያዎችን ሊዘጋ ነው፡፡

እነዚህን ሱቆች የሚዘጋው በሚቀጥለው ዓመት ነው፡፡

ይህን ሁሉ ማከፋፈያና የችርቻሮ መሸጫ ሱቅ ለመዝጋት እንዲወስን ያደረገው ደግሞ በርካታ ደንበኞች ግዢ የሚፈጽሙት ሱቅ እየመጡ ሳይሆን ባሉበት ሆነው በድረ ገጽ መንገድ በመሆኑ ነው፡፡

የገበያው ሁኔታ ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ አሁን ወደነበረበት እየተመለሰ ነው ያለው ድርጅቱ፣ ነገር ግን በያዝነው መስከረም ሽያጭ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር በ5 እጅ ዝቅ ብሎብኛል ይላል፡፡

ኤች ኤንድ ኤም በመላው ዓለም 5ሺ የችርቻሮ መደብሮች አሉት፡፡

አሁን እዘጋቸዋለው ያላቸው መደብሮች የት አገር የሚገኙትን እንደሆነ ለጊዜው አልገለጸም፡፡

በዚህ ረገድ ገና የተብራራ ውሳኔ ላይ አልደረስንም፡፡ እንደ አገሩ ሁኔታና እንደ ገበያው እያየን የምንዘጋ ይሆናል ብሏል ቃል አቀባዩ፡፡

ኤች ኤንድ ኤም አብዛኛዎቹ ከመደብሮች ጋር የሚፈራረመው የኮንትራት ስምምነት በየዓመቱ ኪራይ ሱቆችን የመዝጋት፣ ዋጋ የመደራደር ዕድሎችን ይሰጡታል፡፡

ኤች ኤንድ ኤም ከታክስ በፊት 2.3 ቢሊዮን የስዊድሽ ክሮነር አትርፌያለው ብሎ ነበር፡፡ ድርጅቱ ትርፌ በዚህ ዓመት ወድቋል ቢልም ይህ ብዙ የምጣኔ ሀብት ተንታኞች ከጠበቁት በጣም የተሻለ የሚባል ነው፡፡

ድርጅቱ በኮሮና ምክንያት በመላው ዓለም 166 መደብሮቼ እንደተዘጉ ናቸው ብሏል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ የሚከፈቱት ለተወሰኑ ሰዓታት ብቻ ነው፡፡

የዓለም ትልልቅ ድርጅቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የችርቻሮ መደብሮች አስፈላጊነት ላይ ጥያቄ እያነሱ መሆናቸው የሚታወስ ነው፡፡

የኢንተርኔት መስፋፋትና የክፍያ መዘመን ከጊዜና ገንዘብ ቁጠባ ጋር ተያይዞ ግብይት በበይነ መረብ እየተቀላጠፈ መምጣቱ ምናልባት ወደፊት የችርቻሮ ሱቆች እምብዛምም ላያስፈልጉ ይችላሉ የሚሉ ትንበያዎች እንዲነሱ እያደረገ ነው፡፡