ምርጫ፡ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ፀጉር ላይ ያረፈችው ዝንብ ዓለምን እያነጋገረች ነው

ማይክ ፔንስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አንዲት ዝንብ ዓለምን እያነጋገረች ነው፡፡

ትናንት ምሽት ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስና ሴናተር ካመላ ሐሪስ ክርክር አድርገዋል፡፡ ያውም ለ90 ደቂቃ፡፡

‹ጨዋታው› በመደበኛው 90 ደቂቃ የሚጠናቀቅ ዓይነት አልነበረም፡፡ ማን አሸነፈ ብለን ከጠየቅን ምላሹ እንደ ዳኛው ይወሰናል፡፡

ለምሳሌ ሴኤንኤን ካመላ ሐሪስ ‹በከፍተኛ የግብ ብልጫ› ፔንስን እንደዘረረች ይናገራል፡፡ ፎክስ ኒውስ ማይክ ፔንስ ያስቆጠሩት የክርክር ጎል በዓለም ታይቶ አይታወቅም እያለ ነው፡፡

ለዚህ ነው አሸናፊው እንደ ዳኛው ይወሰናል ያልናችሁ፡፡

ከሌሊቱ የፖለቲካ ክርክርና እሱን ተከትሎ ከተፈጠረው የትንታኔ ግርግር ሁሉ የማኅበራዊ ሚዲያውን ትኩረት ያገኘቸው ያልተጠበቀች በራሪ ነፍሳት ሆናለች፡፡

ጋዜጠኛ ሱሳን ፔጅ እንኳ 90 ደቂቃ ውድድሩን በመሀል ዳኝነት መርታ የዚህችን ነፍሳት ያህል ትኩረት አላገኘችም፡፡

ማይክ ፔንስ ኳስ የመሰለ ክብ ጭንቅላት ነው ያለቸው፡፡ ጭንቅላታቸውን የሞላው ግርማ ሞገስን የሰጣቸው ነጭ ሽበት ነው፡፡ ይቺ ጠቋራ ዝንብ በዚህ ነጭ ጸጉር ላይ አረፈች፡፡ ልክ በጥጥ ክምር ላይ ጥቁር አሞራ ሲያርፍ እንደማለት ነው፡፡

ዝንቦች በባህሪያቸው ቶሎ አርፈው ቶሎ ይበራሉ፡፡ ይቺ ግን የፔንስን ጭንቅላት ኢንዲያና ግዛት አስመሰለችው፡፡ ለ2 ደቂቃ ያህል ነቅነቅ አልል ብላ ነበር፡፡

እውነት ለመናገር የትናንቱ ክርክር ቁም ነገራም ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ለሚዲያ የሚመች አይደለም፡፡ ጎል ያልተቆጠረበት የ90 ደቂቃ እግር ኳስ በሉት፡፡

እግር ኳስ ቢያንስ በፍጹም ቅጣት ምት አሸናፊው ይለያል፡፡ ይህ ክርክር ግን 90 ደቂቃ ቆይቶም አሸናፊውን ለመለየት የማይመች ነበር፡፡

የሌሊቱ ፖለቲካዊ ክርክር እንደ ትራምፕና ባይደን መደናቆር ያልነበረት በመሆኑ ተሞግሷል፡፡ ቢያንስ ፔንስና ሐሪስ ተደማምጠዋል፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው ይሄ?

ለሚዲያ የሚመችም አልነበረም፡፡ ርዕሰ ዜና የሚሆን ነገር የሚወጣው አልነበረም፡፡ ከአለቆቻቸው በሰል ብለው የታዩት ፔንስና ሐሪስ ጥሩ ነጥቦችን ያነሱ ቢሆንም ለሚዲያ እርእስት የሚሆን ነገር ዝር አላለም፡፡

ዝር ያለችው አንዲት ዝንብ ትኩረት ብታገኝ የማይገርመው ለዚሁ ነው፡፡

በ90 ደቂቃ ክርክር ምንም ለየት ያለ ነገር ከሌለ ጋዜጠኞች ምን ይጻፉ ታዲያ? ይቺ ዝንብ ባትኖር ምን ይውጣቸው ነበር? የሚዲያ አምላክ ይሆን የላካት?

ይቺ ዝንብ ከትናንት ሌሊት ጀምሮ የአሜሪካን ማኅበራዊ ሚዲያ ሁነኛ ርእስ ለመሆን በቅታለች፡፡ ከአሜሪካን አልፋ ዓለምን አዳርሳለች፡፡ ሰው ሆና ኢኒስታግራም ብትከፍት 50 ሚሊዮን ተከታዮችን ታፈራ ነበር፡፡

የአሐዝ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡ ዝንቧ ወይም "the fly" የሚለው ቃል በትዊተር እሽክርክሪትና ቅብብሎሽ 700,000 ጊዜ በላይ ተጋርቷል፡፡

የጆ ባይደን የምርጫ ቅስቀሳ ሰዎች ይህን አጋጣሚ ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል ያደረጉት ሙከራ ተሳክቶላቸዋል፡፡

ዝንቧም ትመርጣለች ወይም በእንግሊዝኛው "flywillvote.com" የሚል ድረ ገጽ በመክፈት ባይደን ዝንብ መግደያ ወንፊት እንዲይዙ በማድረግ ሳቢ ምሥል በማስቀመጥ ሰዎች የምርጫ ምዝገባ እንዲያደርጉ ማድረግ ተችሏል፡፡ ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች ይህንን ሐሳብ ወደነዋል ብለዋል፡፡

ይህ ምርጫ እንዲሰምር ለዝንቧ 5 ዶላር ይለግሱ የሚለው የገንዘብ ማሰባሰብያ ውጤታማ ሆኗል፡፡ ትራምፕ በዚህ ጉዳይ ላይ በትዊተር ሰሌዳ የጻፉት ነገር ሩብ ሚሊዮን ሰዎች አጋርተውታል፡፡

የዝንብ መግደያ ወንፊት ለገቢ ማስገብያ ውሎ ጠቀም ያለ ገንዘብ ሳያስገባ አልቀረም፡፡ በባይደን የምርጫ መሪ ቃል ማለትም (truth over lies) ትሩዝ ኦቨር ላይስ በሚለው ምትክ ትሩዝ ኦቨር ፍላይስ (truth over flies) ወደሚለው ተከሽኖ ቀርቦ በአጭር ሰዓት ውስጥ ተሸጦ አልቋል፡፡

የሚገርመው ይቺ ዝንብ ዋልታ ረገጥ ሆነው የቆሙትን ዲሞክራቶችንና ሪፐብሊካንን ማቀራረቧ ነው፡፡ የሁለቱ ፓርቲ ደጋፊዎች ለመጀመርያ ጊዜ በጋራ የሚስቁበትን ነገር አግኝተዋል፡፡

አንዳንዶች ይቺን ዝንብ ለፈጠረችው መቀራረብ የአሜሪካ ጀግኒት "an American hero" የሚል ስም ሰጥተዋታል፡፡ ለሌሎች ደግሞ ምንም ትዝታ ካልነበረው ምሽት የተገኘች አይረሴ ሲሉ አቆላምጠዋታል፡፡

የቀድሞዋ የዋይት ሐውስ አማካሪ ኬሊኒ ኮኔይ ዝንቧ ድምጽ የመስጠት እድል ሊሰጣት ይገባል ብለው የቀለዱ ሲሆን፣ የሪፐብሊካኑ ሴናተር ራንድ ፓል በበኩላቸው ዲሞክራቶች እኛን ለመሰለል ነፍሳትን እየላኩብን ለመሆኑ ማስረጃ ናት ሲሉ ቀልደዋል፡፡

የዓለም ትልቁ መዝገበ ቃላት ሜሪየም ዌብስተር በበኩሉ ዝንብ "fly" የሚለው ቃል በዓለም ላይ ከትናንት ሌሊት ጀምሮ እጅግ ተወዳጅ ቃል እንደሆነ ይፋ አድርጓል፡፡ ከዚህ በፊት ይህ ቃል በመዝገበ ቃላቱ ድረ ገጽ እንዲህ ተፈላጊ ቃል ሆኖ አያውቅም፡፡

የዛሬ አራት ዓመት ግድም በተመሳሳይ አንዲት ዝንብ ሒላሪ ክሊንተን አናት ላይ አርፋ መነጋገርያ ሆና ነበር፡፡ አንዳንዶች ያቺው ዝንብ ትሆን ፔንስ ጭንቅላት ላይ ያረፈችው ሲሉ አሽሟጠዋል፡፡

ሌሎች ደግሞ ዝንቧ ተሸናፊዎች ጭንቅላት ላይ እንደምትወጣ በመተንተን ምርጫውን እነ ጆ እንደሚያሸንፉ ተንብየዋል፡፡

አንዳንድ ሰዎች ግን ቀልድ ብሎ ነገር አያውቁም፡፡ ለምሳሌ ቤን ሻፒሮ ዝንቧ አላሳቀቻቸውም፡፡ ፔንስ ሐሪስን ድምጥማጧን አጥፍቷታል፡፡ ይህንን ድልን ለማንኳሰስ ነው ዝንቧ ጉዳይ ሆና እየተራገበች ያለቸው ብለዋል በትዊተር ሰሌዳቸው፡፡

እየቀለዱ አይደለም፡፡ ወግ አጥባቂ የፖለቲካ ተንታኝ ናቸው፡፡