ትግራይ፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ 'ክልሉን ከፌዴሬሽኑ እንዲወጣ የሚገፋ ነው'፡ የትግራይ ምክትል ፕሬዝዳንት

የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር አብርሃም ተከስተ

የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገወጥ መንገድ የተቋቋመ ነው ላለው የትግራይ ክልል ም/ቤትና ካቢኔ የፌዴራል መንግሥት የበጀት ድጎማ እንደማያደርግ መግለጹ ክልሉን ከፌዴሬሽኑ እንዲወጣ የሚገፋ ነው አሉ።

ይህ ውሳኔ እስካሁን ሲወሰድ የነበረው "ሕገወጥ እርምጃ" ቀጣይ አካል ነው ያሉት አብርሃም (ዶ/ር)፣ እርምጃው ኃላፊነት የጎደለው ከመሆኑ በተጨማሪ "የትግራይ ክልልን ከፌዴሬሽኑ እንዲወጣ የሚገፋ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀደም ብሎ የትግራይ ክልል ምክር ቤትና ከፍተኛ የሕግ አስፈፃሚው አካል በሕገመንግሥቱ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ሁሉም የፌዴራል ተቋማት ምንም ዓይነት ሕጋዊ ግንኙነት እንዳያደርግ የወሰነ ሲሆን፤ በማስከተልም ከፌዴራል መንግሥቱ የሚደረግ የበጀት ድጎማን እንዳያገኝ መወሰኑን የምክር ቤቱ አፈጉባኤ ለብሔራዊው ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

ይህንን ውሳኔ በሚመለከት አብረሃም ተከስተ (ዶ/ር) ለቢቢሲ እንደተናገሩት ምክር ቤቱ የፌደራል መንግሥት ከክልሎች ከሚሰበስበው ገቢ ላይ ለትግራይ ክልል መንግሥት ድጎማ እንዳይሰጥ ውሳኔ ማሳለፉ "በሌላ አገላለጽ ትግራይ የፌዴሬሽኑ አካል አይደለችም እንደ ማለት ነው" ብለዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤቱን ውሳኔ "በትግራይ ክልልና ሕዝብ ላይ ጦርነት እንደማወጅ" አድርገው እንደሚቆጥሩት የተናገሩት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ ለዚህም ደግሞ ምክንያታቸውን ሲገልፁ ፌዴሬሽኑ እና የፌዴሬሽኑ አባል መንግሥታት አንዱ የሚያገናኛቸው የበጀት ሥርዓቱ መሆኑን አመልክተዋል።

የትግራይ ክልል የፌዴሬሽኑ አባል ናት ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንት አብረሃም (ዶ/ር)፤ እርምጃው ፌዴሬሽኑን የሚበትን ነው ብለዋል።

የፌዴሬሽኑ አባላት አንዱ መሳሪያ የበጀት ግንኙነቱ ነው የሚሉት አብረሃም (ዶ/ር) ትግራይን ከበጀት ውጪ ማድረግ ማለት "ከፌዴሬሽኑ እንድትወጣ የሚገፋ ነው" ነው ሲሉ ተናግረዋል።

እርምጃውን "በጣም አደገኛ" ያሉት አብረሃም (ዶ/ር)፣ አገሪቷን ወደ ቀውስ የሚያስገባ፣ የሚበትን በማለት "ኃላፊነት የጎደለው እርምጃ" ሲሉም ኮንነውታል።

የፌደራል መንግሥት ገቢ የሚሰበስበው ትግራይን ጨምሮ ከክልሎች ነው ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ይህንኑ መልሶ ለክልሎች እንደሚያከፋፍልም ተናግረዋል።

ከትግራይ የሚሰበስበውን ገቢ ለትግራይ አላካፍልም ማለት "እብደት ነው" በማለት ውሳኔውን አጣጥለውታል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ እንዳለው ወደዚህ እርምጃ የሚገባ ከሆነ ክልሉ ለፌደራል መንግሥቱ ከትግራይ የሚሰበስበው ገቢ ላይ እርምጃ እንደሚወስድም አመልክተዋል።

እርምጃው ምን ዓይነት ነው ተብለው የተጠየቁት አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) የፌደራል መንግሥት ባለፈው ዓመት ብቻ ከትግራይ ክልል ወደ ሰባት ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን፣ በዚህ በተያዘው 2013 ዓ.ም ደግሞ ወደ ዘጠኝ ቢሊየን ብር እሰበስባለሁ ብሎ ማቀዱን ገልፀዋል።

ስለዚህ ይህንን ሰብስቦ ሕጋዊ የፌዴሬሽኑ አካል ለሆነችው ትግራይ አላከፋፍልም የሚል መንግሥት "የእብደት ሥራ ነው" በማለት እንዲሁ ዝም ብለን አናይም ሲሉ ተናግረዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገወጥና ተፈጻሚነት የሌለው ነው ያለውና ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በተለየ በትግራይ ክልል በተናጠል የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ የተቋቋማው የክልሉ መንግሥት ላይ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

በዚሁ መሰረትም ሁሉም የፌዴራል ተቋማት ከትግራይ ክልል ከፍተኛ አስፈፃሚ አካላት ጋር እንደሕጋዊ አካላት በመቁጠር ደብዳቤ መፃፃፍ፣ መረጃ መላላክ፣ የፌዴራል ተቋማት ለክልል ተቋማት የሚሰጧቸውን ድጋፎች መስጠት፣ በፌዴራል ደረጃ የሚካሄዱ መድረኮች ላይ ማሳተፍ የመሳሰሉ ጉዳዮችን እንዳያከናውኑ ወስኗል።

ከዚህም ጎን ለጎን የክልሉ ሕዝብ መሰረታዊ የልማትና የአገልግሎት ተጠቃሚነቱ እንዳይስተጓጎል እንደ ቀበሌ ፣ወረዳ ፣ ከተማ ካሉ ሕጋዊ መዋቅሮች ጋር ብቻ ግንኙነት እንደሚደረግና በዚህም ላይ ክትትል እንደሚደረግ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አደም ፋራህ ለኢቲቪ ተናግረዋል።

የበጀት ድጎማን በተመለከተም "በሕገወጥ መንገድ የተቋቋመው የትግራይ ምክር ቤትና ካቢኔ ሕጋዊ ሰውነት ስለሌለው" ከፌዴራል መንግሥት የበጀት ድጎማ እንደማያገኝ ተነግሯል።

ነገር ግን የፌደራል መንግሥቱ በትግራይ ክልል ካሉ የከተማ አስተዳደሮች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ጋር በሚኖር ግንኙነት አማካይነት ሕዝቡ ማግኘት የሚገባውን መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲያገኝ የሚደረግ መሆኑና ክትትልም እንሚደረግበት ተነግሯል።