ኖቤል፡ የዘንድሮ የሥነ ጽሑፍ የኖቤል ሽልማት ያሸነፈችው ሴት ማን ናት?

አሜሪካዊቷ ገጣሚ ሉዊስ ግሉክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዛሬ ቀትር ላይ በሥነ ጽሑፍ ዘርፍ የኖቤል ተሸላሚ ማን እንደሆነች ይፋ ተደርጓል፡፡

አሜሪካዊቷ ገጣሚ ሉዊስ ግሉክ ናት ተሸላሚዋ፡፡

ሉዊስ አሸናፊ መሆኗ ሲነገራት እጅግ እንደተደነቀች በመድረኩ ተገልጿል፡፡

ሉዊስ ‹‹ያለምንም ጥያቄ ለሥነ ግጥም የተሰጠች ናት፡፡ በሥራዎቿም ወደኋላ ማለትን አታውቅም›› ብሏል የስዊድሽ አካዳሚ በሥነ ሥርዓቱ ላይ።

ሉዊስ ግሉክ የተወለደችው እንደ አውሮጳዊያኑ በ1943 በኒውዮርክ ከተማ ነው፡፡

ከዚያ በኋላ የኖረችው በማሳቹሴት ሲሆን በዬል ዩኒቨርስቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ፕሮፌሰር ሆና አገልግላለች፡፡

ሉዊስ ግሉክ ከ2010 ወዲህ የሥነጽሑፍ ኖቤል ለማሸነፍ 3ኛዋ ሴት ናት፡፡ ኖቤል ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ 16 ሴቶች ብቻ ናቸው በሥነ ጽሑፍ ማሸነፍ የቻሉት፡፡

ሉዊስ ግሉክ ከኖቤል ወዲያ ያሉ ሽልማቶች የቀራት የለም፡፡

ትልቁን የፑልትዘር ሽልማት በ1993 አግኝታቸለች፡፡ ዘ ዋይልድ አይሪስ እና የናሽናል ቡክ አዋርድ በ2014 ወስዳለች፡፡

በሥነ ግጥም ደግሞ በ2001 የቦሊንገን ሽልማትን አሸንፋለች፡፡

በ2008 ደግሞ የዋላስ ስቲቨንስ ሽልማትን ወስዳለች፡፡

በ2015 ደግሞ የናሽናል ሂይማኒቲስ ሜዳል አዋርድን አሸንፋለች፡፡

የግጥም ሥራዎቿ በብዛት ሰው የመሆን ጣጣ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ የሰው ልጆች ያሉባቸውን መከራና ስቃይ፣ ሞትና ሕይወት ልጅነትና የቤተሰብ ሕይወት በብዛት በሥራዎቿ ይንጸባረቃሉ፡፡

ከዚህ ቀደም የኖቤል አሸናፊዎች ሽልማታቸውን ከስዊድን ንጉሥ ካርል 16ኛ ጉስታፍ በስቶክሆልም ይወስዱ የነበረ ሲሆን አሁን ግን በወረርሽኙ ምክንያት ይህ ሊሆን አልቻለም፡፡ ወደ አንድ ሚሊዮን ዶላር የተጠጋ ገንዘብ ይሰጣታል፡፡

ግሉክ አሁን 77 ዓመቷ ነው፡፡

ከሥራዎቿ መካከል ‹‹ዘ ዋይልድ አይሪስ›› እና‹‹ ዘ ትራይምፍ ኦፍ አኪሊስ›› ‹‹አቨርኖ››፣ እና ‹‹አራራት›› ይጠቀሳሉ፡፡

እስከዛሬ 30 የእንግዝኛ፣ 15 የፈረንሳይኛ ፣ 2 የቻይንኛ ጸሐፊዎች ኖቤል ማሸነፍ ችለዋል፡፡ ከአረብ ጸሐፊዎች አንድ ደራሲ ብቻ ነው ኖቤል ማሸነፍ የቻለው፡፡ እሱም ግብጻዊው ናጂብ ማኅፉዝ ነው፡፡