ታላቁ ህዳሴ ግድብ፡ የግብፅና የኬንያ መሪዎች በህዳሴው ግድብ ውዝግብ ላይ መወያየታቸው ተገለጸ

ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ እና አብዱል ፈታህ አል ሲሲ

የፎቶው ባለመብት, State House Kenya

የምስሉ መግለጫ,

ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ እና አብዱል ፈታህ አል ሲሲ

የግብፁ ፕሬዚደንት አብደል ፈታህ አልሲሲ እና የኬንያው ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ በኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ውዝግብ ላይ መወያየታቸውን የግብፅ ባለሥልጣናት አስታወቁ።

ፕሬዚደንት ኡሁሩ ባለፍነው እሁድ ከፈረንሳይ ወደ አገራቸው ሲመለሱ እግረ መንገዳቸውን ወደ ግብፅ ተጉዘው ከአገሪቱ መሪ ጋር ካይሮ ላይ መገናኘታቸው ተገልጿል።

ከግብፅ ቃል አቀባይ የተሰጠ መግለጫ እንዳመለከተው "በስብሰባው ላይ በቀጠናው ስላሉ የጋራ የልማት ጉዳዮች፣ በተለይ ደግሞ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይ ተነጋግረዋል። በቀጣይነትም ሁለቱ አገራት ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል" ብሏል።

ይሁን እንጂ ኬንያ በግድቡ ጉዳይ ላይ መወያየታቸውን አልገለጸችም። ከኬኒያ በኩል የተባለው ሁለቱ መሪዎች በሁለትዮሽ ግንኙነታቸው ላይ መነጋገራቸውን ነው።

ከእነዚህም መካከል በቀጠናው ሰላም እና ፀጥታ፣ ንግድ እና አፍሪካ ለኮቪድ-19 የሰጠችው ምላሽም በውይይታቸው ውስጥ እንደተካተተ ተጠቅሷል።

ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ በተነሱ ሕጋዊና ቴክኒካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሱዳንና ከግብፅ ጋር ለዓመታት ስታካሂዳቸው የነበሩ ድርድሮች እስካሁን ድረስ መቋጫ አላገኙም።

መጀመሪያ ላይ በአሜሪካና በዓለም ባንክ አሸማጋይነት ሲደረግ የነበረው ድርድር ፍሬ ባላማፍራቱም ጉዳዩ ወደ አፍሪካ ሕብረት መጥቶ ድርድር ሲካሄድ ቆይቷል።

በህዳሴ ግድብ ውዝግቡን ለመፈታት በአፍሪካ ሕብረት አሸማጋይነት በተመራው የድርድር ሂደት ኬንያ ሌላኛዋ ታዛቢ እንደሆነች ተገልጿል።

ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ በሕብረቱ አሸማጋይነት ሲካሄድ የነበረው የሦስትዮሽ ድርድር ያለስምምነት መጠናቀቁንም የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ከአገራቱ ጋር ከስምምነት ለመድረስ ፍላጎት እንዳላት በተደጋጋሚ የገለጸች ሲሆን፤ ነገር ግን በድርድሮቹ የሚገኘው ውጤት ግድቡን ውሃ ከመያዝና ሥራውን ከማስጀመር እንደማያግዳት በተደጋጋሚ ስትገልፅ ቆይታ ነበር።

ሱዳንና ግብጽ በበኩላቸው ግድቡ ከሚያገኙት ዓመታዊ የውሃ መጠን ላይ መቀነስን ስለሚያስከትል ከስምምነት ከመደረሱ በፊት የውሃ ሙሌቱ እንዳይጀመር ሲወተወቱ ቆይተዋል።

ይሁን እንጅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ዙር የግድቡ የውሃ ሙሌት መጠናቀቁን ሐምሌ 15/2012 ዓ.ም አስታውቀዋል።

ከዚያም በኋላ ድርድሩ እንደቀጠለ ነው።

ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ በአባይ ውሃ ላይ የተመሰረተችው ግብፅ፤ በቅርቡ ግድቡ ለሕዝቦቿ ህልውና ስጋት ነው ስትል ተቃውሞዋን ስትገልጽ ቆይታለች።

ለአስር ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ተደርጎበት እየተገነባ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታው ከሦስት አራተኛው በላይ መጠናቀቁ ተገልጿል።

ቢሆንም ግን በግድቡ ዙሪያ በተነሱ ሕጋዊና ቴክኒካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ኢትዮጵያ ከሱዳንና ከግብፅ ጋር ለዓመታት ስታካሂዳቸው የነበሩት ድርድሮች እስካሁን መቋጫ አላኙም።

ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለ65 ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን የኤሌክትሪክ ኃይል አንዲያገኙ ያስችላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።