የአንበጣ መንጋ ፡ በአማራ ክልል የአርሶ አደሮችን ልፋት መና እያስቀረ ያለው አንበጣ መንጋ

አንበጣ የሚያባርሩ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አቶ ይማም መሐመድ በራያ ቆቦ ወረዳ የ024 ያያ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው።

በአካባቢው ጤፍ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ አተርና ሽንብራ የሚመረት መሆኑን ጠቅሰው አብዛኛው ማሳ የተሸፈነው በማሽላ እንደሆነ ይናገራሉ።

ቀደም ሲል በአፋር ክልል የአንበጣ መንጋ መከሰቱን እንደሰሙ እና ወደ አካባቢያቸው ሳይመጣ ለመከላከል እንዳልተቻለ ጠቁመዋል።

መስከረም 6 ጀምሮ ወደ አካባቢው መግባት የጀመረው የበረሃ አንበጣ መንጋን ለመከላከል ጥረት ቢያደርጉም መከላከል አልቻልንም ብለዋል።

"አንዱን ንዑስ ቀበሌ ሲያጠናቅቅ [እኛም] እያፈገፈግን ስንከላከል አሸነፈን። አሁን ሙሉ በሙሉ [ሰብሉን] አጠናቀቀ" ሲሉ የለፉበት ሰብል መውደሙን ይናገራሉ።

''[አሁን] ዝም ብለን ቆመን እያየን ነው። ተዓምር ነገር ነው የምናየው።"

"ከመስከረም 6 እስከ አሁን አርሶ አደሩ ቤቱ ሳይገባ ታገለ። ምንም ማድረግ አልተቻለም. . . የሚበላብንን ነገር ጨርሷል፤ ከእንግዲህ ወዲያ ተስፋ የለንም" ብለዋል።

በቀበሌው ያለውን ሰብል ሙሉ ለሙሉ ከመጨረስ ባለፈ ወደ አጎራባች ቀበሌዎች እየገባ መሆኑንም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የዘንድሮ አዝመራ 'ጥሩ እና ቆንጆ' የሚባል እንደነበር የሚናገሩት አቶ ይማም፤ ሆኖም የአንበጣው መንጋ እንዳወደመውና መንግሥት ኬሚካል አቅርቦ፣ አርሶ አደሩ ደግሞ ጅራፍ እና ቆርቆሮ በመጠቀም በዘመናዊ እና ባህላዊ መንገድ ለመከላከል የተደረገው ጥረት አልተሳካም ብለዋል።

እህል ከኅዳር አጋማሽ ጀምሮ ነበር መሰብሰብ የነበረበት ያሉት አርሶ አደሩ ለመሰብሰብ ያልደረሰ በመሆኑ በአንበጣ መንጋው መበላጡን ጠቁመዋል።

የአንበጣ መንጋው ባደረሰው ጉዳት ግራ የተጋቡት አርሶ አደሩ ምንም ማድረግ እንዳልቻሉ ይናገራሉ። "ዝም ብለን ቁጭ ብለናል። ከባድ ነው በጣም። ዝናብ ከጣለ ለበልግ እናርሳለን ብለን ቁጭ ብለናል" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

አርሶ አደር ሙስጠፋ አሸብርም የራያ ቆቦ ነዋሪ ናቸው።

ከመስከረም መጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ አንበጣውን በኬሚካልም ሆነ በባህላዊ መንገድ ለመከላከል ባለመቻላቸው አካባቢውን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሮታል ብለዋል።

"ቀደም ብሎ ሁለት ቀበሌዎች ገባ። ቀዳሚዎቹ ንዑስ ቀበሌ 2 እና 3 ናቸው። አዚያ አሁን ሰብሉ አልቋል። አሁን ወደ ንዑስ ቀበሌ አንድ አቀንቷል። አዚያ አዳርሶ ወደ ቀበሌ 023 ሊገባ ነው" ሲሉ አስረድተዋል።

"ጥይት ቢተኮስ፣ እሪ ቢባል እና መርዝ ቢረጭ አንዴ ከገባ አይነሳም" ሲሉ የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል እንደተቸገሩ ይናገራሉ።

አንበጣው ባለባቸው አካባቢዎች ሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱንም ጠቀሙዋል።

"ተስፋችን ምናልባት የበልግ ዝናብ ከጣለ በልግ እንዘራለን ነው እንጂ ምን ተስፋ አለን?" ሲሉ ማሳ ላይ የነበረው ሰብል መውደሙን አመልክተዋል።

መንግሥት ዝናብ አግኝተው ለበልግ እስኪዘሩ ድረስ ድጋፍ እንዲያደርግላቸውም ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግሥቴ የአንበጣው መንጋ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ጉዳት ማድረሱን አረጋግጠዋል።

ጉዳቱ በምሥራቅ አማራ ሦስት ዞኖች መከሰቱን ጠቁመው መጠኑ ግን በባለሙያዎች ተጠንቶ ይፋ ይደረጋል ብለዋል።

የአንበጣ መንጋው በደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ እና ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች መከሰቱን ገልጸው፤ በተጨማሪም ጉዳቱ የከፋ ባይሆንም በሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት ወረዳ በቅርቡ የአንበጣ መንጋው መከሰቱንም ያብራራሉ።

በእነዚህ አካባቢዎች ከ151 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ አሰሳ ተደርጎ በ78 ሺህ 800 ሄክታር ላይ የአንበጣ መንጋው መከሰቱ መረጋገጡን ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገልፀዋል።

የአንበጣ መንጋውን ለመከላከልም በሰው ኃይል እና በአውሮፕላን በመታገዝ ቢያንስ ከ51 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነውን መሬት ማጽዳት ተችሏል ብለዋል።

ነገር ግን አሁን አንበጣው መብረር ስለጀመረ ከእስካሁኑ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ይገመታል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

እንድ ምክትል ኃላፊው ከሆነ ችግሩን ለመቅረፍ ኅብረተሰቡን በማሳተፍ እና በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት በማካሄድ እየተሠራ ነው።

በአንዳንድ ቦታዎች ያለውን የአንበጣ መንጋ በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት ካልሆነ መቆጣጠር የማይቻል ነው ሲሉ የችግሩን ጥልቀት ያስረዳሉ።

የመከላከል ሥራው ካልተጠናከረ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በንፋስ ኃይል እየተገፋ ሊሠፋ ይችላል ያሉት አቶ ተስፋሁን ለዚህም እየተሠራ ነው ነው ብለዋል።

ከወራት በፊት ጀምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በመከሰት በእጸዋት ላይ ጉዳት እያደረሰ ያለው የአንበጣ መንጋ፤ በአሁኑ ጊዜ በሰሜና፣ በሰሜን ምሥራቅና በመካከለኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው።

በአንበጣ መንጋው ሳቢያ በሰብል ላይ በደረሰ ጉዳት በብዙ ቦታዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ለችግር ሊጋለጡ እንደሚችሉ እየተነገረ ነው።