ኮሮናቫይረስ፡ በአፍሪካ በኮቪድ-19 የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ የሆነበት 5 ምክንያቶች

ጭምብል ያጠለቁ ኢትዮጵያውያን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በርካታ የአፍሪካ አገራት ምንም እንኳን ደካማ የጤና ሥርዓት ቢኖራቸውም የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት ባካሄዱት ዘመቻ ተወድሰዋል።

እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ መሰረት ከአንድ ቢሊዮን በላይ የሕዝብ ብዛት ባላት አህጉር አፍሪካ፤ እስካሁን በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር 1.5 ሚሊዮን ገደማ ነው። የሟቾቹ አጠቃላይ ቁጥር ደግሞ 37 ሺህ።

ይህም በአሜሪካ ከተመዘገበው 580 ሺህ ፣ በአውሮፓ 230 ሺህ እና በእስያ 205 ሺህ የሟቾች ቁጥር ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ነው። በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም በአፍሪካ እየቀነሰ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

በሽታውም ከሌሎች አህጉራት ጋር ሲታይ በአፍሪካ ያን ያህል የከፋ እንዳልሆነ የግልና የሕዝብ ድርጅቶችን መረጃ በማጠናቀር የተሰራ አህጉራዊ ጥናት አመልክቷል።

ይሁን እንጅ በአህጉሪቷ እየተደረገ ያለው ምርመራ አነስተኛ መሆኑ በሽታውን ለመቆጣጠር የሰጠችውን ምላሽ አጥልቶበታል። ቢሆንም ግን በአፍሪካ ሳይመዘገብ የቀረ የሞት ቁጥር መኖሩን የሚያመላክት መረጃ አለመኖሩን የአፍሪካ የበሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል ዳሬክተር ዶክተር ጆን ኬንጋሶንግ ተናግረዋል።

ታዲያ በአፍሪካ ከሌላው አህጉር በተለየ በበሽታው አነስተኛ የሞት ቁጥር የተመዘገበበት ምክንያት ምንድን ነው?

1: ፈጣን እርምጃ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

በሌጎስ የሚገኝ ቤተ ክርስቲያን

በአህጉሯ ለመጀመሪያ ጊዜ ቫይረሱ መገኘቱ የተረጋገጠው እአአ. የካቲት 14 በግብፅ ነበር። ወረርሽኙ ደካማ የጤና ሥርዓት ባላት አህጉር በስፋት እና በፍጥነት ይዛመታል የሚል ከፍተኛ ስጋትም ነበር።

በመሆኑም ከመጀመሪያው ጀምሮ በርካታ የአፍሪካ መንግሥታት የቫይረሱን ሥርጭት ለመቆጣጠር አፋጣን እርምጃ ወሰዱ።

በእጅ የመጨባበጥ ሰላምታን ማስቀረት፣ በተደጋጋሚ እጅን መታጠብ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግን ወዲያው ነበር ያስተዋወቁት።

እንደ ሌሴቶ ያሉ አንዳንድ አገራትም በአገራቸው ቫይረሱ መግባቱ ሳይረጋገጥ ነበር እርምጃ መውሰድ የጀመሩት።

ሌሴቶ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ መጋቢት ወር ላይ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ አድርጋለች። ከዚያም ለሦስት ሳምንታት የዘለቀ የእንቅስቃሴ ገደብ ጣለች። በተመሳሳይ ሌሎች የደቡባዊ አፍሪካ አገራትም ይህንኑ ተገበሩ።

ይሁን እንጅ በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ የእንቅስቃሴ ገደቡ ከተነሳ ከቀናት በኋላ ሌሴቶ የመጀመሪያውን በቫይረሱ የተያዘ ሰው አገኘች።

ከ2 ሚሊዮን በላይ የሕዝብ ብዛት ያላት ሌሴቶ እስካሁን 1 ሺህ 700 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን የመዘገበች ሲሆን፤ የ40 ሰዎች ሕይወትም በቫይረሱ ሳቢያ አልፎባታል።

2: የሕዝብ ድጋፍ

ፒኢአርሲ የተባለ ድርጅት ነሐሴ ወር ላይ በ18 አፍሪካ አገራት ላይ በሰራው የዳሰሳ ጥናት፤ ለጥንቃቄ መመሪያዎቹ የነበረው የሕዝብ ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበር 85 በመቶ የጥናቱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

የጥናቱ ተሳታፊዎች ቀደም ብለው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ያደርጉ እንደነበር አክለዋል።

ሪፖርቱ " የሕብረተሰብ ጤና እና ማህበራዊ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመተግበር የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት ከመጋቢት እስከ ግንቦት ድረስ የቫይረሱን ስርጭት መቆጣጠር ችለው ነበር " ብሏል።

ይሁን እንጅ ሰኔ ወር ላይ የተጣሉት ገደቦች እየላሉ በመምጣታቸው፤ ሐምሌ ወር ላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ጭማሬ እንዳሳየ ሪፖርቱ ጨምሮ ገልጿል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ወዲህ ግን ግማሽ በሚሆነው የአህጉሪቱ ክፍል በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች እና በበሽታው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል።

ይህም ምን አልባት በደቡብ ንፍቀ ክበብ ካለው የክረምት የአየር ጠባይ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ተነግሯል።

በአገራቱ በሽታውን ለመቆጣጠር የተጣሉ ገደቦችም ዋጋ ሳያስከፍሉ አልቀሩም ታዲያ። በኢኮኖሚው ፣ በማህበራዊው፣ በፖለቲካዊ ዘርፉ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል። በርካታ የሥራ እድሎችም ታጥፈዋል።

በዓለማችን ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ከጣሉ አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ በዓመቱ የመጀመሪያው አጋማሽ 2.2 ሚሊዮን ሠራተኞች ሥራ አጥተዋል።

በዚህም ምክንያት ምንም እንኳ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ቢጨምርም በርካታ አገራት ኢኮኖሚያቸውን እንደገና ለመክፈት ተገደዋል።

እንደ ፒኢአርሲ ሪፖርት ከሆነ፤ ኢኮኖሚው እንደገና ለመከፈቱ የተሰጠው የሕዝብ አስተያየት የተቀላቀለ ነው።

አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ የበሽታውን ሥርጭት መቀነስ የሚቻል በመሆኑ እንቅስቃሴው መከፈት አለበት ያሉ ቢኖሩም፤ ሌሎች ደግሞ ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴ መመለሱ ያዘናጋል ብለዋል።

መረጃው እንደሚያመለክተው በአፍሪካ ያሉ ሕዝቦች ኮቪድ-19 አደገኛ በሽታ እንደሆነ ቢመለከቱትም፤ በርካቶች ግን ለራሳቸው ከሚያደርጉት ጥንቃቄ በላይ የኢኮኖሚውና ማህበራዊ ጫናው አይሎባቸዋል። ይህም ለበሽታው እንዲጋለጡ አድርጓቸዋል ሲል ሪፖርቱ ድምዳሜውን አስቀምጧል።

3: ወጣት የሕዝብ ብዛት እና አነስተኛ የአረጋውያን የእንክብካቤ ማዕከላት

በአፍሪካ አብዛኛው ሕዝብ ወጣት በመሆኑ በሽታውን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በበሽታው የሞቱት አብዛኞቹ ከ80 ዓመት በላይ ያሉ ናቸው። እንደ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ከሆነ አፍሪካ በአማካይ 19 ዓመት እድሜ ያላቸው የዓለማችን ከፍተኛ የወጣቶች ቁጥር የሚገኝባት አህጉር ናት።

እንደ የዓለም ጤና ድርጅት ከሆነ በሽታው በአብዛኛው በወጣቶቹ ውስጥ ነው ያለው፤ ነገር ግን ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት 91 በመቶ የሚሆኑት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከ60 ዓመት በታች ናቸው፤ ከ80 ዓመት በላይ የሆኑትም ምልክት የማያሳዩ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

በናይሮቢ ህፃናት እጃቸውን ሲታጠቡ

"በአፍሪካ ደግሞ ከ65 ዓመት በላይ የሆነው ሕዝብ 3 በመቶ ብቻ ነው። በአውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካ እና ሃብታም የእስያ አገራት ግን በእድሜ የገፋ ሕዝብ ነው ያላቸው።" ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳሬክተር ዶክተር ማሺዲሶ ሞቲ ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም በምዕራብ አገራት አረጋውያን የሚኖሩት በእንክብካቤ ማዕከላት መሆኑን በመጥቀስ እነዚህም የበሽታው ሥርጭት ጠንከር ያለባቸው ቦታዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በአፍሪካ አገራት አብዛኞቹ በእድሜ የገፉ ሰዎች በሚኖሩባቸው የገጠር አካባቢዎች እንደዚህ ዓይነት ማቆያዎች የተለመዱ አይደሉም።

በአብዛኞቹ የአፍሪካ አገራትም ሰዎች በከተማ ሲሰሩ ቆይተው ጡረታ ሲወጡ ወደ ገጠር የመሄድ ልማድ አለ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ይህ ደግሞ በገጠር አካባቢም ያለው የሕዝብ ብዛት አነስተኛ በመሆኑ አካላዊ ርቀትን ለመጠበቅ ቀላል ነው።

ከዚህም በተጨማሪ በአገር ውስጥም ሆነ በአገራቱ መካከል ባለው ያልዳበረው የትራንስፖርት ሥርዓት ከበሽታው መሸሸጊያ ምክንያት ሆኗል። አፍሪካዊያን ባደጉ አገራት እንዳሉ ሕዝቦች ጉዞ አያደርጉም።

ይህም ከሰዎች ጋር ያላቸውን ንክኪ እንዲቀንስ አድርጎታል።

4: ምቹ የአየር ንብረት

በአሜሪካ የሜሪላንድ ዩንቨርሲቲ አጥኝዎች የሙቀት መጠን፣ የወበቅ እና ኬክሮስ [ከምድር ወገብ በላይና በታች ያለው ርቀት]እና በኮሮናቫይረስ ሥርጭትን በተመለከተ አንድ ጥናት አካሂዷል።

የጥናቱ ቡድን መሪ ሞሃመድ ሳጃዲ "በመጀመሪያ በዓለማችን 50 ከተሞች ያለውን የቫይረሱን ሥርጭት ተመለከትን። ቫይረሱ ዝቅተኛ የሙቀት መጠንና ወበቅ ውስጥ ለመሰራጨት ጊዜ አልወሰደበትም" ሲሉ ተናግረዋል።

"ይህ ማለት ግን በሌላ አየር ጠባይ ውስጥ ቫይረሱ አይሰራጭም ማለት አይደለም" ያሉት አጥኝው፤ የሙቀት እና ወበቅ መጠን ሲቀንስ ግን ቫይረሱ በተሻለ የመሰራጨት እድል አለው ብለዋል።

በመሆኑም ከትሮፒካል [ከምድር ወገብ አካባቢ ርቀው የሚገኙ] የአፍሪካ አገራት ከሌሎቹ የባሰ ችግር ገጥሟቸዋል።

5: ጥሩ የማህበረሰብ ጤና ሥርዓት

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተከሰተው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኢቦላ ወረርሽኝን ለመዋጋት እየታገለች ባለበት ወቅት ነበር።

ጎረቤት አገራትም በተጠንቀቅ ላይ ነበሩ። በመሆኑም ለተጓዦች የሚደረግ የኢቦላ ምርመራ የኮቪድ-19 ምርመራን እንዲያካትት ተደርጓል።

አስከፊውን የኢቦላ ወረርሽኝ እአአ ከ2013-2016 ሲታገሉ የቆዩት በርካታ የምዕራብ አፍሪካ አገራትም በሕብረተሰብ ጤና እርምጃዎች ላይ ጥሩ ልምድ አካብተው ነበር።

ታማሚዎችን ለይቶ ማቆያ ማስገባትን፣ ንክኪ ያላቸውን ሰዎች መለየትን፣ እነርሱን መፈለግና መርምሮ ለይቶ ማቆያ ማስገባትን ጨምሮ የሚወሰዱ ሌሎች እርምጃዎች ኮቪድ-19ንም ለመከላከል ተጠቅመውበታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

በናይጄሪያ የፖሊዮ ክትባት

ከዚህም በተጨማሪ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ያላት አፍሪካዊቷ አገር ናይጀሪያ፤ የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ለመስጠት በየመንደሩ የሚሄደውን የጤና ቡድን፤ ስለ አዲሱ ወረርሽኝ [ኮቪድ-19] ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር በአፋጣኝ እንዲሰማራ አድርጋለች።

ይህ በፖሊዮ መከላከል ፕሮግራም ላይ ይሰሩ የነበሩት ዶክተር ሮስመሪ ኦንይቤ ሚያዚያ ላይ ያቀረቡት ሃሳብ ነበር።

ዶክተር ሮስመሪ " ዜናውን እንደሰማሁ ሕብረተሰቤን ለመጠበቅ የእኔ ሙያ እና እርዳታ እንደሚያስፈልግ አሰብኩ። በመሆኑም ፖሊዮ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎችን በማንቀሳቀስ ንክኪ ያላቸውን ሰዎች እንዲለዩ እና እንዲከታተሉ አደረግን" ብለዋል።

ከሌሎች ዓለማት ጋር ሲነፃፀር በአብዛኛው የአፍሪካ አገራት ሆስፒታሎች መሰረተ ልማት ያልተሟላና ያልዘመነ ነው። የአህጉሪቷ ጥንካሬም በተፈተነው የሕብረተሰብ ጤና ሥርዓት ውስጥ ይገኛል።

ይህ ማለት ግን የአፍሪካ ሕዝብ መዘናጋት አለበት ማለት አይደለም።

የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳሬክተር ዶክተር ሞቲ " በቀጠናው ያለው የቫይረሱ ስርጭት አዝጋሚ ነው ማለት ወረርሽኙ ለተወሰነ ጊዜ ይቆያል ማለት ነው። ሥርጭቱ ሊጨምር እንደሚችልም ይጠበቃል" በማለት አሳስበዋል።