ትግራይ ፡ የትግራይ ክልል መንገዶች በአሽከርካሪዎች አንደበት

ሑመራ
የምስሉ መግለጫ,

የሁመራ ከተማ

በፌደራልና በትግራይ ክልል መንግሥት መካከል የነበረው ፍጥጫ ባለፈው ሳምንት ፈንድቶ ወደ ወታደራዊ ግጭት ከተሸጋገረ ሳምንት ሆነ።

ይህንንም ተከትሎ በክልሉ የስልክም ሆነ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ አካባቢው በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ለማወቅ እጅግ አስቸጋሪ ሆኗል።

በመቀሌ የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ በዛሬው ዕለት በመቀሌ አውቶቡስ ተራ ተገኝቶ ከሰቲት ሁመራ፣ ሽራሮ፣ ሽረ፣ አክሱም፣ አድዋ እና አብዪ ዓዲን አልፈው መቀለ የገቡ አሽከርካሪዎች ያጋጠማቸውንና የተመለከቱትን እንዲነግሩት ጠይቋቸዋል።

በአውቶብስ መናኸሪያው የሚሰሩ ወጣቶች ሽረ-ሁመራ፤ ዓድዋ-አክሱም፣ ዓብዪ ዓዲ - ተከዜ፣ ዓዲግራት-ሐውዜን እና ሌሎች መስመሮችን እየጠሩ ተጓዦችን ሲያሳፍሩ መመልከቱን ገልጿቷል።

ቢቢሲ ያገኘው ወጣት ፍታለ ሙላው ከሁመራ ተነስቶ ወደ መቀሌ የገባው በትናንትናው ዕለት፣ ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም ነው።

''ከሁመራ ተነስቼ በሽራሮ በኩል ሽረ ገባሁ። መንገዱ ሰላም ነው ያለው። አድዋ እና አክሱም አልፌ በዓብዪ ዓዲ በኩል መቀሌ እስክደርስም ሰላም ነው'' በማለት ያለው ሁኔታ ይገልጻል።

ፍታለ ሙላው ተሳፋሪዎችን ጭኖ መቀለ ላጪ ከሚገኝ አውቶቡስ ተራ ወደሚኖርባት የሁመራ ከተማ በዛሬው ዕለት ህዳር 01/2013 ዓ.ም ጥዋት መጓዙን ዘጋቢያችን አመልክቷል።

አሽከርካሪ ጸጋይ በርሀ በበኩሉ ከአክሱም ተሳፋሪዎች ጭኖ መቀለ የገባው በትናንትናው ዕለት ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም ነው።

በዛሬው ዕለትም ጥዋት ደግሞ ወደ አክሱም የሚመለሱ ተሳፋሪዎችን እየጫነ ነበር።

የምስሉ መግለጫ,

የሁመራ ከተማ

ከአክሱም በተምቤን በኩል ወደ መቀሌ እንደመጣ የሚናገረው ጸጋይ "መንገዱ ሰላም ጥሩ ነው'' ብሏል።

በተመሳሳይ ከሽሬ እንዳ ሥላሴ ተነስቶ ትናንት አመሻሽ መቀለ የደረሰው ሌላኛው አሽከርካሪ ካህሱ አጽብሃ መንገዱ ሰላም እንደነበርና ያጋጠመው ችግር እንዳልነበር አመልክቷል።

ካህሱ እንደሚናገረው በሁመራ እና ሽሬ የሚገኙ ነዋሪዎች መቀለ የአየር ጥቃት ተፈፀመ ስለተባሉ እየተጨነቁ መሆናቸውንና በመቀለም በኩል የተለያዩ የትግራይ ክፍሎች ላይ አየር ጥቃት ደርሷል መባሉ ስጋት ሆናባቸዋል።

በመቀለ፣ አዲግራት፣ ፈላፍል፣ መቀለ እና አላማጣ የአውሮፕላን ድብደባዎች እንዳሉ ቢነገርም ሕዝቡ ግን የተለመደውን የእለት ጉዳዩን እየፈፀመ መሆኑን አሽከርካሪዎቹ ይናገራሉ።

በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት በክልሉ የነዳጅ እጥረት በማጋጠሙ በመጓጓዣ አገልግሎት ላይ ትልቅ ተጽእኖ እንደፈጠረ ጠቅሰው፤ ችግሩ ባለበት ከቀጠለ ደግሞ በመጓጓዣ ዋጋ ጭማሪ ሊኖር እንደሚችል መንገደኞች እና አሽከርካሪዎች ለቢቢሲ ዘጋቢ ገልፀዋል።

ከዚህ ቀደም 21 ብር ከ57 ሳንቲም የነበረው የአንድ ሊትር ቤንዚን ዋጋ በጥቁር ገበያ በ200 ብር እየተሸጠ ነው።

13 ብር የነበረ የናፍጣ ዋጋም 60 ብር መድረሱ ተገልጿል።

የትግራይ ልዩ ኃይል በአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት የሠሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ካሳወቁና ሠራዊቱ እርምጃ እንዲወስድ ካዘዙ በኋላ በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።

የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊቱን ወደ ተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች አሰማርቶ እርምጃ እየወሰደ በርካታ አካባቢዎችን እየተቆጣጠረ መሆኑ ከመንግሥት በኩል የተነገረ ሲሆን፤ በተመረጡ ኢላማዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሙ ተነግሯል።

ከግጭቱ በኋላ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ ቢነገርም ነዳጅን ጨምሮ ተለያዩ የመሠረታዊ አቅርቦቶች እጥረት እየተከሰተ መሆኑም ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች አመልክተዋል።