ጃፓኖች ትዳርን እንደተውት አብሮ መብላትንም እርግፍ አርገው እየተውት ይሆን?።

ብቻዋን ምግብ ቤት ያለች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Shiho Fukada and Keith Bedford

የፈረንጆቹን አዲስ ዓመት እየጀመርን ነው ጊዜ ይለወጣል። ጊዜ የማይለውጠው ምን አለ? ጃፓኖችም ቢሆን።

ለምሳሌ የዛሬ 10 እና 20 ዓመት አንዲት ሴት ጃፓናዊት ብቻዋን ምግብ ቤት ገብታ፣ መዘርዝረ ምግብ ቃኝታ፣ ምግብ ጥርግርግ አድርጋ በልታ ብትወጣ አገር ጉድ ነበር የሚባለው።

አንዲት የጃፓን ሴት ካፌ ገብታ በርገር ስትገምጥ ብትታይ ተስተናጋጆች ለእሷ ይሸማቀቁ ነበር።

ምን ይህ ብቻ፣ ቢሮ በምሳ ዕቃ ምግብ አምጥቶ ለብቻ መብላት እንኳ ያሳፍር ነበር።

ከዚህ ሀፍረት ለመዳን አማራጩ ሁለት ነበር። ወይ ከሰው ጋር ተጠግቶ አብሮ መብላት፣ ወይ ሆድን እያከኩ መዋል።

ይቅርታ ሦስተኛ አማራጭ አለ። ዘንግቼው ነው።

መታጠቢያ ቤት ገብቶ በር ቆልፎ ጥርግርግ አድርጎ መብላት. . .።

ይህ በጃፓን በጣም የተለመደ ተግባር ነበር። እዚያ ይህ ተግባር እጅግ የተለመደ ከመሆኑ የተነሳ የራሱ መጠሪያ ስም አለው። "ቤንጆ ሜሺ" ይባላል። የመታጠቢያ ቤት ምሣ ማለት ነው።

ዛሬ ጃፓን ያን ዘመን እየረሳችው ነው። ብቸኝነት ነውር መሆኑ እያበቃለት ነው።

ስለዚህ ጉዳይ በደንብ የምታጫውተነን ሚኪ ታተይሽን ተዋወቋት።

በቶክዮ አንድ ቡና ቤት ውስጥ አስተናጋጅ ናት። ቡና ቤቱ 'ሂቶሪ' ይባላል። በቶክዮ ታዋቂ ቡና ቤት ነው። ሰዎች እዚህ ቡና ቤት የሚመጡት ታዲያ ለብቻቸው ነው።

ሴቶች 'ባለጌ ወንበር' ላይ ፊጥ ብለው፣ ያሻቸውን ኮክቴይል መጠጥ አዝዘው፣ ደንቅ የግል ጊዜን አሳልፈው እየተንገዳገዱ ቤታቸው መግባት ይችላሉ። ይህ የዛሬ 10 ዓመት በጃፓን የሚሞከር አልነበረም። እረ በጭራሽ!

ይህ 'የብቸኞች' ቡና ቤት የተከፈተው በ2018 ነበር። እንዴት ሊከፈት ቻለ? ምክንያቱም የጃፓን የሕይወት ዘይቤና ባሕል ቀስ በቀስ እየተቀየረ ስለመጣ።

ላጤ ጃፓናዊያን እና ፈት ጃፓናዊያን ቁጥራቸው እየተምዘገዘገ ነው፤ ሽቅብ!

ስለዚህ ብቻቸውን እንደሚኖሩት ሁሉ ብቻቸውን ሽር ብትን ማለትን ይፈልጋሉ። የብቸኝነት ኑሮ ተበራክቷል፤ እዚያም እዚህም።

መታጠቢያ ቤት ቆልፎ ምሣ መብላት የቀረው ከዚህ በኋላ ነው።

አስተናጋጇ ታተይሺ ደንበኞቿ እየበዙ እንደሆነ በየምሽቱ ታስተውላለች።

"እዚህ የሚመጡት ብዙዎቹ ብቸኝነትን ፈልገው ነው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ከሌላ በቸኛ ሰው ጋር መዳበል ሽተው" ትላለች ታተይሺ።

በዚህ ቡና ቤት ግን ሰብሰብ ብሎ መምጣት አይቻልም። ክልክል ነው። የብቸኞች ቡና ቤት ነው።

ቡና ቤቱ አሰራሩ ራሱ ለቡድን አይመችም። አብሮነትን አያበረታታም። ጠበብ ያለና ባለ አንድ-አንድ ወንበር ነው።

የጃፓን ባሕል የደቦ ነው። የሚበላው በጋራ፣ የሚሰራው በጋራ፣ መዝናናት በጋራ…።

አሁን ግን ይህ ቶሎ ቶሎ እየተቀየረ ነው።

በጃፓን አዲሱ ብቸኝነት 'ሂቶሪ' ተብሎ ይጠራል። 'አንድዬ' እንደማለት ነው። ቡና ቤቱም ስሙን የወሰደው ከዚሁ ነው።

ይህን የብቸኝነት፣ ነጠል የማለት አዲስ ባሕል የተረዱ ቢዝነሶች እየጎመሩ ነው።

የጉዞ ወኪሎች በፊት ለአንድ ሰው የሚሆን ፓኬጅ አልነበራቸውም። አሁን አሁን የነጠላ ተጓዦች በዝተዋል። ምግብ ቤቶች ለአንድ ሰው ጠረጴዛና ወንበር አልነበራቸውም። አሁን እየበዙ ነው። ካፌዎችም እንደዚያው፣ መዝናኛዎችም እንደዚያው።

ይህ በእጅጉ ብቸኝነትን የመውደድ አባዜ ጃፓኖቹ 'ኦሂቶሪዛማ' ብለው እየጠሩት ነው። አሁን ማኅበረሰባዊ እንቅስቃሴ እየሆነ ነው። ጽንሰ ሐሳቡ ሰዎች ብቸኝነትን እንዲወዱ ማድረግ ነው።

ሐሳቡ በደቦ ባሕል የተቆላለፈውን የጃፓን አኗኗር መበጣጠስ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Shiho Fukada and Keith Bedford

የነጠላ ጉልበት

ኦሂቶሪሳማ በደምሳሳው ሲተረጎም 'የላጤ ድግስ' እንደማለት ነው። የላጤ ፌሽታ። ላጤነት ከትዳር ገሸሽ ማለት ብቻ አይደለም። በሁሉም የአኗኗር ዘይቤ ነገሮችን ለብቻ ማድረግንም ያካትታል።

ለምሳሌ በኢንስታግራም ይህንን የጃፓን ቃል አስገብታችሁ ኢንተርኔቱን ብታስሱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፎቶዎችን ታገኛላችሁ።

ሁሉም የብቸኛ የሕይወት ዘይቤን የሚያንቆለጳጵሱ ናቸው።

ባለፉት ሁለት ዓመታት የጃንፓ ኢንተርኔት መድረኮች ይህንን የብቸኛ ሕይወትን ውበት በሚያሞግሱ መረጃዎች ታጭቀዋል።

ጃፓኖች እየተቀየሩ ይሆን?

ለምሳሌ መስክ ላይ የሚጠበስ ሥጋ አብስሎ በጋራ መብላት አዲስ ፋሽን ሆኗል፤ በጃፓን። 'ሒቶሪ ያኪኒኩ' ይሉታል።

ያኪኒኩ እንደኛ ጥሬ ሥጋ ሰብሰብ ብሎ ከመብላት ጋር ይመሳሰላል። እነሱ ሥጋውን ቢጠብሱትም።

የሚገርመው ታዲያ ይህ የመሥክ ላይ ሥጋን በደቦ አርዶ፣ በቅርጫ መልክ ተካፍሎ ጠብሶ በጋራ የመብላቱ ባሕል በአዲስ እየተቀረ መምጣቱ ነው።

አሁን በርካታ ጃፓናዊያን ይህን ለብቻቸው እያደረጉት ነው። አንድ ሰው ለብቻው መስክ ሄዶ፣ ክምር ሙዳ ሥጋ ብረት ምጣድ ላይ ጠብሶ፣ ተመግቦ፣ ተምነሽንሾ ይመጣል።

ይሄ ሴቶችንም ይጨምራል። ይህ ለጃፓን ባሕል ባዕድ ነው። ሆኖም አሁን እየለመደ መጥቷል።

ካሪዮኪን ለብቻ

ምን ይህ ብቻ፣ ካራዮኪ የሚሉት የጃፓን መዝናኛ አለ። ይህ በሩቅ ምሥራቅ አገሮች በጣም የሚዘወተር ነው። ቡና ቤቶች፣ ላውንጆች፣ ምሽት ክበቦች ካራዮኪ ከሌላቸው ምኑን መዝናኛ ሆኑ?

ካሪዮኪ በመሰረቱ በሞቅታ ውስጥ ዘፋኝ መሆን ማለት ነው። የሚዝናኑ ሰዎች መድረክ ላይ ወጥተው፣ ማይክራፎን ጨብጠው ከተቀናበረ ሙዚቃ ውስጥ፣ ከሚወዱት ዘፋኝ፣ የወደዱትን ዜማ ወስደው መዝፈን።

'ሩቅ ምሥራቅ ሳለሁ፣ ጃፓኗን ወድጄ' የሚለውን የጥላሁን ገሠሠ ዜማን እየተጫወተ ከሙዚቃው የጥላሁን ድምጽ ይወጣና የሚዝናናው ሰው ድምጽ ይገባል። ይህ ነው ካሪዮኪ።

ካሪዮኪ ሲታሰብ ታዲያ በደቡ የሚሆን ነገር ነው። በርካታ ወዳጆች በየተራ መድረክ እየወጡ የሚወዱትን ዜማ ማንጎራጎር። አሁን ግን ጃፓኖች ለብቻቸው ካሪዮኪ አስከፍተው መዝፈን ጀምረዋል። ቡና ቤቶች ውስጥ የካሪዮኬ ስቱዲዮዎች አሉ፤ የስልክ ማነጋገርያ ክፍሎች የመሰሉ። በቃ ብቸኛው ሰው እዚያች ክፍል ገብቶ ለብቻውን አንጎራጉሮ ሲወጣለት ይወጣል።

ጃፓን፣ አብሮ መብላትን ትታ፣ አብሮ መጠጣትን ትታ፣ አብሮ መደነስን ትታ፣ ትዳርን ትታ አሁን ምን ቀራት? ምናልባት አብሮ መሥራት?

እርግጥ ነው በብዙ አገሮች ብቸኝነት እየተስፋፋ ነው። በምዕራቡ ዓለም ነጠል ብሎ መኖር የተለመደ ነገር ነው። አስገራሚም አይሆንም። በቤተሰብ ሕይወትና በአብሮነት አኗኗር የሚታወቁት ጃፓኖች ብቸኝነት እየወደዱ መምጣታቸው ነው አስገራሚው።

የፎቶው ባለመብት, Shiho Fukada and Keith Bedford

125 ሚሊዮን የደረሰው የጃፓን ሕዝብ እንደ ፍንጭት ጥርስ ዝርዝር ብለው በተፈጠሩ በርከት ባሉ ትንንሽ ደሴቶች ተጠጋግቶ ነው የሚኖረው።

"ጃፓን ትንሽዬ አገር ናት፤ ሰዎች ባይፈልጉም ይቀራረባሉ፤ ተጠጋግተው ነው የሚኖሩት" ይላሉ ሞቶኮ ማቱሺታ።

ማቱሺታ በምጣኔ ሀብት የምርምር ማዕከል ውስጥ ተመራማሪ ናቸው።

ኦሒቶሪሳማ ላይ ምርምር አድርገዋል። ይህ ብቸኝነትን እየሻቱ የመምጣቱ ነገር ጃፓን ብቻ ሳይሆን ቀሪው ዓለምም ወደዚያው እያቀና ነው ይላሉ።

ማቱሺታ እንደሚሉት ለዚህ አዲስ ባሕል መፈጠር የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ምክንያት ናቸው። እንዴት ለሚለው እንዲህ ያብራራሉ።

"አሁን አሁን ዋጋ የምንሰጣቸው ነገሮች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ብዙ መወደድ (ላይክ) የሚያስገኙ ነገሮችን ነው። ብዙ የጃፓን ሴቶች ራሳቸውን በማኅበራዊ ገጽ ላይ ማውጣት ጀመሩ። ሕይወታቸውን አደባባይ አሰጡት። ብዙ ሰዎች ተከተሏቸው እንጂ አላሸማቀቋቸውም።"

ስለዚህ ብቻ መኖርን የኅብረተሰቡን ሳይሆን የራስን የሕይወት አኗኗር ዘይቤ መከተል ችግር ሲፈጥር አልታየም። እንዲያውም ተወዳጅና ዝነኛ መሆን ጀመረ። ወጣቶች ይህን እያዩ በድፍረት ወደ ምግብ ቤት፣ መዝናኛ፣ እየሄዱ ዓለማቸውን መቅጨት ጀመሩ።

ቀደም ብሎ ሴት ጃፓናዊ ተማሪዎች ትምህርት ቤት ውስጥ እንኳ ምሳቸውን ተደብቀው ይበሉ የነበረው ወደው አልነበረም። ጓደኛ አልባ መሆን አሳፋሪ ስለነበረ ነው። አለመወደድን፣ መገፋትን፣ ቆንጆ አለመሆንን ያመላክት ነበር። አሁን ያ ስሜት ጠፋ።

ይህ ብቻ አይደለም፤ ሴቶች ማግባት አለባቸው፤ መውለድ አለባቸው የሚለው ጠንካራ ማኅበራዊ አስተሳሰብ በፍጥነት እየተሸረሸረ ነው።

10 ሺህ ጃፓናዊያን ላይ በተደረገ ጥናት ብዙዎቹ ብቻ መኖር የተሻለ ነው ብለው እንዳመኑ አሳይቷል። ብዙዎቹ ከትዳር መፋታት የነጻነት መቀዳጀት እንደሆነ እንደሚያስቡ አመላክቷል።

ጃፓን የአዛውንቶች አገር ናት። የወሊድ መጠን አሽቆልቁሎ መሬት ሊነካ ምን ቀረው። ባለፈው ዓመት በጃፓን የተወለዱ ልጆች ብዛት 864ሺህ ብቻ ነበር። ከ1899 (እአአ) ጀምሮ ጃፓን የወሊድ ቁጥር መመዝገብ ጀምራለች። በመቶ ዓመት የታየ አነስተኛ የወሊድ ቁጥር ነው ይህ አሀዝ።

ሌላው የላጤ ቁጥር መመንደግ ነው። ከ2015 ወዲህ የላጤዎች ቁጥር ከ25 በመቶ ወደ 35 በመቶ ተመንድጓል።

በትዳር ያልተጣመረው ሕዝብ ቁጥር መጨመር የመጣው ካለማግባት ብቻ ሳይሆን አግብቶ መፍታት በጣም እየተለመደ በመምጣቱም ጭምር ነው።

ካዙሒሳ አራካዋ በዚህ ጉዳይ ተመራማሪ ነው። መጽሐፍም ጽፏል። እሱ በሰራው ጥናት 50 ከመቶ የሚሆነው ጃፓናዊ በ2040 ብቻውን ይኖራል። የጃፓን ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሔዋን የደረሰ ግማሽ በግማሽ ሕዝብ ላጤ ሆኖ ይቀራል።

በብዙ አገራትም ይኸው ነው እየሆነ ያለው።

ሰዎች የሕይወትን ጥያቄ ለመጠየቅ ብቻቸውን መሆንን ይመርጣሉ። ሕይወት የከበዳቸው ሰዎች ወደዚህ ከባድ ዓለም ሌላ ፍጡር መጋበዝ አይፈልጉም። ራሳቸው ላይ የልጅ ጫና ማምጣትን አይሹም።

ብዙ ነገር አይበቃም። ጊዜ አይበቃም። ሌላ ሰውን ባሕሪ መሸከም ማባበል ይሰለቻል። ማኅበራዊ ሕይወት ደስ የሚሉ ብዙ ትሩፋቶች ቢኖሩትም አዲሱ ትውልድ ግን ለእነሱ ጊዜም ታጋሽነትም እያጣ ይመስላል።

ዓለማችን በሚቀጥሉት 50 ዓመታት የላጤዎች ወይም የፈቶች ዓለም ትሆናለች ይላል ካዙሒሳ አራካዋ።

ጃፓን ግን ይህን መንገድ ቀድማ የተያያዘችው ይመስላል። በ10 ዓመቱ ውስጥ ከደቦ ወዳድ ማኅበረሰብነት ወደ ላጤና ነጠላነት የተጓዘችበት ፍጥነት እንደ ባቡሮቿ ነው።