ጣሊያን ፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተከሰሱበት የማፊያ ቡድን አባላት የፍርድ ሂደት በጣሊያን ተጀመረ

ታዋቂው ፀረ ማፍያ ዐቃቤ ሕግ ግራቴሪ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

ታዋቂው ፀረ ማፍያ ዐቃቤ ሕግ ግራቴሪ

በመቶዎች የሚቆጠሩ የጣልያኑ ኃያል የማፊያ ቡድን አባላት ናቸው የተባሉ ግለሰቦች በተደራጀ የወንጀል ክስ በአስርት ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ለፍርድ ሊቀርቡ ነው።

ንድራንጌታ በተባለው የማፊያ ቡድን ላይ ረዘም ላለ ጊዜ ከተደረገ ምርመራ በኋላ 355 ተጠርጣሪ የውንብድና ቡድን አባላትና ሙሰኛ ባለሥልጣናት ላይ ክስ ተመሰርቶባቸውል።

ከ900 በላይ ምስክሮች እማኝነታቸውን ይሰጣሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የክስ መዝገቡ ግድያን፣ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን፣ ምዝበራና ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ያካትታል ተብሏል።

ክሱን የሚመለከተው ችሎት ረቡዕ የተጀመረ ሲሆን ከሁለት ዓመት በላይ ሊቆይ እንደሚችል ተነግሯል።

ችሎቱ በደቡባዊ የጣሊያን ክፍል ካላብሪያ ውስጥ በምትገኘውና 'የንድራንጌታ ግዛት' እምብርት በሚባለው ሰፍራ ለዚሁ ችሎት ተብሎ በተዘጋጀ ሕንፃ ውስጥ እየተካሄደ ነው።

ሕንፃው ቀደም ሲል በላሜዚያ ተርሜ ከተማ የጥሪ ማዕከል ሆኖ ያገለገለ ሲሆን የፍርድ ሂደቱን ለሚከታተሉ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ክፍት ቦታ እንዲኖር ለማስቻልና ለጥብቅ ጥበቃ እንዲያመች ተደርጎ ማሻሻያ ተደርጎበታል።

ከአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ ወዲህ በጣሊያን ውስጥ ከማፊያ ቡድን ጋር በተያያዘ እንደዚህ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ተከሳሾች ላይ የክስ ሂደት አልተከናወነም።

ተከሳሾቹ እነማን ናቸው?

ከ1986 እስከ 1992 (እአአ) በተካሄደውና በሲሲሊ ውስጥ በርካታ የተደራጁ የወንጀል ቤተሰቦች ላይ ካነጣጠረው የፍርድ ሂደት በተለየ መልኩ የረቡዕ ዕለቱ ችሎት ትኩረቱን ያደረገው 'የንድራንጌታ' ማፊያ ኃያል ክፍል በሆነው የማንኩሶ ቤተሰብ ላይ ብቻ ነው።

'ንድራንጌታ' በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ በጣም ኃያል የማፊያ ቡድን ሲሆን ማኑኩሶ የተባለው የቡድኑ አካል በአብዛኛው በካላብሪያን ግዛት በቪቦ ቫሌንቲያ ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ ይነገራል።

በቅርቡ በተደረገው የቅድም ፍርድ ሂደት ላይ ተከሳሾችን ስም ብቻ ለማንበብ ከሦስት ሰዓታት በላይ እንደፈጀ ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል። ከእነዚህም መካከል ፖለቲከኞች፣ የፖሊስ መኮንኖች፣ የመንግሥት ሠራተኞች እና የውንብድና ቡድኑ ተባባሪዎች ይገኙበታል።

ቀንደኛው ተከሳሽ የ66 ዓመቱ የቡድኑ አለቃ ሉዊጂ ማንኩሶ ሲሆን "ዘ አንክል" [አጎትየው] ተብሎም ይጠራል። ሌሎች ተከሳሾች እንደ "ዘ ዎልፍ" [ተኩላው]፣ "ፋቲ" [ወፍራሙ] እና "ብሎንዲ" [ባለወርቃማ ፀጉር] በመሳሰሉ ቅጽል ስሞች ይጠራሉ ተብሏል።

ፈጣን የፍርድ ሂደትን የመረጡ 92 ተጠርጣሪዎች በሚጨመሩበት ጊዜ የተከሰሱ ሰዎች ቁጥር ከ400 በላይ ከፍ ይላል ተብሏል።

ከእነዚህ መካከል የቀድሞው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲልቪዮ ቤርሎስኮኒ ፓርቲ የሆነው 'ፎርዛ ኢታሊያ ፓርቲ' ጠበቃና የቀድሞው የምክር ቤት አባል የሆኑት ጂያንካርሎ ፒቴሊ ይገኙበታል።

ፒቴሊ 'ንድራንጌታ' ቡድንን ከፖለቲካው ዓለምና እንደ ፍርድ ቤቶች ካሉ ሌሎች ተቋማት ጋር አገናኝተዋል በመባል የሚቀርብባቸውን ክስ ያስተባብላሉ።

አብዛኞቹ ተከሳሾች በታኅሣስ 2019 ጣሊያን፣ ጀርመን፣ ስዊዘርላንድ እና ቡልጋሪያ ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋሉ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

ወደ ፍርድ ቤትነት የተቀየረው የጥሪ ማዕከል

ክሶቹ ምንድን ናቸው?

የ'ንድራንጌታ' ቡድን ከደቡብ አሜሪካ እና ከሌላም የዓለም አካባቢ ወደ አውሮፓ የሚገቡ የኮኬይን ዕፅ አቅርቦቶችን እንደሚቆጣጠር ይታመናል።

የክስ መዝገቡ ከማፊያ ቡድን ጋር መተባበርን፣ ግድያን፣ የግድያ ሙከራን፣ ብዝበዛን፣ አራጣ ማበደርን፣ ማጭበርበርን፣ የመንግሥት ምስጢሮችን ይፋ ማድረግ እና ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀምን ያካትታል።

በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የወንጀል ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ፌዴሪኮ ቫሬስ "ይህ የፍርድ ሂደት ንድራንጌታ በኅብረተሰቡ ውስጥ ምን ያህል ስር የሰደደ መሆኑን ያሳያል" ሲሉ ለኤኤፍፒ ገልጸዋል።

"በክልሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለፍርድ የሚያስቀርብ በጣም ሥር የሰደደ የወንጀል ቡድን መኖሩ በጣም የሚያስደነግጥ ነው" ሲሉም አክለዋል።

ጉዳዩን የያዙት ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በፖሊስ ጥበቃ እየተደረገላቸው የኖሩት በጣሊያን በጣም ታዋቂው የ62 ዓመቱ ፀረ ማፊያ ዐቃቤ ሕግ ኒኮላ ግራቴሪ ናቸው።

ዐቃቤ ሕጉ ሕዝቡ ላይ ከፍተኛ የፍርሃት ተጽእኖን መፍጠር የቻለውን ኃያሉን የማፊያ ቡድን 'ንድራንጌታን' ተጠያቂ ለማድረግ ቃል ገብቷል።

ፕሮፌሰር ቫሬስ በበኩላቸው ይህ የፍርድ ሂደት የቡድኑን መጨረሻ እንደማያመላክት አስጠንቅቀዋል። "እስር ቤት ሊገቡ ይችላሉ፤ ነገር ግን የተቋቋሙበትን ዋናዎቹ ምክንያቶች ካልተወገዱ እየተባዙ ይሄዳሉ" ብለዋል።