ኮቪድ-19፡ የኮሮናቫይረስን መነሻ የሚያጠናው የተመራማሪዎች ቡድን ውሃን ከተማ ገባ

የተመራማሪዎች ቡድኑ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የዓለም ጤና ድርጅት የተመራማሪዎች ቡድን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መነሻ ለማጥናት በቻይናዋ ከተማ ውሃን መግባቱ ተገለፀ።

ቡድኑ ሐሙስ ጠዋት ቻይና የገባው በዓለም ጤና ድርጅትና በቻይና መካከል ለወራት ድርድር ከተደረገ በኋላ ነው።

10 ተመራማሪዎችን የያዘው ቡድኑ እአአ በ2019 ለወረርሽኙ መነሻ ናቸው ከተባሉ የምርምር ተቋማት፣ ሆስፒታሎች እና የባህር ምግቦች የገበያ ቦታዎች ለሰዎች ቃለ መጠይቅ ከማድረጉ በፊት ተመራማሪዎቹ ለሁለት ሳምንት ራሳቸውን ለይተው ይቆያሉ ተብሏል።

ቻይና መጀመሪያ ላይ ቫይረሱ ሲከሰት ግልፅ ባለመሆኗ በተለይ በአሜሪካ ትችት ይቀርብባታል ።

ቻይና በበኩሏ ቫይረሱ የተነሳው ሌላ ቦታ ነው ስትል ትሞግታለች።

በዓለም ጤና ድርጅት ፕሮፌሰር የሆኑት ዳል ፊሸር፤ ዓለም ጉብኝቱ ሳይንሳዊ እንደሆነ ይረዳል ብለው እንደሚያስቡ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፕሮፌሰሩ ወደ ውሃን ማቅናታቸው "ለፖለቲካም ሆነ ለወቀሳ ሳይሆን ለሳይንሳዊ ጥያቄዎች ነው" ብለዋል።

ፕሮፌሰር ፊሸር እንደተናገሩት በርካታ ተመራማሪዎች ቫይረሱ 'ተፈጥሯዊ ክስተት' እንደሆነ ያምናሉ።

ከዚህ ቀደም የተመራማሪ ቡድኑ ቻይና እንዳይገባ መታገዱ የዓለም ጤና ድርጅት መግለፁ ይታወሳል።

በወቅቱ ሁለት የቡድኑ አባላት ጉዞ ጀምረው የነበረ ሲሆን የዓለም ጤና ድርጅትም ችግሩ ቪዛ አለማግኘታቸው እንደሆነ ገልጾ ነበር።

ሆኖም ቻይና የጉብኝቱን ቀን ጨምሮ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች እየተዘጋጁ መሆኑን በመግለፅ የቀረበባትን ወቀሳ አስተባብላለች።

የድርጅቱ ዳሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ሁለት የቡድኑ አባላት ጉዞ መጀመራቸውንና ሌሎቹ ደግሞ በመጨረሻ ሰዓት ጉዟቸው መደናቀፉን በመጥቀስ ቻይና ቡድኑ እንዲገባ አለመፍቀዷ እንዳሳዘናቸው መግለጻቸውም የሚታወስ ነው።