መመጣጠን ያልቻለው የንግድ ሚዛን ጉድለትና የናረው የውጭ ምንዛሪ

ብርና ዶላር

ኢትዮጵያ ሚሊኒየም (2000) ዓ.ምን ልትረከብ ወራት በቀሯት ወቅት የኢትዮጵያ ባንኮች አንድ ዶላርን በ8.7 ብር ገደማ ይመነዝሩ ነበር። በዓመታት ከፍተኛ በሚባል ሁኔታ ጭማሬ እያሳየ የመጣው የምንዛሪ ተመን ንሮ አንድ ዶላር በ39.47 (40) ብር እየተመነዘረ ነው።

ይህ የምንዛሬ ተመን በኢትዮጵያ ይፋዊ የባንክ ግብይት መሰረት ነው። ነገር ግን በተለምዶ ጥቁር ገበያ በሚባለው ምንዛሬ ተመን መሰረት አንድ ዶላር 55 ብር እና ከዚያ በላይ እንደሆነ ተሰምቷል።

በተለይም አገሪቷ የይፋዊ እና በጥቁር ገበያ የምንዛሪ ተመንን ዋጋ ለማቀራረብ እየሰራችበት ባለችበት ወቅት በጥቁር ገበያና በመደበኛው ገበያ መካከል ያለው ልዩነት አስራ ስድስት ብር ገደማ መሆኑም የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችን ስጋት ላይ ጥሏል።

ከሰሞኑ በጥቁር ገበያ ላይ የዶላር ምንዛሪ የናረው በትግራይ ክልል ባለው ወታደራዊ ግጭት፣ አገሪቷ ባጋጠማት አለመረጋጋት እንደሆነ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ቢጠቅሱም የብር ከዶላርም ሆነ ከሌሎች የመገበያያ ገንዘቦች አንፃር መድከም በዓመታት ውስጥ የታየ እንደሆነ ተንታኞቹ ይናገራሉ፤ ይህም አገሪቷ እየተከተለችው ካለው የብር ተገቢውን ዋጋ እንዲይዝ (ዲቫሉዌት) ከማድረግ ጋርና በተለይም የአገሪቱ የንግድ ሚዛን ጉድለት ጋር እንደሚያያዝ ያስረዳሉ።

ከሰሞኑ የናረው የጥቁር ገበያ ምንዛሬ

የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለዓመታት የአገሪቱ አንገብጋቢ ችግር ሆኖ ዘልቋል። የአገሪቱ የተዛባ የንግድ ሥርዓት በተለይም የወጪና የገቢ ንግድ አለመመጣጠን ለእጥረቱ መባባስ ምክንያትም ሆኗል።

ይህ እጥረት በምጣኔ ሃብቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ ተፅዕኖ በማሳረፉ በርካታ ፋብሪካዎችንና ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ እንዲሁም ህልውናቸውን ፈተና ላይ ጥሎታል።

ኢትዮጵያ በወጪ ንግድ፣ በብድር፣ በእርዳታ እንዲሁም ከውጭ አገራት በሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) የምታገኘው ገንዘብ ተጠራቅሞ ለገቢ ንግድ ከምትፈልገው ዶላር በእጅጉ ያነሰ እንደሆነ የፋይናንስ አስተዳደርና የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ ያስረዳሉ።

አገሪቷ ለዓመታት ከምትንገታገትበት የንግድ ሚዛን ጉድለት በተጨማሪ ወታደራዊ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ሲፈጠሩ መንግሥት እንደ አንድ አካል የውጭ ምንዛሬ ስለሚፈልግም የፍላጎትና የአቅርቦት ልዩነት እንደሚፈጠር ይናገራሉ።

በተለይም በተለይም ባለፈው አንድ ወር ውስጥ በጥቁር ገበያ ያለው የዶላር ተመን ከፍተኛ በሚባል ሁኔታ ተምዘግዝጓል። ለዚህም እንደ ዋነኝነት የሚጠቀሰው በአገሪቱ ውስጥ ያለው ግጭትና አለመረጋጋት ነው።

መንግሥት ለሚያካሂደው ወታደራዊ እርምጃ የዶላር ፍላጎት ስለሚኖረው ከዚህም ጋር ተያይዞ መንግሥት ወጪ የሚያደርገው ዶላር ለሌሎች ገቢ ንግዶች የሚውለውን ስለሚሆን እጥረቱን ያጎላዋል።

እንዲህ ባሉ ምክንያቶችም ነጋዴዎች ዶላር ከባንክ የማግኘት ዕድላቸውን ስለሚያጠበውና ከዚህ ቀደም ለነጋዴዎች የሚቀርበው ይፋዊ ዶላር እንደበፊቱ በቂ ስለማይሆን ከፍተኛ እጥረት ሊከተል እንደሚችል ጠቆም ያደርጋሉ።

"ያው ግጭቶች ሲኖሩ አገሪቱ የምታወጣቸው የውጭ ምንዛሪ ይኖራልና ነጋዴ የሚፈልገውን ያህል አያገኝም" ይላሉ።

"ነጋዴዎች ከባንክ ዶላር ካላገኙ ያላቸው አማራጭ ከባንክ ውጭ ያለ ጥቁር ገበያን እንደ አንድ አማራጭ መጠቀም ነው። በዚህም ምክንያት ፍላጎቱ በከፍተኛ ሁኔታ ነው የሚንረው" ይላሉ አቶ አብዱልመናን።

በቀላል ቋንቋም ሲያስረዱ ዶላር እንደ ማንኛውም የሚገዛና የሚለወጥ ሸቀጥ ቢታይ የዶላር ተመንም እንደ ማንኛውም ሸቀጥ በገበያ ዋጋ የሚተመን ይሆናል።

መሰረታዊ በሆነው የምጣኔ ሃብት እሳቤ መሰረት ፍላጎትና አቅርቦት በማይመጣጠኑበት ወቅት እንደ ማንኛውም ሸቀጥ መናር ሊፈጠር የሚችል ሲሆን፤ የዶላር እጥረት በገበያው ውስጥ ካጋጠመ የዶላር ዋጋ ሊንር እንደሚችልም ያስረዳሉ።

እንዲሁ በተቃራኒው የዶላር አቅርቦት በብዛት ካለ ደግሞ ዋጋው እንዲሁ ያሽቆለቁላል በማለትም በፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለውን እሳቤ ያስረዳሉ።

ከዚህም በተጨማሪ በገበያው ውስጥ የዶላር አቅርቦት እጥረት ካለ ነጋዴዎችም እቃ የማከማቸትና ዋጋ የመጨመር አዝማሚያም እንደሚኖር በዓመታት ውስጥ ታይቷል።

አቶ አብዱልመናንም "አለመረጋጋት በሚኖርበት ወቅት የሸቀጦት አቅርቦት ችግርም ስለሚፈጠር፤ እቃ ማከማቸት እንዲሁም የዋጋ መናርም ይከሰታል" ይላሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚ ዲፓርትመንት መምህር የሆኑት ዶክተር ተኪኤ አለሙ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አገራት ውስጥ አለመረጋጋቶች በሚፈጠሩበት ጊዜ ይኸው ሁኔታ እንደሚፈጠር ታሪክን በማጣቀስ ይናገራሉ።

በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጀርመን የመገበያያ ገንዘብ (ዶች ማርክ) በመጥፋቱ ዜጎች በሲጋራ ይገበያዩ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ምንም እንኳን በጥቁር ገበያው ላይ ያለው የምንዛሪ ተመን ፍጥነት በአገሪቱ ባለው አለመረጋጋት ምክንያት ቢሆንም፤ የመደበኛው የብር ምንዛሪ ተመን ነፀብራቅ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ። በመደበኛው ግብይት ላይ የሚታየው የብር መዳከም በጥቁር ገበያውም ላይ የሚታይ ነው ይላሉ።

የብር መዳከምና የለጋሾች ጉትጎታ

የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ለዓመታት መንግሥት ብር ከበዶላር ጋር ያለው ምንዛሪ ተመንን መዳከም እንዳለባት ሲጎተጉቱ ነበር።

ለአስርት ዓመታት አገሪቱ ስትተዳደርበት የነበረው የውጭ ምንዛሬ የግብይት ሥርዓት (የፊክስድ ፎሬይን ኤክስቸንጅ ማርኬት) አሰራርን በተመለከተ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ ሲተቸው ነበር።

የኢትዮጵያ ብር ካለው መግዛት አቅም በላይ ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው ለዓመታትም ሲያሳስብ ነበር። ባንኩ ሲሰራበት የነበረው ሥርዓት ዶላር የመግዛት አቅምን መሰረት በማድረግ የብር የምንዛሪ ዋጋ ተመን ላልተወሰነ ጊዜ በቋሚነት በአንዴ የሚወሰንበት መሆኑ ይታወሳል።

ተቋማቱ ብር ዶላርን የመግዛት አቅሙ ከፍ ያለ በመሆኑም የወጪ ንግድን ለማበረታታት በገበያ ፍላጎት የሚመራ ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሪ የግብይት ሥርዓት ቢዘረጋ አገሪቱ ያለባትን ማነቆ መፍታት እንደሚያስችላት ሲያሳስሰብ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ ፍላጎት የሚመራ ሥርዓት እንዲዘረጋ ወስኗል። በሦስት ዓመታት ውስጥም ሙሉ በሙሉ ገበያ መር ይሆናልም የሚል እቅድ ተይዟል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም ከሁለት ዓመታት በፊት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍና የዓለም ባንክ ለሶስቱ ዓመት የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ድጋፍ በተመለከተ ባደረገው ውይይት እንደ አንድ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠው በሂደት ብርን ማዳከምና ከጥቁር ገበያው ጋር ማመጣጠን እንደሆነ አቶ አብዱልመናን ይናገራሉ።

አገሪቱ ከገባችበት የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ለመውጣት የዓለም አቀፉ ገንዘብ ተቋም፣ አይ ኤም ኤፍ 2.9 ቢሊዮን ዶላር ሲያመቻችላትም ከተቀመጡላት ቅድመ ሁኔታዎች መካከል በዋነኝነት የብር የውጭ ምንዛሪ ተመንን በፍጥነት መቀነስና የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን በሂደት በገበያ ፍላጎት እንዲወሰን ማድረግ የሚሉ ናቸው።

ከዚህም በተጨማሪ አገሪቱ ይህንን የብድር ድጋፍ ለማግኘት የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ማዛወር፣ የመንግሥትን ወጪን መቀነስና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችም ተቀምጠውላታል። ኢትዮጵያ በገባችውም ውል መሰረት በቋሚነት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመፍታትና የገበያ ሥርዓቱንም ለማስተካከል እየሰራች ትገኛለች።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በይፋዊና በጥቁር ገበያ ላይ ያለውን ሰፊ ልዩነት ለማመጣጠንና የብር የመግዛት አቅም ከውጭ ምንዛሪ አንፃር እንዲቀንስ ለማድረግ መንግሥት ብርን ለማዳከም እየሰራ መሆኑንም አቶ አብዱልመናን ይናገራሉ።

በይፋዊና በጥቁር ገበያ ያለውን ልዩነትም ለማጥበብ እየወሰደ ባለው እርምጃ ብር እየተዳከመ መምጣቱንም ያወሳሉ።

"ባለፈው ዓመትም ብር ከዶላር ጋር ሲነፃፀር 15 በመቶ በሚባል ሁኔታም ተዳክሟል" ይላሉ።

የብር የውጭ ምንዛሪ ተመን ከዶላር ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎችም የመገበያያ ገንዘቦችም አንፃር ተዳክሟል።

"የባለፈው ዓመት ፍጥነቱ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማቱ ያመጡት ጫና የፈጠረው ነው። ይሄም ሆኖ ግን ይፋዊ (መደበኛ) በሆነውና በጥቁር ገበያው መካከል እንደተባለው መጥበብ አልቻለም" ይላሉ አብዱልመናን።

ነገር ግን በተቃራኒው ያለው ልዩነት መጥበብ ሳይሆን መንግሥት ይፋዊና የጥቁር ገበያን ለማመጣጠን በሚደረገው ሁኔታ ብር ሲዳከም የጥቁር ገበያውም ከፍ እንደሚል ዶክተር ተኪኤ ይናገራሉ።

"መሰራት ያለበት የጥቁር ገበያውን ተመን እንዴት አድርገን ዝቅ እናድርገው በሚለው ላይ መሆን አለበት። ይህም የተሻለው እሳቤ ሊሆን ይገባል" በማለት አፅንኦት የሚሰጡት ዶክተር ተኪኤ አክለውም "የጥቁር ገበያን ልድረስበት ሲባል የባንኩ ተመን ከፍ ማለቱ አይቀርም" ይላሉ።

በተለይም የጥቁር ገበያ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር የአገሪቱን የዶላር ክምችት ማመናመን እንዲሁም የምታገኛቸውን ገቢ እንድታጣ እንደሚያደርጋትም ይጠቅሳሉ።

አገሪቱ ዶላር ከምታገኝባቸውና የዶላርም ክምችቷንም ለማጠናከር ከምትሰራባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ዲያስፖራው ከውጭ የሚልከው ገንዘብ (ሬሚታንስ) ነው።

ይፋዊ በሆነው ገበያና የጥቁር ገበያ ተመን ላይ ባለው ከፍተኛ ልዩነት ምክንያት በርካቶች በባንክ ብራቸውን የመላክ ፍላጎት እንደሚቀንስ ዶክተር ተኪኤ ይጠቅሳሉ።

"በአንድ ዶላርና በብር መካከል ከአስር ብር በላይ ልዩነት ካለ ማንኛውም ሰው ባንክን መጠቀም አይፈልግም። ጭማሪ ወዳለበት ነው የሚያመራው" ይላሉ።

ይህንንም ሁኔታ ለማስተካከል በቁጥጥርና በማሸግ ሊሆን እንደማይገባም አፅንኦት በመስጠት ይናገራሉ።

በባንኮችና በጥቁር ገበያው መካከል የምንዛሪ ዋጋ ልዩነትን ለማጥበብ ብርን ማዳከም ሳይሆን መፍትሄ የሚሉት እነዚህን ነጋዴዎች ሕጋዊ ማድረግና ንግድ ፈቃድ መስጠት ነው።

"ሥራው አደጋ ስላለውና መወረስም ስላላ በከፍተኛ ሁኔታ የጥቁር ገበያው ይንራል ይህንን ለማስተካከል ሕጋዊ ቢሆኑ ጤናማ ውድድርም ይመጣል" በማለት ያስረዳሉ።

አቶ አብዱልመናንም እንደ ዶክተር ተኪኤ የበለጠ ዘመቻና ማስፈራሪያ በሚኖርበት ወቅት ሥራው የበለጠ አደገኛ ስለሚሆን ተመኑም በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር ታዝበዋል። መንግሥት እንዲህ አይነት እርምጃዎችን ቢወስድም "ኢትዮጵያ ውስጥ ዘመቻ ችግር ፈትቶ እንደማያውቅ" አቶ አብዱልመናን ይያሳስባሉ።

ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማቱ የምንዛሬ ተመንን ማዳከም ወደ ውጭ አገር ምርታቸውን የሚልኩ ባለሃብቶችን እንዲበረታቱና የንግድ ጉድለቱ እንዲስተካከል፣ አገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝና ያለባትን ማነቆ እንድትቀርፍ ያስችላል ሲሉ ቆይተዋል።

ነገር ግን ብሯን ማዳከሟ ከፍተኛ ስጋት እንዳጫረና ለአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ያተረፈው ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት እንደተከሰተም የዘርፉ ባለሙያዎች እየተናገሩር ነው።

የብር የውጭ ምንዛሬ የመግዛት አቅም መዳከም የተፈለገውን ያህል ውጤት በምጣኔ ሀብቱ ላይ እንዳላመጣ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በተለይም ታስቦ የነበረው የወጪና የገቢ ንግድን ማመጣጠን አልቻለም።

አቶ አብዱልመናን እንደሚናገሩት አገሪቱ ከወጪ ንግድ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ስታገኝ በገቢ ንግድ ደግሞ 15 ቢሊዮን ዶላር ወጪ አድርጋለች። ይህንንም ከፍተኛ ልዩነት ማመጣጠን አለመቻሉ ከፍተኛ ማነቆ ፈጥሯል ይላሉ።

ዶክተር ተኪኤ በበኩላቸው ከወጪ ንግዷ በላይ በከፍተኛ ሁኔታ ምርቶች ከውጭ አገር የምታስገባው ኢትዮጵያ የብር ምንዛሬ ማሽቆልቆል ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትን አስከትሏል ይላሉ።

አገሪቱ በየወሩ የምታስመዘግበው የዋጋ ግሽበት ከ20 በመቶ በላይ በመሆኑ በዜጎች ላይ እያሳረፈ ያለው ኢኮኖሚያዊ ጫና ከፍተኛ ሆኗል። ከዋጋ ግሸበትም ጋር ተያይዞ መሰረታዊ የሚባሉ ሸቀጦች ዋጋ መናርም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

ኢትዮጵያ ብሯን በዋነኝነት ያዳከመችው አገሪቷቱ የምትሸጠው ምርት ዋጋ ከረከሰ በርካታ ገቢ ይገኛል፤ እንዲሁም የወጪ ንግዱም ይበረታታል በሚል ቢሆንም ከምርታማነት እንዲሁም ከተወዳዳሪነት ጋር ተያይዞ በርካታ ጥያቄዎች ይነሳሉ።

ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ እውነታ ይሰራል ወይ? በማለት የሚጠይቁት ዶክተሩ አገሪቱ በዋነኝነት ወደ ውጪ የምትልካቸው የግብርና ምርቶች በዓለም ገበያ ያላቸው ተፈላጊነትም እዚህ ግባ የማይባል እንደሆነ ይነገራል። ስለዚህ የምትሸጠው ምርት መታየት አለበት ይላሉ።

"የኢትዮጵያ ምርት ዋጋው ስለቀነሰ የኛን ምርቶች ይገዛልናል የሚል ነው። አቅርቦታችን በከፍተኛ ሁኔታ አምርተን ለዓለም አቀፉ ገበያ እንድናቀርብ የሚያስችለን አቅም የለንም። ስለዚህ እሱ ይሰራል የሚል እምነት የለኝም" በማለትም ያለውን የገበያ ሥርዓትን ዶ/ር ተኪኤ ያስረዳሉ።

ከዚህም በተጨማሪ የአምራች (ማኑፋክቸሪንግ) ዘርፉም አመርቂ የሚባል ውጤት ባለማምጣቱና የአገሪቱ የገቢ ንግድ ከፍተኛ በመሆኑ የንግድ ሚዛኑን አጉድሎታል።

ከዚህ በተጨማሪም የገንዘብ ተመኑ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች የመግዣ ዋጋቸውን በመጨመር የገቢ ንግዷን ለመተካትም ቢታሰብ እንኳን፤ አገሪቱ በዋነኝነት ከውጭ የምታስገባው ነዳጅ፣ መድኃኒትና መሰረታዊ ሸቀጦች መሆናቸውን የሚገልፁት ዶክተር ተኪኤ የእነዚህ እቃዎች ዋጋ መናር ከፍተኛ ቀውስ እንደሚያስከትልም ያስረዳሉ።

ምርትን ወደ ውጭ የሚልኩ ባለሃብቶችን በማበረታት የሚገኘውን ምንዛሪ ከፍ በማድረግ ያለባትን ማነቆ እንድትቀርፍ የታለመ ቢሆንም ለማምረት የሚመጡት ግብዓቶች ዋጋ በተመኑ መጨመር ምክንያት መናሩ ችግር እንደሆነባቸውም ሲናገሩ ይሰማሉ።

በዚህም በብር መዳከም ምክንያት ግብዓቶችን በውድ ዋጋ ገዝተው በተቃራኒው የምርታቸው ዋጋ ስለሚረክስ ላኪዎች ይማረራሉ።

ከውጭ የሚገቡ ምርቶች የመግዣ ዋጋቸውን በመጨመር ያለውን ፍላጎት እንዲቀንስ ለማድረግ ቢታለምም ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባው ምርቶች መሰረታዊ ሸቀጦች ላይ ጭማሪ እንዲኖር አድርጎታል።

የሚገቡትም ሸቀጦች በከፍተኛ ሁኔታ ዋጋ መቀነስ ሳይሆን በከፍተኛ ሁኔታ በመናር የዋጋ ግሸበቱን በማባባስ የኑሮ ውድነቱን እንዳከበደውም ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ የምታመርታቸው ምርቶች ዋጋ ቢቀንስም የአቅርቦቱ መጠን አነስተኛ ከሆነ በተቃራኒው አገሪቱ የገቢ ንግዷ በዚያው መንገድ በመቀጠሉ የተፈለገውን ውጤት ማግኘት እንዳልተቻለም ተነግሯል።

የምንዛሬ ለውጡ የገቢውን ንግድ ለመቀነስ እንዲሁም ሸማቾች ከውጭ የሚገቡ እቃዎችን እንዳይገዙ ለማድረግ እንዲሁም የንግድ ሚዛን ጉድለትን ለማስተካከል ያስችላል ቢባልም ፍሬያማ አልሆነም።

የብር መዳከምና የምንዛሬ ተመኑ ለውጥ በብድርም ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረም እንደሆነ ይነገራል።

ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የኢትዮጵያ ብር ካለው አቅም በላይ ዋጋ ይዟል ብለው ማሳሰባቸው እንዲሁም ብር እንድታዳክም መምከራቸው፤ ለመምህሩ ተቋማቱ አገራት በገበያ መር መተዳደር አለባቸው ከሚለው ርዕዮተ ዓለም ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይናገራሉ።

"የአገራቱን የመገበያያ ገንዘብ ማዳከም ወይም በገበያ ፍላጎት እንዲወሰን የማድረግ ምክር ምጣኔ ሃብታዊ ሳይሆን የርዕዮተ ዓለም ጥያቄ ነው" ይላሉ።

መፍትሄምንድን ነው?

ኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲሁም በገቢና በወጪ ንግድ ሚዛን መጓደል ችግር የገጠማት ሲሆን፤ በዋነኝነት እንደ መፍትሄ የሚቀመጠውም የወጪውን ንግድ ማሻሻልና በተለይም የአምራች (ማኑፋክቸሪንግ) ዘርፉን ማነቆዎች ለማቃለል መሞከር እንደሆነ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎቹ የሚሰጡት አስተያየት ነው።

የብር መዳከሙ ባለበት ሁኔታ የወጪና የገቢ ንግዱ የማይሻሻል ከሆነ በሚቀጥሉት ዓመታት የዶላር ተመን በጥቁር ገበያ መናር ይበልጥ እየተባባሰ ሊሄድ እንደሚችል የሚናገሩት አቶ አብዱልመናን ለዚህ የመንግሥት ፖሊሲ ወሳኝ ነው ይላሉ።

ለሰሞኑ የምንዛሪ ዋጋ መናር የአገሪቱ አለመረጋጋት ምክንያት ቢሆንም መሰረታዊ ችግሮች ካልተፈቱ በመደበኛወም ሆነ በጥቁር ገበያው የብር መዳከሙ ጉዳይ የሚቀጥል ይሆናል፤ መሰረታዊ የሆነና የወጪ ንግዱን የማሻሻል እርምጃ የማይወሰድ ከሆነ የመርገብ ሁኔታ እንደማይኖርም ያስረዳሉ።

መንግሥት በዋነኝነት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ የፖለቲካ መረጋጋትቱን ማምጣት ቢሆንም፤ ነገር ግን በመሰረታዊነትና ዘለቄታዊ መፍትሄ ለማምጣት ግን የውጭ ምንዛሪውን እጥረት መፍታት ነው።

"አገሪቷ በማንኛውም መንገድ የገቢና ወጪ ንግዷን ልታመጣጥን ይገባል" የሚሉት አቶ አብዱልመናን በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን አንቀው የያዙትን ችግሮች መፍትሄ ልታበጅለት እንደሚገባ ይጠቁማሉ።

ጨምረውም የንግድ ሚዛን ጉድለቷን ለማስተካከል ከግብርና ግብዓቶችና ቁሳቁሶች በመውጣት ወደ ማኑፋክቼሪንግ ዘርፉ መገባት መንግሥት በከፍተኛ ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራው የሚገባው ጉዳይ ነው ይላሉ።

በተለይም ከማኑፋክቼሪንግ ዘርፉ ጋር ተያይዞ ሙስና፣ ብቃት ማነስ፣ የተንዛዛ ቢሮክራሲ፣ የኃይል እጥረት፣ የመሰረተ ልማት ችግር፣ ገንዘብ፣ መሬትና ሌሎችም ተግዳሮቶች ይጠቀሳሉ።

በተለይም ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ይገኝባቸዋል ተብለው ታስበው የነበሩት የኢንዱስትሪ ፓርኮች የኃይል እጥረትን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች በሙሉ አቅማቸው ማምረት አለመቻላቸው ይነገራል።

መንግሥት የወጪ ንግዱን ለማጠናከር በባለሙያ፣ የፋይናንስ ተቋማቱን እንዲሁም ሌሎች ማሻሻያዎችን በመስራት ችግሩን ሊቀርፍ ይገባል የሚሉት አቶ አብዱልመናን የገቢ ንግድን መተካት አስፈላጊነትንም ያሰምሩበታል።

"የገቢ ንግድን መተካትም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። መንግሥት አገሪቷ በየትኞቹ ምርቶች ላይ የገቢ ንግዷን መተካት ትችላለች የሚለውንም ማጤን ያስፈልገዋል። በአሁኑ ወቅት ስንዴን ጨምሮ ሽንኩርት ሳይቀር ከውጭ ታስገባለች። ይህ የሚያሳዝን ነገር ነው" ይላሉ።

በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት መንግሥት መጠነ ሰፊ ማሻሻያ ሊያደርግም እንደሚገባ አበክረው ያሳስባሉ።

ዶክተር ተኪኤ ብርን ማዳከም የተሳሳተ ፖሊሲ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚጨምር አይደለም ይላሉ። የብር መዳከም ለከፍተኛ ለሆነ ግሽበት እንደሚያጋልጥ በመጥቀስ የላቲን አሜሪካ አገራትና የዚምባብዌ እጣ እንዳይደርስ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ይላሉ።

አገሪቱ የሚጠቅማትን ፖሊሲ በደንብ ልታጤን እንደሚገባና ለምጣኔ ሃብቷ የሚስማማው የትኛውን መንገድ መከተል ነው የሚለው በደንብ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም ዶክተር ተኪኤ ይመክራሉ።