ኮሮናቫይረስ ፡ የብራዚል ሆስፒታሎች ለኮቪድ-19 ህሙማን የኦክስጅን እጥረት ገጥሟቸዋል ተባለ

የጤና ባለሙያና ህመምተኛ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በብራዚሏ ማናውስ ከተማ የሚገኙ ሆስፒታሎች ለኮሮናቫይረስ ህሙማን የሚውል የማገዣ መሳሪያ መተንፈሻ (ኦክስጅን) ከፍተኛ እጥረት እንዳጋጠማቸውና ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታም ላይ ደርሷል ተብሏል።

ከተማዋ በኮሮና ቫይረስ ክፉኛ ከተጠቁት አንዷ ስትሆን በርካታ ሞቶችም ተመዝግቧል።

የጤና ባለሙያዎች እንደሚናገሩት በህክምና ቁሳቁሶች እጥረትና እርዳታ ባለማግኘት በርካታ ሰዎች ሊሞቱ እንደሚችሉም አስጠንቅቀዋል።

ከአሜሪካ ቀጥሎ በኮሮናቫይረስ ሟቾች ቁጥር እየተከተለች ባለችው ብራዚል 205 ሺህ ዜጎቿን በቫይረሱ ተነጥቃለች።

በተለይም አማዞና ግዛት በመጀመሪያው ዙር በከፍተኛ ሁኔታ ከተጠቁት ስትሆን አሁንም ባገረሸው በዚህ ዙርም በርካታ ሰዎች በቫይረሱ እየተያዙ መሆኑ ተዘግቧል።

አስከሬን ማቀዝቀዣም እጥረት በማጋጠሙ ፍሪጅ የተገጠማላቸው ማከማቻዎች ወደ ሆስፒታሎቹ እየተጋዙ ነው ተብሏል።

ባለስልጣናቱም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል።

ጀሴም ኦሬላና ፊዮክሩዝ አማዞኒያ ሳይንቲፊክ ኢንቨስቲጌሽን የተባለውን ተቋም ወክለው እንደተናገሩት በማናውስ የሚገኙ ሆስፒታሎች በሙሉ ኦክስጅን እንዳለቀባቸው ነው፤ አንዳንድ የኮሮና ማዕከላትም በከፍተኛ ሁኔታ በህሙማን መጨናነቅ ተፈጥሮባቸዋል ማለታቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

ተመራማሪዋ በአንዳንድ ሆስፒታሎች የሚያስደነግጡ ሁኔታዎችንም እንደሰሙ ለብራዚል ሚዲያዎች ተናግረዋል።

ተስፋ የቆረጡ የጤና ባለሙያዎች ህሙማኑን በህይወት ለማቆየት ያለ መተንፈሻ መሳሪያ እንዲተነፍሱ ለማድረግም እየታገሉ መሆናቸውን ፎልሃ ደ ሳኦ ፓውሎ ጋዜጣ ዘግቧል።

በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ በተጋራ ቪዲዮም ላይ አንዲት የጤና ባለሙያ ህዝቡን እርዳታ ስትማፀን ያሳያል።

"በሚያስፈራ ሁኔታ ላይ ነን። የነበረን ኦክስጅን አልቋል" ያለችው ባለሙያዋ አክላም "ኦከስጅን ባለመኖሩ ምክንያት በርካታ ሰዎች እየሞቱ ነው። እባካችሁ ወደ ክሊኒኩ ይዛችሁት ነው። ሰዎች እየሞቱ ነው"

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአማዞና አስተዳዳሪ ዊልሰን ሊማ ግዛቲቷ በአጠቃላይ በዚህ ወረርሽኝ ክፉኛ የሚባል ደረጃ ላይ እንደደረሰች ተናግረው የምሽት የሰዓት እላፊ አዋጅም አስተላልፈዋል።

የወረርሽኙን መዛመት ለመግታት ይረዳል የተባለው የሰዓት እላፊ አዋጅ ከዛሬ አርብ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል።

የግዛቲቷ የጤና ቢሮ ፀኃፊ ማርሴለስ ካምፔሎ በበኩላቸው ግዛቲቷ በአካባቢው ከሚመረተው ኦክስጅን ሶስት እጥፍ በላይ እንደሚያስፈልጋትና የድረሱልን ተማፅኖና ጥሪም አሰምተዋል።

የብራዚል ምክትል ፕሬዚዳንት በበኩላቸው ኦክስጅንን ጨምሮ ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶን ወደ አካባቢው መላካቸውን የሚያሳይ ምስል በትዊተር ገፃቸው አጋርተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ፅኑ ህመምተኞችም ሌሎች ከተሞች ወደሚገኙ ሆስፒታሎች እንደሚወሰዱም ሮይተርስ ዘግቧል።