አውስትራሊያ ፓሲፊክን ውቅያኖስን አቋርጦ የመጣውን የአሜሪካ ርግብ ልትገድል ነው

ርግብ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

የአውስትራሊያ ባለስልጣናት ርግቡ በእቃ መጫኛ መርከብ ወደ አውስትራሊያ ሳይመጣ እንዳልቀረ ግምታቸውን አስቀምጠዋል

የሠላማዊ [ፓሲፊክን] ውቅያኖስን አቋርጦ አውስትራሊያ የገባው ርግብ የአገሪቱን ጥብቅ ሕግና ደንብ በመተላለፍ በቁጥጥር ስር ውሎ በአንድ ስፍራ እንዲቀመጥ ሊደረግ ነው።

ይህ ርግብ አሁን በአውስትራሊያዋ ከተማ ሜልበርን ከመገኘቱ አስቀድሞ በጥቅምት ወር በአሜሪካ ኦሪገን ግዛት በነበረ ውድድር ላይ አንድ ርግብ መጥፋቱ ተገልጾ ነበር።

ነገር ግን ባለሥልጣናት 'ጆዬ' የሚል ስም ያወጡለት ይህ ርግብ፣ ለአውስትራሊያ የዶሮ ርባታ ኢንደስትሪና የአእዋፋት ዝርያ "በቀጥታ የብዝሃ ሕይወት ስጋት ነው" ሲሉ ወስነዋል።

ርግቡም ተይዞ እንዲገደል ውሳኔ ተላልፏል።

ነዋሪነቱ በሜልበርን የሆነው ኬቨን ሴሊ ርግቡን ያገኘው በገና ሰሞን ጓሮው ውስጥ ነበር።

"በጣም በረሃብ ጥውልግ ብሎ ነበር፤ ስለዚህ ብስኩት ሰባብሬ አስቀመጥኩለት" ሲል ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል የነበረውን ሁኔታ አስረድቷል።

ከዚያም ወደ በይነ መረብ በመሄድ ርግቡ ከየት እንደመጣ ሲያጣራ ባለቤቱ በአሜሪካዋ የአልባማ ግዛት የሚኖርና በአሜሪካ ምዕራብ ግዛት ኦሪገን በርግቦች ውድድር ወቅት መጥፋቱን ተመዝግቦ አነበበ።

ከዚህ በኋላ ርግብ 'ጆዬ' የአውስትራሊያ መገናኛ ብዙሃንን ቀልብ ሳበ። በዚህም ምክንያት የአውስትራሊያ ባለሥልጣናት ተላላፊ በሽታ ስላሰጋቸው ኬቨን ሴሊን አገኙት።

እስካሁን ድረስ ርግቡ አልተያዘም፤ ነገር ግን የግብርና፣ ውሃና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ የአካባቢው አዕዋፋትን በሽታ ሊያሲዝ ስለሚችል ታድኖ መያዝ አለበት ሲሉ ውሳኔ አሳልፈዋል።

የቢሮው ቃል አቀባይ "ማንኛውም ከባሕር ማዶ ወደ አገር ውስጥ የሚገባ ለማዳ ወፍ የአውስትራሊያን የጤና መስፈርት ሳያሟላና ፈቃድ ሳያገኝ አይገባም" ብለዋል።

"ለብዝሃ ሕይወት ያለውን አደጋ ለመቆጣጠርም ርግቡ ተይዞ መወገድ አለበት" ብለዋል።

ርግቡ ከአሜሪካ የምዕራብ ግዛት ወደ አውስትራሊያ ደቡባዊ ክፍል 8 ሺህ ማይል ርቀት እንዴት መጓዝ እንደቻለ እቅጩን የሚናገር አንድም አስረጂ አልተገኘም። ነገር ግን ባለሥልጣናቱ በእቃ ጫኝ መርከብ ላይ ሆኖ እንደመጣ ግምታቸውን ተናግረዋል።

ወደ አውስትራሊያ በሕጋዊ መንገድ ርግብ ይዞ መግባት የሚቻል ቢሆንም ውጣ ውረዱ እንዲሁም ወጪው ግን ከባድ መሆኑ ይነገራል።

አንድ ርግብን ወደ አውስትራሊያ ለማስገባት በአስር ሺዎች የሚቆጠር ዶላር መክፈል የሚያስፈልግ ሲሆን ለበርካታ አስርት ዓመታት አንድም ርግብ ከአሜሪካ ወደ አውስትራሊያ ገብቶ አያውቅም።

በአውስትራሊያ እንዲህ አይነት ችግር ሲገጥም ርግቡ 'ጆይ' የመጀመሪያው እንስሳ አይደለም።

ከዚህ ቀደም ተዋናይ ጆኒ ዶፕ እና በወቅቱ ባለቤቱ የነበረችው አምበር ሀርድ ውሻዎቻቸውን በሕገወጥ መልኩ በግል አውሮፕላናቸው ይዘው በመምጣታቸው ተመሳሳይ እግድ ተጥሎባቸው ነበር።