ኮሮናቫይረስ- ዚምባብዌ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ያላዳረጉ 10ሺህ ዜጎቿን አሰረች

የፎቶው ባለመብት, EPA
የዚምባብዌ ፖሊስ ባለፈው ሳምንት ብቻ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ያላደረጉ 10 ሺህ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለፀ።
በተጨማሪም 16,000 ሰዎች ደግሞ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ በመጣሳቸው ብቻ በቁጥጥር ስር ውለዋል ተብሏል።
በርካታ በቁጥጥር ስር የዋሉ ዜጎች መቀጮ እንዲከፍሉ መጠየቃቸው ተገልጿል።
ዚምባብዌ የተህዋሲውን ስርጭት ባለበት ለመግታትና ለመቆጣጠር በሚል ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ያወጣችው ከፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ሁለት ቀን ቀደም ብላ ነው።
በደቡብ አፍሪካ ከነበሩ ትልልቅ ክብረ በዓላትና መሰባሰቦች በኋላ በአገሪቱ የኮሮናቫይረስ ስርጭት በፍጥነት እየጨመረ መምጣቱ የተገለፀ ሲሆን፤ ይህም ወደ ሁለተኛ ዙር ወረርሽኝ ያድጋል ተብሎ ተሰግቷል።
በዚምባብዌ በአሁን ጊዜ 9000 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጠ ሲሆን፣ ረቡዕ እለት በአንድ ቀን በኮሮናቫይረስ ምክንያት 38 ሰዎች መሞታቸው ተመዝግቦ፣ በአገሪቱ ታሪክ ከፍተኛው ነው ተብሏል።
የአገሪቱ የኮሮናቫይረስ ስርጭት መጨመር የጤና ተቋማት በሕሙማን እንዲጨናነቁ ሲያደርግ፣ የሕክምና ባለሙያዎችም በኮሮናቫይረስ መከላከል ወቅት የሚያደርጉት የመከላከያ ጭምብል፣ እጥረት እንዳጋጠማቸው እየተገለፀ ነው።
በዚምባብዌ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱ ከታወቀበት ከመጋቢት ወር ጀምሮ እስካሁን ድረስ 34 ሺህ ሰዎች በተህዋሲው መያዛቸው ሲረጋገጥ ከእነዚህም መካከል 600 ያህሉ ሞተዋል።
አፍሪካ እስካሁን ከ3 ሚሊዮን በላይ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች የተመዘገቡባት ሲሆን 75 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችም በበሽታው ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል።