ትግራይ- በፌደራል መንግሥቱና ሕወሓት መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ኤርትራውያን ስደተኞች ያሉበት ሁኔታ

ስደተኛ በሱዳን

የፎቶው ባለመብት, AFP

የተባበሩት መንግሥታትና የአውሮፓ ሕብረት በፌደራል መንግሥቱና በህወሓት ኃይሎች መካከል የተካሄደውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ በክልሉ የሰብዓዊ ቀውስ ሊባባስ ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ትናንት ማምሻውን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት ኃላፊ ፊሊፖ ግራንዲ፣ በትግራይ ክልል ባለው ሁኔታና በንፁሃን ዜጎች ላይ ባለው ተጽዕኖ በተለይ ደግሞ በክልሉ ተጠልለው የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ሁኔታ እጅጉን እንዳሳሰባቸው ገልፀዋል።

በትግራይ ክልል ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው በሱዳን የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ይገኛሉ።

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ በአገር ውስጥ ተፈናቅለዋል የተባለ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ ወደ አዲስ አበባና ሌሎች የአገሪቱ ክልሎች መሸሻቸው ተገልጿል።

የፌደራል መንግሥቱ ከህወሓት ኃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ በገባበት በትግራይ ክልል ውስጥ፣ በመቶ ሺህ የሚደርሱ የኤርትራ ስደተኞች የሚኖሩ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥትና የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት (ዩኤንኤችሲአር) ከለላ ያደርጉላቸው ነበር።

በክልሉ ግጭቱ እንደተቀሰቀሰ የበርካታ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅት ሠራተኞች፣ የዩኤንኤችሲአርን ጨምሮ፣ ስደተኞቹን ከአነስተኛ ድጋፍ ጋር በአንዳንድ ስፍራም ያለምንም ድጋፍ ትተዋቸው አካባቢውን ለቅቀው መውጣታቸውን ቢቢሲ መረዳት ችሏል።

በጥቅምት ወር ላይ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ስደተኞቸ ድርጅት ኤጀንሲ ኃላፊዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ በአካባቢው ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ድርጅቱ ወደ ስደተኞች መጠለያዎች መድረስ እንዲሁም ሠራተኞቻቸውን ማግኘት አለመቻላቸውን ገልፀው ነበር።

"ምን እየተካሄደ እንደሆነ ለማወቅ ለእኛ ከባድ ነው። ከዚህ የግንኙነት መስመር ሙሉ በሙሉ መቋረጥ በፊትም የነበረን የግንኙነት መስመር በጣም ውሱን ነበር። በሽመልባ የስደተኞች መጠለያ የሚገኙ ስደተኞች ለደኅንነታቸው ሲሉ ወደ ህጻጽ መጠለያ ጣብያ እያመሩ ነው።"

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በህወሓት ታጣቂዎች ላይ ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ መውሰድ የጀመረው እርምጃ፣ በክልሉ የተለያዩ ስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የለውም ሲል ተናግሮ ነበር።

ባለስልጣናት በትግራይ የሚገኙት የስደተኛ መጠለያዎች ደኅንነታቸው የተጠበቀ በመሆኑ ስጋት ገብቷቸው ለቅቀው የወጡ እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በታኅሣስ ወር ላይ "በርካታ ቁጥር ያላቸውና የተሳሳተ መረጃ የደረሳቸው ስደተኞች ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ መጠለያውን ለቀው ወጥተዋል" ሲል ተናግሯል።

"መንግሥት እነዚህን ስደተኞች ወደ መጡበት መጠለያ ጣቢያ ደኅንታቸው ተጠብቆ እንዲመለሱ እያደረገ ነው" በማለት ምግብ ወደ መጠለያ ጣብያዎቹ እየተጓጓዘ መሆኑን አስታውቋል።

በማይ አይኒ የስደተኞች መጠለያ ጣብያ ይኖር የነበረና አሁን ወደ ሌላ የአገሪቱ ክፍል የሄደ ስደተኛ ለቢቢሲ እንደገለፀው መጠለያውን ለቀው የወጡበት ምክንያት ሁለት መሆኑን አብራርቷል።

"የመጀመሪያው ምክንያት እንደ ምግብ፣ ውሃ፣ መድኃኒት ያሉ መሠረታዊ አቅርቦቶች አለመኖራቸው ነው። የዩኤንኤችሲአር ሠራተኞች መጠለያ ጣቢያውን ጥለው ከሄዱ በኋላ ስደተኞቹ ለረሃብ ብቻ ሳይሆን ለአደጋም ተጋልጠናል።"

ለደኅንነቱ ሲባል ስሙ እንዳይገለፅ የጠየቀው ይህ ስደተኛ ሁለተኛ ያለውን ምክንያት ሲያስረዳም የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ጎን በመሰለፍ እየተዋጉ መሆናቸውን መስማታቸው ለአደጋ እንደተጋለጡ እንዲሰማቸው ማድረጉን ያስረዳል።

"የኤርትራ ወታደሮች በሽመልባና ህጻጽ የስደተኛ ካምፖች አደረጉ የተባለውን ስንሰማ በመጠለያ ውስጥ ያለን ሁሉ በፍርሃት ተናጥንና ወዲያውኑ ካምፑን ለቅቀን ወጣን።"

በአዲ ሀሪሽ ይኖር የነበረ ሌላ ስደተኛ በበኩሉ ". . . ጦርነቱ መጠለያ ጣቢያው ወደ ሚገኝበት አካባቢ በደረሰ ሰዓት፣ ለደኅንነታችን ስንል ከለላ ፍለጋ ሸሸን። ምግብና ውሃ እያለቀ ሲመጣም ስደተኛው ያለውን እየተጋራ ሲቃመስ ነበር። መጠለያ ጣብያውን ለቅቀን የወጣነው በረሃብና በጥማት ምክንያት ነው" ሲል ለቢቢሲ የነበረውን ሁኔታ አስረድቷል።

አንድ ስደተኛ እንደሚገልፀው "አዲ ሃሪሽ የስደተኞች መጠለያን ለቅቄ ወደ አዲ አርቃይ ሄድኩ። ከአዲ አርቃይ በሰው 95 ብር በመክፈል ወደ ጎንደር አቀናን። በኬላዎች አካባቢ ቢያስቆሙንም ኤርትራዊነቴን የሚገልጽ መታወቂያ ስላለኝ ችግር አልገጠመኝም" ብሏል።

ከዚያም ከጎንደር ተነስቶ ወደ አዲስ አበባ ለአንድ ሰው 900 ብር በመክፈል መሄዱን ተናግሯል። እርሱ እንደሚለው ከሆነ ከጎንደር አዲስ አበባ ለመድረስ 13 ሰዓት ያህል ወስዶባቸዋል።

በሽመልባ የስደተኞች ጣቢያ ይኖር የነበረ ስደተኛ ማንነቱ እንዳይገለጽ በመጠየቅ ለቢቢሲ እንደተናገረው፣ በኅዳር 2/2013 ዓ.ም የኤርትራ ወታደሮች ወደ ሽመልባና ህጻጽ መጠለያዎች መምጣታቸውን ገልጿል።

"የኤርትራ ወታደር ደንብ ልብስን የለበሱ ሰዎች በአንድ ስፍራ እንድንሰባሰብ ካደረጉ በኋላ የመጡት ከትግራይ ሚሊሻዎች ሊከላከሉን መሆኑን ነገሩን።"

"እዚህ ሊከላከልላችሁ የሚችል ማንም የዩኤንኤችሲአር ባለስልጣን የለም፤ ሁሉም ሄደዋል አይመለሱም" አሉን።

ግሰለቡ እንዳለው ከሆነ ወታደሮቹ "በረሃብ ከምትሞቱ" በማለት፣ ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ እንዳግባቧቸውና የኤርትራ መንግሥት ይቅርታ እንዳደረገላቸው እንደነገሯቸው ያስታውሳል።

በሚቀጥለው ቀን ከጋሽ ባርካ ክልል የኤርትራ ባለሥልጣናት መጥተው የስደተኞቹን ተወካይ፣ "የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ባለሥልጣን ሠራተኞች" በመሰብሰብ ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ እንዲያሳምኗቸው መናገራቸውን ይገልጻል።

ነገር ግን ስደተኞቹ ለተወካያቸው ጥያቄያቸው እስኪመለስ ድረስ መመለስ እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።

ይህ ኤርትራዊ ስደተኛ እንደሚገልፀው፣ ከሁለት ቀናት በኋላ የኤርትራ ብሔራዊ ደኅንነት አባላት የሆኑ ሰዎች ወደ መጠለያው በመምጣት፣ በጉልበት ስደተኞቹን በመክበብ የተወሰኑትን ወደ ኤርትራ ወስደዋቸዋል።

ከተወሰዱት ስደተኞች መካከል በርካቶቹ ለአስር ዓመት ያህል በመጠለያ ጣቢያው የኖሩ ሲሆን የተወሰኑት ደግሞ የስደተኛ ማኅበረሰቡ ተወካይ ናቸው።

ይህ ግለሰብ ለቢቢሲ እንደገለፀው በኃይል ታፍነው ከተወሰዱት መካከል አንዲት ኤርትራዊ እናት ያለችበት ሲሆን፣ ጨቅላ ልጅ መታቀፏን ያስታውሳል።

"ባለፈው ዓመት በመጠለያ ውስጥ ትዳር ከመሰረተች በኋላ ነበር የወለደችው። ከትዳር አጋሯና ከጨቅላ ልጇ ጋር በጉልበት እንድትመለስ ተደርጓል።"

ሽመልባና ህጻጽ የስደተኞች መጠለያዎችን በተመለከተ ዩኤንኤችሲአር እስካሁን እንዳልጎበኛቸው ተናግሯል።

"ወደ እዚያ ለመሄድ ፈቃድ የለንም። የምናውቀው ነገር ቢኖር ለሁለት ወራት ያህል ከየትኛውም አቅርቦት ተቋርጠው ነው ያሉት።"

ከሽመልባና ህጻጽ የስደተኛ ጣብያዎች ታፍነው ስለተወሰዱ ኤርትራውያን የተጠየቀው ድርጅቱ፣ "በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን አናግረናል። በእርግጥም በሰሜን መጠለያ ጣቢያዎች ስደተኞች ታፍነው መወሰዳችውን ሰምተናል። ማረጋገጥ የምንችልበት መንገድ የለም፤ ነገር ግን እውነት ከሆነ በአስከፊ ሁኔታ የዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ ነው" ሲል ምላሽን ሰጥቷል።

የስደተኞች ድርጅቱ በድጋሚ የኢትዮጵያ መንግሥትን መጠለያ ጣቢያዎቹ የተለመደውን አገልግሎት መስጠት እንዲቀጥሉ እንዲደረግ ጠይቋል።

የኤርትራ ስደተኞች በትግራይ

በትግራይ በሚገኙ አራት የስደተኛ መጠለያ ጣብያዎች 100 ሺህ የሚጠጉ ኤርትራውያን ስደተኞች ይኖራሉ። ኤርትራውያኑ አገራቸውን ጥለው የተሰደዱት ፖለቲካዊ እስርንና የግዴታ የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎትን በመሸሽ ነው።

ባለፈው ወር የተባበሩት መንግሥታት ስደተኞች ኤጀንሲ የበላይ ኃላፊ በትግራይ ክልል የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች በግዴታ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ስለመደረጉ፣ ስለ መታገታቸውንና መገደላቸው መስማታቸው በመግለጽ "እጅጉን ስጋት እንደፈጠረባቸው" ተናግረው ነበር።

ፊሊፖ ግራንዴ እንዳሉት እንዲህ አይነት ድርጊት ከተረጋገጠ፣ ዋነኛ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ነው ብለዋል። ግራንዴ አክለውም የተባበሩት መንግሥታት በትግራይ የሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎችን ለመጎብኘት ያለምንም ገደብ እንዲፈቀድ ጠይቀዋል።

በፈረንጆቹ ገና የተባበሩት መንግሥታት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በጥምረት በማይ አይኒ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ለ13 ሺህ ኤርትራውያን ስደተኞች የምግብ እርዳታ አድርሷል።

240 ሜትሪክ ቶን ምግብ ደግሞ በአዲ ሃሩሽ የስደተኞች መጠለያ ለሚገኙ 12 ሺህ 170 ስደተኞች መሰጠቱን የተባበሩት መንግሥታት ያወጣው መግለጫ ያሳያል።

ድርጅቱ ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለስደተኞቹ ሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ እየተሰራ ቢሆንም በትግራይ ክልል ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ጊዜ አንስቶ ሽመልባና ህጻጽ የስደተኛ መጠለያ ጣብያዎችን መመልከት እንዳልቻለ ገልጿል።

ፊሊፖ ግራንዴም በእነዚህ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ኤርትራውያን ደኅንነት እንደሚያሳስባቸው በመግለጫቸው ላይ ገልፀዋል።

በእነዚህ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ስደተኞች ለሳምንታት ያለምንም እርዳታ መቆየታቸውን በመግለጽ የሁኔታውን አሳሳቢነት ጠቅሰዋል።

አክለውም እነዚህ ጣቢያዎች ስላሉበት ሁኔታ የተለያዩ ተጨባጭ ያልሆኑ መረጃዎች እንዲሁም የዓለም አቀፍ ሕግና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የሚያሳዩ ውድመቶች መድረሳቸውን የሚያስረዱ የሳተላይት ምስሎች መመልከታቸውንም አብራርተዋል።