ትግራይ ፡ የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም (አምባዬ) መስፍን

አቶ ስዩም መስፍን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በትግራይ ውስጥ የተከሰተውን ወታራዊ ግጭትን ተከትሎ በተፈላጊነት የስም ዝርዝራቸውን ካወጣው ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች መካከል አንዱ የሆኑት የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም መስፍን በአገሪቱ የጸጥታ ኃይሎች ረቡዕ ጥር 05/2013 ዓ.ም መገደላቸው ተገልጿል።

አቶ ስዩም መስፍን ከፍተኛ የህወሓት አመራር ሆነው ከሃያ ዓመታት በላይ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና በቻይና የአገሪቱ አምባሳደር ሆነው የሰሩ ሲሆን ከህወሓት የትጥቅ ትግል ጀምሮ ከፍተኛ ተጽእኖ የነበራቸው ግለሰብ እንደነበሩ ይነገራል።

ስዩም (አምባዬ) መስፍን

ስዩም መስፍን በ1940ዎቹ መጀመሪያ ትግራይ ውስጥ አዘባ ተብሎ በሚጠራ የአጋሜ አውራጃ ቀበሌ ነው የተወለዱት።

የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲ ግራት ከተማ አግአዚ ትምህርት ቤት በመከታተል፤ በባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የዲፕሎማ ምሩቅ ናቸው።

ከፍተኛ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የገቡት አቶ ስዩም፤ በዩኒቨርሲቲው የትግራይ ተማሪዎች ማኅበርን ካቋቋሙት መካከል አንዱ ናቸው።

በ1965 ዓ.ም ማኅበሩ በድብቅ ወደ ተመሰረተው የትግራይ ብሔር የፖለቲካ ቡድንነት ሲሸጋገር ስዩም ፓርቲውን ከመሰረቱት ሰባት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች አንዱ ነበሩ።

የንጉሡ ሥርዓት መውደቅን ተከትሎ በርካታ ወጣቶች የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በመመስረት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ፤ የትግራይ ብሐር ፓርቲ አባላትም "የትግራይ ሕዝብ ጥያቄዎች በትጥቅ ትግል ነው የሚፈቱት" በማለት ጠመንጃ አንስተው ትግል ለመጀመር ወደ ትግራይ በረሃማ አካባቢዎች ሄዱ።

አቶ ስዩም መስፍንም የዚህ ውሳኔ አካል ሆነው ከጓዶቻቸው ጋር ወደ ትግራይ አቀኑ።

ስዩም - በትጥቅ ትግል

የትግራይ ሕዝብን ጥያቄዎች ለመመለስ ትጥቅ ትግል እንዲጀመር ከተወሰነ በኋላ የንቅናቄው አመራር በሦስት የተለያዩ መንገዶች የተሰጠውን ዓላማ እንዲፈጽም ተወሰነ።

አንዱ ቡድን ወደ ደደቢት በረሃ በመሄድ የትጥቅ ትግሉ መጀመርን ይፋ እንዲያደረግ፣ ሁለተኛው ወደ ኤርትራ በመሄድ የትጥቅ ትግል ተሞክሮ እንዲወስድ፣ ሦስተኛው ደግሞ በከተማ ውስጥ ፖለቲካዊ ሥራዎች እንዲመራ ተደረገ።

በዚህም አቶ ስዩም መስፍን ወደ በረሃ በመሄድ የትጥቅ ትግሉን ከጀመሩት አስራ አንድ ሰዎች መካከል አንዱ ነበሩ።

ቤተሰባቸው አምባዬ ብሎ መጠሪያ ስም ያወጣላቸው አቶ ስዩም፤ ወደ ትጥቅ ትግል ከሄዱ በኋላ ግን ሁሉም ስማቸውን ሲቀይሩ አብረዋቸው ከነበሩት ጓዶች መካከል አንዱ የሆነው ታጋይ ስሑል 'ስዩም' የሚለውን ስም ሰጣቸው።

በ1970ዎቹ አጋማሽ ድርጅቱን ከሚመሩት አንዱ በመሆን የተመረጡት አቶ ስዩም፤ አድያቦ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከመንግሥት ሠራዊት ጋር በተደረገው ከባድ ውጊያ ጭንቅላታቸውን ተመትተው ኤርትራ ውስጥ ህክምና እንደተደረገላቸው "ጽናት" በተሰኘው መጽሐፍ ላይ ሰፍሯል።

ታጋይ መሓሪ ተኽለ (ሙሴ) ከኤርትራ ህወሓት ወደ ሚመራው የትጥቅ ትግል ከተቀላቀሉት ጥቂት ቀደምት ታጋዮች በመንግሥት ተይዞ በሽረ እንዳሥላሴ ከታሳረ በኋላ፤ ስዩም ሙሴን ጨምሮ የታሰሩትን ታጋዮች ለማስፈታት የተዘጋጀውን "የሙሴ ኦፕሬሽን" ለመፈጸም የአዕምሮ ህመምተኛ በመምሰል ስለላ ላይ ተሰማርተው እንደነበር ታሪካቸው ያትታል።

ስዩም- የህወሓት መልዕከተኛ

አቶ ስዩም ከ1969 ዓ.ም መጨረሻዎቹ ጀምሮ የህወሓት የውጭ ጉዳዮች ኃላፊ ሆነው ለ15 ዓመታት በሱዳን የሰሩ ሲሆን፤ በካርቱም ቆይታቸውም ስማቸው ወደ 'ሙሳ' ተቀይሮ እንደነበረም ይነገራል።

አቶ ስዩም በ1983 ዓ.ም ከመለስ ዜናዊና ከብርሃነ ገብረክርስቶስ ጋር በመሆን በለንደን ከመንግሥት ጋር ሲደረግ በነበረው ድርድር ላይ ተሳትፈዋል።

ህወሓት/ኢህአዴግ የደርግ ሥርዓትን ጥሎ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር የወቅቱ የሱዳን ፕሬዝደንት የነበሩት ኦማር አልበሽር ባዋሷቸው አውሮፕላን ከሌሎች ጓዶቻቸው ጋር ወደ አዲስ አበባ በሚጓዙበት ጊዜ የቴክኒክ ችግር አጋጥሟቸው ነበር።

በዚህ ምክንያት አውሮፕላኑ ከባድ አደጋ እንደገጠማት በተረዱ ጊዜ ለ17 ዓመታት የመሩት ትግል በድል ተጠናቆ ማየት አለመቻላቸው ከባድ ድንጋጤ ውስጥ ከቷቸው እንደነበር ይነገራል። ነገር ግን የፈሩት ሳይደርስ በሰላም አዲስ አበባ ገቡ።

ስዩም - የውጭ ጉዳይ ሚኒስት

በህወሓት መሪነት ኢህአዴግ የአገሪቱን ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ አንስቶ አቶ ስዩም መስፍን ለ20 ዓመታት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን በቁልፍ የመንግሥት ሥልጣን ላይ ቆይተዋል።

ከኢትዮ ኤርትራ የድንበር ጦርነት ማብቃት በኋላ በ1993 ዓ.ም በህወሓት አመራሮች መካከል ክፍፍል ሲፈጠር አቶ ስዩም ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጎራ ከተሰለፉት መካከል አንዱ ነበሩ።

ከድንበር ጦርነቱ ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ የግልግል ፍርድ ቤት ለደም አፋሳሹ ጦርነት ዋነኛ ምክንያት የነበረችው ባድመን ለኤርትራ ወስኖ እያለ ለኢትዮጵያ እንደተወሰነ አድርገው በቴሌቪዥን መግለጫ በመስጠት ሕዝብ የድጋፍ ሰልፍ እንዲወጣ በማድረጋቸው በተአማኒነታቸው ላይ ዘወትር የሚጠቀስ ጠባሳ ጥሏል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በዙሪያዋ ካሉ ጎረቤት አገራት ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖራት ለማድረግ አስችለዋል ቢባልላቸውም፤ ከኤርትራ ጋር ግን የድንበር ግጭቱ ሳይፈታ እንዲቆይ በማድረግ ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ያደረጉት ጥረት የለም ተብለው ይተቻሉ።

በተጨማሪም ህወሐት በኢሕአዴግ ውስጥ በነበረው ጠንካራ የበላይነት ወቅት በአገሪቱ ውስጥ ለተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተጠያቂ ናቸው ተብለውም ይከሰሳሉ።

በሌላ በኩል አቶ ስዩም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው በቆዩባቸው ዓመታት የእስያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸው እንዲያፈሱ ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ እንደነበረ ይነገራል።

በዚህም ምክንያት የሚኒስትርነት ቦታቸውን ሲለቁ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ለስድስት ዓመታት ሰርተዋል።

ስዩም - ከለው በኋላ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ አቶ ስዩም ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተመልሰው ማገልገል ጀምረው ነበር። ነገር ግን በተመደቡበት ክፍል ደስተኛ እንዳልሆኑ በመግለጽ ወደ መቀለ እንደሄዱ ይነገራል።

በፌደራል መንግሥቱና በህወሐት መካከል የተፈጠረው መካረር በበረታበት ወቅት፤ አቶ ስዩም በተለያዩ አጋጣሚዎች በመገናኛ ብዙሃን ላይ በመቅረብ ጠቅላይ ሚኒስትሩን አጥብቀው ሲተቹ ቆይተዋል።

በአንድ ቃለ ምልልሳቸውም የኖቤል ኮሚቴ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጠው የሠላም ኖቤል ሽልማት ላይ እየተወዛገበ መሆኑን በመግለጽ ሽልማቱን ለማንሳት እያሰበ መሆኑን በመግለጻቸው መነጋገሪያ ሆነው ነበር።

የሽልማት ኮሚቴውም በእንዲህ አይነቱ ጉዳይ ላይ እንዳልተነጋገረና አንድ ጊዜ የተሰጠ የኖቤል ሽልማት እንደማይመለስ ማብራሪያ መስጠቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ሠራዊት የክልሉን ዋና ከተማ መቀለን በቁጥጥር ስር ከማስገባቱ ቀደም ብሎ እስካለው ጊዜ ድረስ አቶ ስዩምና የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች በከተማዋ የቆዩ ሲሆን፤ ከዚያ በኋላ ግን ከተማዋ ወጥተው ወደ ተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች መሄዳቸው ተነግሮ ነበር።

የእስር ማዘዣ ከወጣባቸው ግለሰቦች መካከል አንዱ የነበሩት አቶ ስዩም መስፍንና ሌሎች ጓዶቻቸው ያሉበት ቦታ በጸጥታ ኃይሎች ተከቦ እጅ እንዲሰጡ የቀረበላቸውን ጥሪ ባለመቀበል ጥር 05/2013 ዓ.ም በተወሰደባቸው እርምጃ መገደላቸውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሰጠው መግለጫ አሳውቋል።

መቀለ በኢትዮጵያ ሠራዊት እጅ ውስጥ መግባቷን ተከትሎ ከነበሩት ጥቂት ቀናት ውጪ የህወሓት አመራሮች ለየትኛውም የመገናኛ ብዙሃን ምንም አይነት መግለጫ ሰጥተው ስለማያውቁ ስለተገደሉት አመራሮቹ ከቡድኑም ሆነ ከሌላ ወገን የተሰማ ነገር የለም።