ኮሮናቫይረስ ፡ ጆ ባይደን የ1.9 ትሪሊየን ዶላር የኢኮኖሚ ማነቃቂያ ማዕቀፍ ይፋ አደረጉ

ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ተመራጩ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተመታውን የአሜሪካ ኢኮኖሚ ለማነቃቃት 1.9 ትሪሊዮን ዶላር የገንዘብ ማዕቀፍ እቅድ ይፋ አደረጉ።

ባይደን ይህን ያስታወቁት በሚቀጥለው ሳምንት በቢሯቸው ሥራ ከመጀመራቸው አስቀድሞ ነው።

ይህ የገንዘብ ማዕቀፍ በምክር ቤቱ ከፀደቀ ለሁሉም አሜሪካዊያን ከሚሰጠው 1 ሺህ 400 ዶላር የገንዘብ ድጎማ ጋር ተደማምሮ ለቤተሰብ የሚሰጠውን ድጎማ 1 ትሪሊየን ዶላር ገንዘብን ያካትታል።

የገንዘብ እፎይታ እቅዱ ወረርሽኙን ለመዋጋት የሚውል 415 ቢሊዮን ዶላር እና ለአነስተኛ ንግዶች ማነቃቂያ 440 ቢሊየን ዶላርንም ይጨምራል ።

ዲሞክራቱ ጆ ባይደን በአሜሪካ ከ385 ሺህ በላይ ሰዎችን የገደለውን ወረርሽኝ ለመዋጋት ቃል ገብተዋል።

ባይደን ባለፈው ዓመት ከሪፐብሊካኑ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በተሻለ ቫይረሱን ለመቆጣጠር የተሻለ እንደሚሰሩ ቃል በመግባት ዘመቻ አካሂደው ነበር።

የጆ ባይደን የገንዘብ እፎይታ ማዕቀፍ ዕቅድ የመጣው በክረምት ወቅት የኮሮናቫይረስ ሥርጭት ከፍተኛ በመሆኑ ነው።

በአሜሪካ በአንድ ቀን ከ200 ሺህ በላይ አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሲሆን አንዳንዴ በአንድ ቀን የሟቾች ቁጥር 4 ሺህ ይደርሳል።

ባይደን ምንድን ነው ያሉት?

ጆ ባይደን ከትውልድ ከተማቸው ዊልሚንግተን ዴልዌር ሐሙስ ምሽት ባደረጉት ንግግር "ሰዎች እያጋጠማቸው ያለው ቀውስ በግልፅ የሚታይ ነው፤ የምናባክነው ሰዓት አይኖርም" ብለዋል።

አክለውም "የሕዝባችን ጤና አደጋ ላይ ነው፤ እርምጃ መውሰድ አለብን፤ መውሰድ ያለብንም አሁን ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ተመራጩ ፕሬዚደንት መሰናክሎች ይኖራሉ፤ ነገር ግን ሁል ጊዜም ስለሚያጋጥሙን እንቅፋቶችም ሆነ ስለምናስመዘግበው እድገት ለእናንተ ሀቀኛ እሆናለሁ" ብለዋል።

ለኮሮናቫይረስ የተያዘው እቅድ ምንድን ነው?

ባይደን የክትባት ማዕከላትን ማዘጋጀት እና ወደ ሌሎች ራቅ ያሉ አካባቢዎች ተንቀሳቃሽ ማዕከላትን ማሰናዳት ጨምሮ አሜሪካዊያንን ለመከተብ 20 ቢሊየን ዶላር ለማውጣት ይፈልጋሉ።

በትራምፕ አስተዳደር ሁለት ውጤታማ ክትባቶች እየተሰጡ ቢሆንም፤ የጤና ባለሥልጣናት ግን የክትባት ሥርጭቱ መፋጠን አለበት ብለዋል።

በአሜሪካ የክትባቱ ሥርጭት እስካሁን ስኬታማ አይደለም ብለዋል ፕሬዚደንቱ። የባይደን አስተዳደር በ100 ቀናት ውስጥ 100 ሚሊዮን ክትባቶችን ለማዳረስ ዓላማ ይዟል።

ባይደን የእፎይታ ገንዘብ ማዕቀፍ እቅድ ምርመራዎችን ለማስፋፋት 50 ቢሊዮን ዶላር ፤ በፀደይ ወቅት ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ለማገዝ 130 ቢሊዮን ዶላር ይጠይቃል።

ከዚህም በተጨማሪ እቅዱ በቫይረሱ የተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸውን የሚለዩ 100 ሺህ ጤና ባለሙያዎችን ቅጥር ይደግፋል።

የኢኮኖሚ እፎይታውስ?

በአገሪቷ ወደ 11 ሚሊዮን የሚጠጉ ሥራ አጥ ሰዎች አሉ።

ሥራ ለሌላቸው የሚሰጥ ጥቅማ ጥቅም በሳምንት ከዚህ ቀደም ከነበረው 300 ዶላር ወደ 400 ዶላር ከፍ ብሏል።

የቤት ብድር ክፍያን ጨምሮ ይህ ድጋፍም እስከ መስከረም ወር ድረስ ይራዘማል።

ባለፈው ወር በፀደቀው እቅድ በርካታ አሜሪካውያን በነፍስ ወከፍ 600 ዶላር ይደርሳቸዋል።

ይህም ለአንድ ቤተሰብ የሚደርሰውን አጠቃላይ ገንዘብ ወደ 2 ሺህ ዶላር ያደርሰዋል።

ተመራጩ ፕሬዚደንት የፌደራሉ ዝቅተኛ የሥራ ክፍያ ለአንድ ሰዓት 15 ዶላር የነበረው እጥፍ እንዲሆንም ለምክር ቤቱ ጥሪ ያቀርባሉ ተብሏል።

ባለፈው መጋቢት የአሜሪካ መንግሥት ለዜጎቼ ይሆናል ብሎ 1.4 ትሪሊየን ዶላር መመደቡ ይታወሳል።

ምክር ቤቱ እቅዱን ያፀድቀው ይሆን?

ሪፐብሊካኖች አሜሪካ ወረርሽኙን ለመከላከል ቀድሞውኑ ከነበረው ተጨማሪ ትሪሊየኖች እዳ መጨመሯን ሊቃወሙ ይችላሉ።

ተማራጩ ፕሬዚደንት ደግሞ እቅዳቸው " በአነስተኛ ገንዘብ አይሳካም" ሲሉ ያምናሉ።

ይሁን እንጂ በሁለቱ ምክርቤቶችን በሚቆጣጠሩት ዲሞክራት ባልደረቦቻቸው ይታገዛሉ።

የተመራጩ ፕሬዚደንት የሥራ ዘመን ጅማሮ፤ የአሜሪካ ምክርቤት የሚተኳቸውን ፕሬዚደንት ከሥልጣን ከማባረር ሒደት ጀርባ ነው የሚካሄደው።

ምክርቤቱ በምን ያህል ፍጥነት ይህን እንደሚያደርግና ፕሬዚደንቱን ጥፋተኛ ለማድረግ ድምፅ ይስጡ አይስጡ የታወቀ ነገር የለም።