አፍጋኒስታን፡ የታሊባን መሪ አባላቶቹ በርካታ ሚስቶች ከማግባት እንዲቆጠቡ ትዕዛዝ አስተላለፉ

ፊታቸውን የሸፈኑ ሙስሊም ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአፍጋኒስታን የሚገኘው የታሊባን መሪ ለአመራሩ አባላትና የጦር ኮማንደሮች በርካታ ሚስቶች ከማግባት እንዲቆጠቡ የሚያዝ አዋጅ አስተላልፈዋል።

መሪው "ከጠላቶቻችን ከፍተኛ ትችት እየቀረበብን ነው" በሚልም የጦር ኮማንደሮቻቸው ከአንድ በላይ ሚስት ለማግባት በሚል የተጋነነ ወጪ ከማውጣትም እንዲታቀቡ ማዘዛቸውን የቢቢሲው ኩዳይ ኑር ናስር ዘግቧል።

በእስልምና እምነት መሰረት ወንዶች እሰከ አራት የትዳር አጋር ሊኖራቸው ይችላል። በአፍጋኒስታን፣ ፖኪስታንና በርካታ የእስልምና እምነት ተከታይ ባላቸው አገራትም ከአንድ በላይ ሚስት ማግባት ህጋዊ ፈቃድ አለው።

ነገር ግን ይህ ልምድ ለሙሽራ የሚከፈለው ጥሎሽ ጋርም ተያይዞ የጦር ኮማንደሮች ለከፍተኛ ወጪ ተዳርገዋል በሚልም ይህ አዋጅ እንደተላለፈ ቢቢሲ ከታሊባን ምንጮች ባገኘው መረጃ መረዳት ችሏል።

ጥሎሽ ( ዳውሪ) አፍጋኒስታንን ጨምሮ በፓኪስታንና በሌሎች አገሮችም የሚከናወን ሲሆን ጋብቻውም እንዲፀና በሚል ለሙሽራዋ ቤተሰቦች የሚሰጥ ገንዘብ ነው።

በአሁኑ ወቅት ታጣቂው የታሊባን ቡድን የአገሪቱ መፃኢ ፈንታን በተመለከተ ከአገሪቱ መሪዎች ጋር ውይይትም እያደረጉ ይገኛል።

የታሊባን አባላት የተለያዩ ቤተሰባቸውን ወጪ ለመሸፈን በሙስና ገንዘብ እያሰባሰቡ ነው የሚሉ ውንጀላዎች መሰማታቸውን ተከትሎም በአመራሩ ላይ ስጋት ፈጥሯል።

በርካታዎቹ የታሊባን ከፍተኛ አመራሮች ከአንድ በላይ ሚስት ቢኖራቸውም ህጉ ግን ወደ ኋላ ተመልሶ ስለማይሰራ ተግባራዊ አይደረግባቸውም ተብሏል።

ሁለት ገፅ ያለው ይህ አዋጅ በአፍጋኑ የታሊባን መሪ ሙላህ ሂባቱላህ ስም ተፈርሞ የወጣ ሲሆን በርካታ ሚስቶችን ማግባት በቀጥታ አይከለክልም።

ነገር ግን ለሰርግና ለጥሎሽ የሚውሉ ወጪዎች ከታሊባን ተቃናቃኞች ትችትና ውግዘት እያስከተሉ ስለሆነ አባላቶቻቸው በአጠቃላይ ከአንድ በላይ ሚስት እንዳያገቡ የሚል ትእዛዝን ይዟል።

"አመራሩና የጦር ጀኔራሎቹ ከአንድ በላይ ሚስት ከማግባት ቢታቀቡ ሙስናን በመሳሰሉ ህገወጥ ተግባራት እንዳይሳተፉ ይረዳቸዋል" ይላል አዋጁ

ሆኖም አዋጁ ወንዶች ከአንድ በላይ ሚስት ማግባት የሚችሉበትን ልዩ ሁኔታዎች አስቀምጧል።

በዚህም መሰረት ልጅ የሌላቸው ወንዶች፣ ወንድ ልጅ የሌላቸው፣ ባሏ የሞተባትን ያገቡ እንዲሁም ሃብታም የሆኑ በርካታ ሚስቶችን ማግባት ይችላሉ።

እነዚህን መስፈርቶች የሚያሟሉ ወንዶች ከአንድ በላይ የትዳር አጋር በሚፈልጉበት ወቅት ከኃላፊያቸው ፍቃድ ማግኘት እንደ ቅድመ ሁኔታም ተቀምጧል።

ቢቢሲ ከታሊባን ምንጮች ባገኘው መረጃ መስረት ደብዳቤው በአፍጋኒስታንና በፓኪስታን ለሚገኙ በተለያየ ደረጃ ላይ ላሉ አመራሮች ደርሷቸዋል ተብሏል።