ቻይና፡ የአሊባባ ኩባንያ መስራች ጃክ ማ ከወራት በኋላ ታዩ

ጃክ ማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሊባባ ኩባንያ መስራች ቻይናዊው ባለፀጋ ጃክ ማ ለወራት ከህዝብ እይታ ተሰውረው ከሰሞኑ ብቅ ብለዋል።

የቻይና ባለስልጣናት የቢሊየነሩ የንግድ አሰራር ላይ ከፍተኛ የሆነ ቁጥጥርና ጫና ማሳደራቸውን ተከትሎ ባለሃብቱ ደብዛቸው ጠፍቶ ነበር።

ለወራት ያህልም ያልታዩት ባለፀጋ የት ናቸው የሚለውም ጉዳይ ለበርካታ ጥርጣሬዎችም በር ከፍቶ ነበር።

በተለይም መንግሥት የባለሃብቱን የቢዝነስ አሰራር እየፈተሸና ጠበቅ ያለ ምርመራ በከፈተበት ወቅት መሆኑ ደግሞ ወሬዎችን አቀጣጥሏል።

ቢሊየነሩ ቻይና የሚገኙ 100 የገጠር መምህራን ጋር በቪዲዮ ስብሰባ በማካሄድ "አለሁ" ማለታቸውን የአገሪቱ ሚዲያ ዘግቧል።

ዜናውን መጀመሪያ ሪፖርት ያደረገው ቲናሙ የተባለው የዜና ወኪል እንዳስነበበው እነዚህ መምህራን የጃክ ማ በርካታ እርዳታ ድርጅት ጅማሬዎች አካል መሆናቸውን ነው።

አመታዊ የሆነው ስብሰባም ሳንያ በሚባል ሪዞርት ይካሄድ የነበረ ሲሆን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በበይነ መረብ ሊካሄድ ግድ ብሎታል።

"በወረርሽኙ ምክንያት ሳንያ መሰብሰብ አልቻልንም" በማለት ጃክ ማ ተናግረዋል።

አክለውም " ወረርሽኙ ሲገታ እንደ ቀድሞው ዝግጅታችንን ሳንያ እናደርገዋለን" ብለዋል

በቪዲዮውም ላይ ግራጫ ቀለም በተቀባ ቤት ሰማያዊ ሙሉ ልብስ ለብሰው የነበረ ሲሆን፤ ካሜራውን ፊት ለፊት እየተመለከቱ ነበር ተብሏል።

ከቪዲዮውም ሆነ ቲናሙ ካወጣው ዜና ጃክ ማ የት እንዳሉ ማወቅ አልተቻለም።

የቁጥጥር ጫናው

ባለፈው ወር የቻይና ማዕከላዊ ባንክ የጃክ ማ አንት ግሩፕ የተባለ ኩባንያቸው አሰራር ላይ ከፍተኛ ፍተሻ እንዲደረግ አዘዘ።

ጃክ ማ በቻይና ትልቁ ክፍያ ፈፃሚው ድርጅት የሆነው አንት ግሩፕ መስራችና ባለ ከፍተኛ ድርሻም ናቸው።

ከዚህም በተጨማሪ የቻይና የገበያ ስርአት አስተዳዳሪም እንዲሁ አሊ ባባ ገበያውን በበላይነትና በዋነኝነት የተቆጣጠረበትን አካሄድ ላይም ምርመራ ከፍቷል።

የጃክ ማ መጥፋት በህዝቡ ዘንድ መነጋገሪያ የሆነው ዳኛ ከሆኑበት 'አፍሪካ ቢዝነስ ሂሮስ' ተብሎ ከሚጠራው የቴሌቪዥን ፕሮግራም በመጥፋታቸው ነው።

ምንም እንኳን ኩባንያው አሊባባ በስራ መደራረብ ነው የጠፉት ቢልም በርካታ የቻይና ሚዲያዎች በበኩላቸው ጥቅምት ወር ላይ በተካሄደ ዝግጅት ላይ የቻይናን የባንክ ስርአት በይፋ መተቸታቸውን ተከትሎ ደብዛቸው እንደጠፋ ዘግበዋል።