የህንዷ መንደር በካማላ ሃሪስ ስኬት ደስታዋን እየገለፀች ነው

የህንዷ መንደር ደስታቸውን እየገለፁ

በደቡባዊ ህንድ፣ ናዱ ግዛት የምትገኘው ቱላሴንድራፑራም መንደር ከወትሮው ለየት ባለ ደስታና መንፈስ ተሞልታለች።

ለዚህም ደግሞ የመንደሯ ነዋሪዎች ተገቢ ምክንያት አላቸው።

በዛሬው ዕለት በዓለ ሲመታቸውን የሚፈፅሙት የአሜሪካ ተመራጭ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ ቤተሰቦች ትውልድ መነሻ ስፍራ ናት።

የመንደሯ ነዋሪዎች የየቀኑ ተግባራቸውን ገታ አድርገው በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያ ሴት ምክትል ፕሬዚዳንት የምትሆነውን ካማላ ሃሪስን ስኬት በማክበርም ላይ ናቸው።

በመንደሯ ላይ ያሉ ዋና ዋና ጎዳናዎችም ምክትል ፕሬዚዳንቷን "እንኳን ደስ አለሽ" የሚሉ የደስታ መልዕክቶች ተሰቅለውባታል።

ለዝግጅቱም ጣፋጮች፣ ከረሜላዎችና ብስኩቶች ተዘጋጅተዋል። ከዚህም በተጨማሪ የጆ ባይደንና የካማላ ሃሪስ ፎቶ ያለባቸው የቀን መቁጠሪያዎችም ለነዋሪዎች እየተሰጡ ነው።

የሃሪስን ፎቶ የያዙ ነዋሪዎችም በአካባቢው ባለ የአምልኮ ቦታ ፀሎት እያደረሱላት ነው። አበባ፣ ጣፋጭና ከረሜላዎችንም ለካማላ ሃሪስ ቤተሰቦች አማልክት በማቅረብ ምስጋናና ችሮታቸውን እየገለፁ ነው።

ርችቶች የተተኮሱ ሲሆን ቸኮሌትም ለምዕመናኑ ተከፋፍሏል።

"ካማላ ሃሪስ መንደራችንን መጥታ ብትጎበኝ ደስ ይለናል። የደረሰችበት ስኬት የመንደራችን ነዋሪ ሴቶችን በትልቁ እንዲያልሙ አድርጓቸዋል" በማለት የዝግጅቱ ዋና አስተባባሪ ሱድሃካር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሱድሃካር እንደሚሉት ጆ ባይደንና ካማላ ሃሪስ እንዲያሸንፉ ነዋሪዎች ሲፀልዩ ነበር።

በንግድ ስራ የተመረቀው ሲቫራንጂኒ በበኩሉ የበዓለ ሲመታቸውን ዝግጅት በጉጉት እየጠበቀ እንደሆነ ተናግሯል።

"ካማላ ሃሪስ ከመንደራችን በብዙ ሺዎች ርቀት ላይ የምትገኝ ብትሆንም ጥብቅ ቁርኝት አለን" ብሏል።

ካማላ ሐሪስ የተወለደችው በካሊፎርኒያ ግዛት ኦክላንድ ከተማ ነው፡፡

እናቷ ሻየመላ ጎፓላን ሕንዳዊት ናት፡፡ አባቷ ዶናልድ ሐሪስ ደግሞ ጃማይካዊ ነበሩ፡፡ አባትና እናቷ ሁለቱም በስደት ነው ወደ አሜሪካ የመጡት፡፡

ሁለቱም እንግሊዝ በቅኝ ከገዛቻቸው አገራት ነው የመጡት፡፡ ሁለቱም እንግሊዝ ሄደው እንዲማሩ ተጠይቀው አሜሪካንን የመረጡ ናቸው፡፡

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

ቀጣይዋ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ ማን ናቸው?