ቻይና "ትራምፕ እንኳን ተወገዱ" አለች

ዶናልድ ትራምፕና ባለቤታቸው

የፎቶው ባለመብት, EPA

የቻይና ባለስልጣናት አስተያየት የሚንፀባረቅባቸው የመንግሥት ሚዲያዎች በተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና ደጋፊዎቻቸው ከስልጣን መወገድ የተሰማቸውን ስሜት ለአለም ከመንገር ወደኋላ አላሉም።

የቻይናው ዜና ምንጭ ዢኑዋ ደግሞ ግልፅ ባለ ቋንቋ "ዶናልድ ትራምፕ እንኳን ተወገዱ!" የሚል መልዕክት በትዊተር ገፁ አስፍሯል።

ብሄራዊው ግሎባል ታይምስ ጋዜጣም እንዲሁ የሁለቱን አገራት ግንኙነት በተመለከተ ባወጣው ዘለግ ባለ ፅሁፍ "ቻይና ከትራምፕ የስልጣን ዘመን የተማረችው ነገር ቢኖር ሁለቱ አገራት ግንኙነትን በተመለከተ ምንም መጠበቅ እንደሌለባት ነው።

የቻይናና አሜሪካን ግንኙነት በተመለከተ እውነታውን የማያንፀባርቅ ተስፋ የለንም፤ ምንም አንጠብቅም" በሚል አስፍሯል።

በተለይም በትራምፕ አስተዳደር ተሰናባቹ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ማይክ ፖምፔዮ ላይ ባለስልጣናቱ ስድብ ቀረሽ የሰላ ትችት ሰንዝረዋል።

የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚያደርገው የተለመደው መግለጫም ቃለ አቀባይዋ ሁዋ ቹንይንግ "በማይክ ፖምፔዮ በኩል ሲነዛ የነበረው መርዛማ ውሸት በሙሉ ይጠራል። ልኩ እሱም ተጠርጎ እንደወጣው ውሸቱም በታሪክ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ ይጣላል" ብለዋል።

ነገር ግን ቃለ አቀባይዋ ማይክ ፖምፔዮን ይናፍቋቸዋል ወይ? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሻቸው "በደንብ! በርካታ መዝናኛ የሚሆኑ ነገሮችን እኮ ያመጣልን ነው። በየቀኑ ድራማ እየተከታተልን ነበር" በማለት ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ አወዛጋቢ ጉዳዮችን በመፃፍ የሚታወቁትን ትራምፕ ግሎባል ታይምስ "ውደዱትም፣ ጥሉትም። ማህበራዊ ሚዲያው ያለ ዶናልድ ትራምፕ ተመሳሳይ አይሆንም። ለብዙዎች አሳዛኝ ነው ብሏል"

ጋዜጣው መረጃዎችን ዋቢ አድርጎ እንደፃፈው " በዊቡ ማህበራዊ ሚዲያ ዶናልድ ትራምፕ በመፈለግ የቁንጮነት ቦታን ይዘዋል። በ2020ም በከፍተኛ ሁኔታ ስማቸው በመነሳትና በዊቡ አንደኛ ስፍራን በመያዝ 589 ጊዜ 'ትሬንድ' አድርገዋል። ይኼም የወረርሽኙን ዜና፣ ታዋቂ ሰዎችንና እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን በመብለጥ ነው" በማለትም አስፍሯል።