ጆ ባይደን የአሜሪካ 46ኛ ፕሬዝዳንት ሆነው ሥልጣን ተረከቡ

ባይደን ቃለ መሀላ ሲፈጽሙ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

ባይደን ቃለ መሀላ ሲፈጽሙ

የአሜሪካንን ሕገ መንግሥት ለማስከበርና ለመጠበቅ ቃል ከገቡ በኋላ ጆ ባይደን በይፋ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት በመሆን ቃለ መሐላ ፈጸሙ።

አዲሱ ፕሬዝዳንት ኃላፊነታቸውን ለመቀበል ቃለ መሐላቸውን የፈጸሙት በአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ጆን ሮበርትስ አማካይነት ነው።

ለወትሮው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይታደሙበት በነበረው የሲመት በዓል ሥርዓት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የጆ ባይደን የቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓት ጥቂት ሰዎች ብቻ የታደሙበት ሆኗል።

ፕሬዝዳንቱ ባደረጉት ንግግር በሥነ ሥርዓቱ ላይ የታደሙትን ሰዎች በአገራቸው "በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች" የህሊና ፀሎት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ፕሬዝዳንት ባይደን ባደረጉት ንግግር ላይ አስተዳደራቸው ሊገጥም ይችላል ያሏቸውን ተግዳሮቶች በተመለከተ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝና "የነጭ የበላይነት" እንቅስቃሴን ጠቅሰው፤ ነገር ግን እነዚህንና ሌሎችንም እንቅፋቶች "ተጋፍጠው እንደሚያሸንፏቸው" ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ በምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት የገቡትን ቃል ዛሬም ደግመውታል። "የአሜሪካንን የመጪ ዘመን ተስፋ" ለመመለስ እንደሚሰሩና ለዚህም "ከቃላት በላይ ተግባር" እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

ለረጅም ዘመናት በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ የቆዩት ጆ ባይደን የታላቋን አገር የፕሬዝዳንትንት መንበር ለመያዝ ረጅም ዓመታትን ፈጅቶባቸዋል።

የ78 ዓመቱ አዛውንት ጆ ባይደን ወደ አሜሪካ መንግሥት የሥልጣን ማዕከል ካፒቶል ሒል በምክር ቤት አባልነት የዴላዌር ግዛትን ወክለው የገቡት ከዛሬ 50 ዓመታት በፊት ገደማ ነበር።

ባይደን ነውጠኛውን የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን በምርጫ በማሸነፍ ዛሬ ቃለ መሐላ የፈፀሙበትን የኃላፊነት ቦታ ለመያዝ ሁለት ጊዜ ተወዳድረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

ኋላ ላይ የባራክ ኦባማ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ለፕሬዝዳንትነቱ ቀረብ ብለው አገልግለዋል።

በዚህ ዙር ለተደረገው ምርጫ ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን ሲያፎካክሩ በርካቶች ባይደን የዴሞክራቲክ ፓርቲን ወክለው የመቅረብ ዕድላቸው ጠባብ ነው የሚል ስጋት ነበራቸው።

ነገር ግን ከተናዳፊው ዶናልድ ትራምፕ ጋር በክርክር ተፋጠው እንደተሰጋው ሳይሆን የበርካታ መራጮችን ድምጽ በማግኘት ለፕሬዝዳንትንት በቅተዋል። ባይደን ምክትላቸውን ሴት ያደረጉ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ለመሆንም በቅተዋል።

ደጋፊዎቻቸው ባይደን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ አዋቂ ናቸው ይሏቸዋል። በእርጋታቸው የሚታወቁት ፖለቲከኛ በግል ሕይወታቸው አሳዛኝ ክስተቶችን አሳልፈዋል።

ባይደን የፖለቲካ ሕይወታቸው የጀመረው ከ47 ዓመታት በፊት ነበር። የአሜሪካ ፕሬዝደንት ለመሆን ጥረት ማድረግ የጀመሩት ደግሞ ከ33 ዓመታት በፊት እአአ 1987 ላይ።

ባይደን በጥቁር አሜሪካውያን ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት አላቸው።

ጆ ባይደን ቃለ መሐላቸውን ፈጽመው የፕሬዝዳንትንት መንበሩን ከመረከባቸው ከሰዓታት በፊት ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዋይት ሐውስን ለቀው ከወጡ በኋላ "ተመልሰን እንመጣለን" ማለታቸው እያነጋገረ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የተቀዛቀዘው የጆ ባይደን ሲመተ በዓል