ቴክኖሎጂ ፡ መከፋትዎን ለአለቃዎ የሚጠቁመው የእጅ አምባር

ሲደሰቱ- ቢጫ፤ ሲከፉ ደግሞ ሰማያዊ ይሆናል ማለት ነው።

የፎቶው ባለመብት, MOODBEAM

የምስሉ መግለጫ,

ሲደሰቱ- ቢጫ፤ ሲከፉ ደግሞ ሰማያዊ ይሆናል ማለት ነው።

ሙድቢም የሚባል የእጅ አምባር ተሠርቷል። የእጅ አምባሩ ቀጣሪዎች የሠራተኞቻቸውን ስሜት የሚቆጣጠሩበት ነው።

መሣሪያው ከሞባይል መተግበሪያ ጋር ይገናኝና መደሰትዎን ወይም መከፋትዎን ለአለቃዎ መልዕክት ያስተላልፋል።

የእጅ አምባሩ ቢጫ እና ሰማያዊ ቀለም ያለው ሲሆን፤ አምባሩን ባደረገው ሰው ስሜት መሠረት ቀለሙ ይለዋወጣል። ሲደሰቱ- ቢጫ፤ ሲከፉ ደግሞ ሰማያዊ ይሆናል ማለት ነው።

የእጅ አምባሩን ተቀጣሪዎች ከቤት ሆነው ሲሠሩ እንዲያደርጉት ይበረታታሉ። ፍቃደኛ ካልሆኑ የማጥለቅ ግዴታ የለባቸውም።

በሳምንት ውስጥ የሚሰማቸውን ስሜት ተከትለው ከሁለቱ ቀለሞች አንዱን ይጫናሉ።

አለቆች በወረርሽኙ ሳቢያ ስለሠራተኞቻው ስሜት ማወቅ አልቻሉም። እናም ከዚህ የእጅ አምባር የሚያገኙት መልዕክት ስለተቀጣሪዎች ስሜት ይነግራቸዋል ተብሎ ይታመናል።

የእጅ አምባሩን ከሰሩት አንዷ ክርስቲና ኮልመር መክሀይ "ቀጣሪዎች ከሠራተኞች ጋር ለመገናኘት እየሞከሩ ነው። ስልክ ሳይደውሉ 500 የሚደርሱ ሠራተኞቻቸው ምን እንደተሰማቸው ለማወቅ የእጅ አምባሩን መጠቀም ይችላሉ" ትላለች።

አምባሩን የመሥራት ሐሳብ የመጣላት ልጇ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚሰማትን የምትገልጽበት መንገድ ስትፈልግ ነው።

እአአ 2016 ላይ ገበያ ላይ የዋለው መሣሪያ፤ በህጻናትና ታዳጊዎች ዘንድ ተፈላጊ ሆኗል። ለቤተሰቦቻቸው መልዕክት ማስተላለፊያ መንገድ አድርገውታል።

ክርስቲና እንደምትለው፤ የእጅ አምባሩን የሚጠቀሙ ሠራተኞች ማንነታቸውን ይፋ ለማድረግ ፍቃደኛነት አሳይተዋል።

መሣሪያውን መጠቀም ከጀመሩ ድርጅቶች አንዱ የዩናይትድ ኪንግደሙ ብሬቭ ማይንድ ነው።

"አንድ ተቀጣሪ የሥራ ጫና በዝቶበት ነበር። እጅግ ተከፍቶም ነበር። ይህንን መረጃ ማግኘት የቻልነው በመሣሪያው አማካይነት ነው" ሲሉ ፓዲ በርት የተባሉ ቀጣሪ ተናግረዋል።

ድብርትና ጭንቀት ዓለም ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከምጣኔ ሀብት አንጻር ሲታይ በዓመት ወደ አንድ ትሪሊዮን ዶላር ገደማ ይገመታል።

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው፤ ወረርሽኙ የአእምሮ ህመምን አባብሷል።

ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የተሠራ ጥናትን እንደ ማሳያ ብንወስድ፤ 60 በመቶ የሚደርሱ አዋቂዎች በበሽታው ሳቢያ የአእምሮ ጤናቸው እንደተቃወሰ ተናግረዋል።

የእጅ አምባር አምራቹ ድርጅት ለተቀጣሪዎች እፎይታ ሊሰጥ እንደሚችል ያምናል።

ሳን ፍራንሲስኮ ውስጥ 'ሞደርን ኸልዝ' የተባለ መተግበሪያ አለ። መተግበሪያው ሠራተኞች በቀላሉ ከአቆቻቸው ጋር እንዲገናኙ የሚረዳ ነው።

የአእምሮ ህክምና እርዳታ የሚፈልጉ ሠራተኞችን ከሥነ ልቦና አማካሪዎች ጋርም ያገናኛል።

በተጨማሪም መሣሪያው የሠራተኞችን የአእምሮ ጤና ሁኔታ ከመዘገበ በኋላ የሚያስፈልጋቸውን የህክምና እርዳታ ያመቻቻል።

የሞደርን ኸልዝ ዋና ኃላፊ አሊሰን ዋትሰን እንደምትለው፤ ብዙዎች ከቤት ሆኖ መሥራት ተጽዕኖ አሳድሮባቸዋል።

በሥራ እና በግል ሕይወት መካከል ያለው መስመር መጥፋቱ ከሚያሳድረው ጫና ለመላቀቅም የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች እየተተገበሩ ይገኛሉ።

ማይክሮሶፍት በቅርቡ ይፋ የሚያደርገው አሠራር፤ በየቀኑ ሥራ ሲያልቅ ሠራተኞች በቀጣይ ቀናት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መዝግበው የሚያሸጋግሩበት ነው።

በተመስጦ ወይም ሜዲቴሽን አእምሯቸውን የሚያፍታቱበት ሥርዓትም ተዘርግቷል።

የማይክሮሶፍት የሥራ ቦታ ቴክኖሎጂ ዋና ኃላፊ ከማል ጃንደን "በሥራ እና በግል ሕይወት መካከል ክፍትተ መፍጠር ይቻላል" ይላል።

የአእምሮ ጤና ላይ የሚሠራው ማይንድ የተባለው ተቋም ኃላፊ ኤማ ማሞ፤ ሠራተኞች ለአእምሮ ጤና ቅድሚያ መስጠት አለባቸው ይላሉ።

ከዚህ በተቃራኒው ቴክኖሎጂን ከመጠን በላይ መጠቀም ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ባለሙያዎች አሉ።

በለንደን ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩት ክሪስ ሮውሊ፤ ሠራተኞች የአእምሮ ህክምና ከፈለጉ ከቴክኖሎጂ ውጤቶች ባሻገር ተገቢው ድጋፍ ሊደረገላቸው እንደሚገባ ያስረዳሉ።

ለምሳሌ ሠራተኞች ድጋፍ ሊያደርግላቸው የሚችል አካል እንዳለ እንዲያምኑ ማስቻልን ይጠቅሳሉ።

ተቀጣሪዎች ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር መገናኘት ሲፈልጉ ወይም ሌላ አይነት ድጋፍ ሲሹ በቀላሉ መገናኘት የሚችሉበት መንገድ ከፈጠሩ መካከል ዮንደርደስክ የተባለው የቴክኖሎጂ ተቋም ይጠቀሳል።