ትራምፕ ለመጨረሻ ጊዜ ዋይት ሃውስን ተሰናብተው ወጡ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በዓለ ሲመት ሊፈፀም በተቃረበበት በአሁኑ ወቅት ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዋይት ሃውስን ተሰናብተው ወጥተዋል።
ለአራት አመት ከኖሩበት ቤተ መንግሥትም በሄሊኮፕተር በመሳፈር አቅራቢያው ወዳለው አንድሪውስ የሚባል ስፍራ ደርሰዋል።
በዚያው አጠር ያለ ንግግር ካደረጉ በኋላም በአየር ኃይሉ አውሮፕላን ተጭነው ወደ ፍሎሪዳ ያቀናሉ።
ከዋይት ሃውስም ሲወጡ አጠር ላለ ጊዜ ከሪፖርተሮች ጋር ያወሩ ሲሆን "ፕሬዚዳንት መሆን ትልቅ ክብር ነው" ማለታቸውንም ሲኤንኤን ዘግቧል።
በዚሁ ሳምንት ማክሰኞ ባደረጉት የመሰናበቻ ቪዲዮ ለቀጣዩ አስተዳዳሪ አሜሪካውያን እንዲፀልዩ ቢጠይቁም ስም ከመጥራት ግን ተቆጥበዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በባለፉት አራት አመታት ባከናወኗቸው ተግባራት ከፍተኛ ኩራት እንደሚሰማቸው የገለፁት ትራምፕ በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ ሰላም በማምጣትና በአስርት አመታትም አገራቸው ጦርነት ውስጥ እንዳትሳተፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
የተከታያቸውን በዓለ ሲመት ባለመካፈልም ከአውሮፓውያኑ 1869 በኋላ የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት ሆነዋል።
ጆ ባይደን ቃለ መሃላቸውንም በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት አካባቢ በቅርቡ ነውጥና ሁከት ባስተናገደው በዋሽንግተኑ ካፒቶል ሂል የሚፈፅሙ ይሆናል።
የበዓለ ሲመቱንም ዝግጅት ደህንነትና ፀጥታ ለመቆጣጠር ከብሔራዊ ዘብ የተውጣጡ 25 ሺህ ሰራዊት ሰፍሯል።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝም ምክንያት እንደ ወትሮው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ታዳሚዎች አይሳተፉም።
ከጆ ባይደንም በተጨማሪ የሴት ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን በአሜሪካ ዘንድ ታሪክ የሰራችው ካማላ ሃሪስም ቃለ መሃላዋን ትፈፅማለች።
ተመራጩ ፕሬዚዳንት ስልጣናቸውንም በይፋ ከመቆናጠጣቸው በፊት ሊያከናውኗቸው የሚገቡ አስራ አምስት ተግባራትን በዚሁ ሳምንት አስታውቀዋል።
ከነዚህም መካከል የአየር ንብረት ለውጥ፣ እኩልነት፣ የስደተኞች ጉዳይና ኮሮናቫይረስ ተጠቃሽ ናቸው።
ከዚህም በተጨማሪ በመጀመሪያ ቀናቸው አወዛጋቢ የሆነውን ኪስቶን ኤክስ ኤል የተባለውን የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ፕሮጀክት እንደሚሰርዙ የአሜሪካ ሚዲያዎች ሪፖርት አድርገዋል።
የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧው ፕሮጀክት አልሞ የነበረው የካናዳዊቷን ግዛት አልበርታንና የአሜሪካን ኔብራስካን ግዛትን የሚሸፍን 1 ሺህ 900 ኪሎሜትር እርዝማኔ እንዲኖረው ታቅዶ ነበር።
የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች እንዲሁም ቀደምት አሜሪካውያን ይህ ፕሮጀክት እውን እንዳይሆን ለአስር አመታት ያህል ታግለዋል።