ትግራይ፡ የትግራይ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደና ጓደኛው በመቀለ ከተማ ተገደሉ

ዳዊት ከበደ አርአያ
የምስሉ መግለጫ,

ዳዊት ከበደ አርአያ

የትግራይ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ የነበረው ዳዊት ከበደ አርአያ ወደ ሥራው ከተመለሰ ከቀናት በኋላ በመቀለ ከተማ ውስጥ ተገድሎ መገኘቱ ተዘገበ ።

የሥራ ባልደረቦቹ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የትግራይ ክልላዊ መንግሥት በሚያስተዳድረው ቴሌቪዥን ጣቢያ በጋዜጠኝነት ይሰራ የነበረው ዳዊት ተገድሎ የተገኘው ረቡዕ ዕለት ጥር 12/ 2013 ዓ.ም በመኪና ውስጥ ነው።

ከዳዊት ከበደም አርአያ በተጨማሪ አንድ ሌላ ጓደኛውም መቀሌ ውስጥ በምትገኝ አዲ ሃውሲ በምትባል ሰፈር መገደላቸውን ባልደረቦቹ ተናግረዋል።

የቀይ መስቀል ሠራተኞች የዳዊትንና አብሮት የነበረውን ግለሰብ አስከሬን ካነሱ በኋላ በትግራይ ቴሌቪዥን ለሚሰሩ የሥረራ ባልደረቦቹ ማሳወቃቸውም ተጠቅሷል።

ስለ ግድያው እስካሁን ድረስ ክልሉን ከሚያስተዳድሩት ባለስልጣናት የተሰጠ መረጃ የለም።

አዲስ በተቋቋመው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የደኅንነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ዋልታ ሐረጎትን ስለ ጋዜጠኛው አሟሟት ቢቢሲ በጠየቃቸው ወቅት ምንም መረጃ እንደሌላቸውና፤ መረጃዎችን ሰብስበውና አጠናቅረው ይፋ እንደሚያደርጉም ቃል ገብተዋል።

ስሜ አይጠቀስ ያለ አንድ የዳዊት የሥራ ባልደረባ ለቢቢሲ ትግርኛ እንደተናገረው ሁለቱ ግለሰቦች የተገደሉት በተተኮሰባቸው ጥይት ነው። ይህንን መረጃ ከአካባቢው የፀጥታና ደኅንነት ኃላፊዎች ማረጋገጥ አልተቻለም።

ሁለተኛው የተገደለው ግለሰብ ማንነትንም በተመለከተ ቢቢሲ ባደረገው ማጣራት በትግራይ ቴሌቪዥን የሚሰራ ሌላ ጋዜጠኛ ወንድም መሆኑን መረዳት ችሏል።

ወደ ራ መመለስ

በትግራይ ክልል ወታደራዊ ግጭት በተፋፋመበት በኅዳር ወር ሥራ አቋርጦ እንደነበር የተነገረው ዳዊት ከበደ አርአያ በቅርቡ ወደ ሥራው ተመልሶ ነበር ተብሏል።

የመከላከያ ሠራዊት መቀለን መቆጣጠሩን ተከትሎ ተቋርጦ የነበረውም የክልሉ ቴሌቪዥን ፕሮግራም ስርጭት መተላለፍ የጀመረ ሲሆን ሠራተኞቹም ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ጥሪ አድርጓል።

ዳዊት ወደ ሥራ ተመልሶ ቢሮ በገባበት ወቅት ተይዞ ለቀናትም ያህል በቁጥጥር ስር የነበረ መሆኑን አንድ በቴሌቪዥን ጣቢያ የሥራ ባልደረባው አሳውቀዋል።

እስሩን በተመለከተ የአካባቢው ባለስልጣናት ያሉት ነገር ባይኖርም የሥራ ባልደረባው ግን ከመገደሉ በፊት ለሦስት ቀናት በእስር ላይ እንደነበረ ተናግረዋል።

"የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳዳሪዎች የቀድሞ ጋዜጠኞችንና የካሜራ ባለሙያዎችን እያናገሩ ነበር። ካናገሩዋቸው ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ዳዊት ነው" በማለትም ባልደረባው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከህዳር 19/2013 ዓ.ም ጀምሮ በመከላከያ ቁጥጥር ስር ባለችው መቀለ የምሽት ሰዓት እላፊ የተጣለ ሲሆን በዚያ ሰዓትም በከተማው ማንኛውም እንቅስቃሴ የተከለከለ ነው።

ዳዊት ከበደ አርአያ ማን ነው?

ዳዊት በትግራይ ቴሌቪዥን ተቀጥሮ ከመስራቱ በፊት ለበርካታ ዓመታት በብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ ኢቲቪ ሰርቷል።

ኢቲቪን ከለቀቀ በኋላ የራሱን የትግርኛ መፅሔት በማቋቋም ለበርካታ ዓመታት ፅሁፍ ሲያበረክት ነበር።

በኋላም ባለፈው ዓመት እስከ ተዘጋበት ድረስ አዲስ አበባ በሚገኘው የትግራይ ቴሌቪዥን ቅርንጫፍ ውስጥ እያገለገለ ነበር።

የአዲስ አበባ ቅርንጫፉን መዘጋት ተከትሎ መቀለ ወደሚገኘውም ዋና ጣቢያ በመመለስ በቴሌቪዥን ጣቢያው ሲሰራ ነበር።

የሁለቱ፣ የዳዊትና አብሮት የነበረው ግለሰብ የሥርዓተ ቀብር በትናንትናው ዕለት ጥር 12/ 2013 ዓ.ም አቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል።