ኮሮናቫይረስ፡ በሜክሲኮ ሆስፒታል የኮቪድ-19 ክትባቶች ተሰረቁ

የኮሮናቫይረስ ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሜክሲኮዋ ሞሬሎስ ግዛት በሚገኝ ሆስፒታል የኮቪድ-19 ክትባቶች ተሰርቀዋል ተብሏል።

ይህንንም ተከትሎ የአገሪቱ ጦር ምርመራ ከፍቷል።

ሜክሲኮ ይህንንም ስርቆት ለመመርመርና ጥፋተኞቹንም በቁጥጥር ስር ለማዋል በመላው አገሪቷ ጦሯን አሰማርታለች።

በዋናነትም በአገሪቷ አድራጊና ፈጣሪ ከሆኑት የማፊያ ቡድን እጅ ክትባቶቹም እንዳይገባ ስጋት ስለፈጠረም ነው ሰራዊቱ የተሰማራው።

"ስርቆቱ ምናልባት የተፈፀመው ታማኝ ባልሆነ የሆስፒታሉ የክትባት ቡድን አባል ሊሆን ይችላል" የሚል መግለጫም ከመንግሥት በኩል ወጥቷል።

የተዘረፈው የክትባት መጠን አልተጠቀሰም።

ሜክሲኮ 129 ሚሊዮን ህዝቦቿን በነፃ ክትባት ለመክተብም ቃል ገብታለች።

በአለም አቀፍ ደረጃ በወረርሽኙ ክፉኛ ከተጠቁ አገራት አንዷ የሆነቸው ሜክሲኮ 140 ሺህ ዜጎቿንም በቫይረሱ አጥታለች። ይህም አሃዝ ከአለም አራተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዜና በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ሶኖራ በምትባለው ግዛት ታጣቂዎች አንድ ሆስፒታል ውስጥ በመግባት ለኮሮናቫይረስ ህሙማን የሚውል የማገዣ መሳሪያ መተንፈሻ (ኦክስጅን) መዝረፋቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በዘገባው አስነብቧል።

ዘራፊዎቹ በሆስፒታሉ ሰራተኞች ላይ ጥይት ከደገኑ በኋላ ኦክስጅኑ የት እንደሚቀመጥ ጠይቀዋቸዋል። በመቀጠልም ሶስት ኦክስጅን የተሞላበት መሳሪያና አራት የኦክስጅን ማስቀመጫን ይዘው ሄደዋል ተብሏል።

በአገሪቱ ውስጥ የኦክስጅን ስርቆት በሌላለ አካባቢም እንዲሁ የተከሰተ ሲሆን በቅርቡም የተሰረቀ 44 የኦክስጅን መሳሪያዎችን የያዘ የከባድ ጭነት መኪና ሜክሲኮ ከተማ አቅራቢያ ተይዟል።

በርካታ ዜጎች ህሙማን ቤተሰቦቻቸውን በየቤቶቻቸው እንዲያቆዩ በተገደዱበት ወቅት የማገዣ መሳሪያ መተንፈሻ (ኦከስስጅን)ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። አገሪቷ ባጋጠማት ከፍተኛ የኮሮናቫይረስ ህሙማንም ቁጥር ሆስፒታሎች ሞልተዋል።