የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ሐሰተኛ መረጃዎችን ለሚያሰራጩ ማስጠንቀቂያ ሰጠ

የፎቶው ባለመብት, NISS
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሐሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ህብረተሰቡን ለማደናገር የሚሞክሩ የማህበራዊ ሚድያ አንቂዎች ከሕገ-ወጥ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳሰቧል።
ኤጀንሲው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ ከሰሞኑን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብታቸውን ያላግባብ ተጠቅመው ሃሰተኛ መረጃዎችን በማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው በማሰራጨት ህብረተሰቡን ለማደናገር ሲሞክሩ የነበሩ የማህበራዊ ሚድያ አንቂዎች ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል ብሏል።
ይህ የአጄንሲው መግለጫ የወጣው የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ደህንነትን በማስመልከት በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ ያልተረጋገጡ መረጃዎችን ተከትሎ ነው።
"ከዚህ በኋላ የሐሰት መረጃዎችንና አሉባልታዎችን በማህበራዊ ትስስር ገጾች በማሰራጨት የሀገርን ብሔራዊ ጥቅምና ህልውና ለመጉዳት እንዲሁም የህዝብን ሰላምና ደህንነት ስጋት ላይ ለመጣል የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ማስረጃዎችን በማጠናቀር በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እንደሚያደርግ ያስታውቃል" ይላል የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መግለጫ።
በተመሳሳይ የጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ አሕመድ ቢሮ የጠቅላይ ሚንሰትሩን ደህንነት በማስመልከት በማሕበራዊ ሚዲያዎች የተሰራጨው መረጃ ሐሰት ነው ማለቱ ይታወሳል።
"የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ደህንነት አስመልክቶ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው ወሬ የሀሰት እንደ ሆነ ሁሉም ሰው እንዲገነዘብ ለማሳሰብ እንወዳለን" ይላል በጠ/ሚንሰትሩ ጽ/ቤት የፌስቡክ ገጽ ላይ የወጣጠው አጭር መግለጫ።
ገዢው ብልጽግና ፓርቲም የጠቅላይ ሚንስትሩን "ጤንነትና ደህንነት አስመልክቶ በማህበራዊ ሚዲያ የተናፈሰው ወሬ ፍጹም መሰረተ ቢስና ሆን ተብሎ ህብረተሰቡን ለማደናገር" የተሰራጨ ሐሰት መረጃ ነው ብሏል።
የፎቶው ባለመብት, PMO
ጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ አሕመድ
ጠ/ሚ ዐብይ በይፋ ለመጨረሻ ጊዜ የታዩት መቼ ነው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ለሳምንታት በይፋ አለመታየታቸው በበርካቶች ዘንድ አነጋጋሪነቱን እየጨመረ የመጣ ክስተት ሆኖ ቀጥሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ለመጨረሻ ጊዜ ለሕዝብ የታዩት መቼ ነው የሚለው በራሱ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሰዎችን እያነጋገሩ ካሉ ጉዳዮች አንዱ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመጨረሻ ጊዜ ለሕዝብ የታዩት እና ንግግር ያደረጉት ወይም ደግሞ ንግግር ሲያደርጉ የታዩት ማክሰኞ ታሕሳስ 13፣ 2013 ዓ.ም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ከነዋሪዎች ጋር በተወያዩበት ጊዜ ነበር።
በተመሳሳይ ቀን በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የተካሄደውን የሚኒስትሮች ስብሰባ መምራታቸውንም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እና በትዊትር ገጽ ላይ ሰፍሮ ይታያል።
ነገር ግን ጥር 4 2013 ዓ.ም የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ደቡብ ክለል ተጉዘው የኮይሻን ፕሮጀክት ጎብኝተዋል የሚል በምስል የተደገፈ ዜና አቅርበዋል።
በዚህ ጊዜ የጠቅላይ ሚኒስትሩ በአደባባይ አለመታየት መነጋገሪያ መሆኑን ጨምሮ ስለነበር፣ መንግሥትን የሚደግፉ አክቲቪስቶች ይህንን እንደማስረጃ በመጥቀስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቢሯቸው ስራ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው ጽፈዋል።
ይኹን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተንቀሳቃሽ ምስል በመገናኛ ብዙኀን ላይ ቀርበው የታዩት በመተከል ዞን ከነዋሪዎች ጋር ሲወያዩ ቢሆንም በማህበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው ማለትም፤ በትዊትር እና ፌስቡክ፣ በተለያዩ ጊዜ የተለያዩ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ ቆይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፈረንጆቹን አዲስ አመት፣ ገናን እና ጥምቀትን በማስመልከት የመልካም ምኞት መግለጫዎችን ተላልፈዋል።
በዛሬው ዕለትም በኦሮሚያ እና በሶማሊያ ክልሎች ድንበር አካባቢ ስለሰፈን ሰላም በማንሳት የሁለቱ ክልሎች መሪዎች ስለሰሩት ስራ አመስግነው በግል የትዊተር ሰሌዳቸው ላይ ጽፈዋል።
የእንግሊዙ የውጪ ገዳይ ሚኒስትር ጉብኝት
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅርበት ያላቸው ባለስልጣናትና ግለሰቦች ጠቅላይ ሚንስትሩ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ እና በስራ ገበታቸው ላይ እንዳሉ በማህበራዊ ሚዲያዎቻቸው ላይ ሲገልፉ ቆይተዋል።
በዚሁ መካከል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዶምኒክ ራብ ለሥራ ጉብኝት ጥር 14 2013 ዓ.ም ኢትዮጵያ መግባታቸው ይታወሳል።
ለእንግሊዙን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር አቀባበል ያደረጉት እንዲሁም ከባለስልጣኑ ጋር ውይይት ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ስለመሆናቸው በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው ተዘግቧል።
ነገር ግን ዶምኒክ ራብ በትዊትር ሰሌዳቸው ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር እንደተገናኙ እና እንደተመካከሩ ጽፈዋል።
ዶሚኒክ ራብ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጋር ስለኮሮናቫይረስ፣ በቀጠናዊ ፀጥታ፣ ስለ አየር ንብረት ለውጥና በትግራይ ክልል ስለሚቀርበው የሰብዓዊ እርዳታ እና ሌሎች ጉዳዮች የነበራቸው ውይይት ፍሬያማ እንደሆነ ጠቅሰው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይን አመስግነዋል።
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ደህንነት ላሳሰባቸው ሰዎች መልካም ዜና ቢሆንም ሲወያዩ አለመታየታቸውና የመገናኛ ብዙኀን ሽፋን አለማግኘታቸውን ግን ጥርጣሬን አጭሯል።
የሁለቱ ባለስልጣናት መገናኘትና መወያየት የተገለጸው በዶምኒክ ራብ የትዊተር ሰሌዳ ላይ ብቻ ነው።