ኮሮናቫይረስ፡ የላቲን አሜሪካው ቁጥር-1 ቢሊዮነር በኮቪድ ተያዙ

ካርሎስ ስሊም

የፎቶው ባለመብት, Gety Images

በመላው ላቲን አሜሪካ የናጠጡ ሀብታም የሚባሉት ካርሎስ ስሊም በኮቪድ ተህዋሲ መያዛቸው ታወቀ፡፡

የ80 ዓመቱ ቢሊዮነር ካርሎስ ሜክሲኳዊ ሲሆኑ በቴሌኮሚኒኬሽን ቢዝነስ እውቅ ናቸው፡፡

ለጊዜው መጠነኛ የኮቪድ ምልክቶችን ብቻ እያሳዩ ነው ተብሏል፡፡

ልጃቸው በትዊተር ሰሌዳው እንደጻፈው ‹አባቴ ደህና ነው አታስቡ› ብሏል፡፡

የቢሊየነሩ በኮቪድ መያዝ ዜና የተሰማው የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት የ67 ዓመቱ አንድሬስ ማኑል ሎፔዝ ኦብራዶር በኮቪድ መያዛቸውን ተከትሎ ነው፡፡

ሜክሲኮ ከዓለም አገራት ክፉኛ በኮቪድ ከተጎዱ አገራት ተርታ የምትመደብ ናት፡፡

ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች በተህዋሲው የተያዙ ሲሆን 150ሺህ ዜጎች ደግሞ ሕይወታቸው በዋዛ አልፏል፡፡

ዛሬ ሰኞ የካርሎስ ስሊም ልጅ ዶሚት ካርሎስ ስሊም እንደጻፈው ‹አባቴ ለአንድ ሳምንት መጠነኛ ምልክቶችን ካሳየ በኋላ አሁን ሻል እያለው ነው፤ ለውጥ አለው›› ብሏል፡፡

ቢሊየነሩ ካርሎስ ስሊም ዋንኛውን የሜክሲኮ የቴሌኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ፣ ሞቪል ኩባንያን በባለቤትነት ያስተዳድራሉ፡፡

ፎርብስ መጽሔት የዚህ ቴሌኮም ኩባንያቸው ግምት 52 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል ሲል ገምቶታል፡፡

ሜክሲኮ አሁን ወረርሽኙ በከፍተኛ ሁኔታ በመስፋፋቱ በዋና ከተማዋ ሜክሲኮ ሲቲ ሆስፒታሎች እየሞሉ ነው ብሏል በሜክሲኮ የቢቢሲ ዘጋቢ ዊል ግራንት፡፡

የኮቪድ ተህዋሲ ያገኛቸውና አሁን ከቤታቸው ሆነው ሥራ እየሠሩ ያሉት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሎፔዝ ኦብራዶር የሩሲያ ሠራሹን ስፑትኪን ክትባትን ወደ አገራቸው ለማስገባት ከፑቲን ጋር እንደተነጋገሩ ተዘግቧል፡፡

በዚህም መሠረት 24 ሚሊዮን ጠብታዎች በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ሜክሲኮ ይደርሳሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡