ትግራይ፡ ተመድ እና ኤንአርሲ በትግራይ ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው አሉ

በትግራይ ክልል ስለሚያስፈልገው ሰብአዊ እርዳታ ምን ተባለ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር እና የኖርዌጂያን ሪፊዉጂ ካውንስል ዋና ጸሐፊ በትግራይ ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው አሉ።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ በትግራይ ያደረጉትን ጉብኝነት ሲያጠናቅቁ በክልሉ ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው ሲሉ መግለጫ ሰጥተዋል።

በተመሳሳይ የኖርዌጂያን ሪፊውጂ ካውንስል (ኤንአርሲ) ዋና ጸሓፊ ጃን ኢግላንድ በትግራይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች በበቂ ሁኔታ ድጋፍ እያገኙ አይደለም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

መንግሥት በበኩሉ ለተፈናቃዮች የሚያስፈልገውን እርዳታ ለማቅረብ አቅሙ እና ዝግጁነቱ አንዳለው ከዚህ ቀደም አስታውቋል።

ጃን ኢግላንድ "ባለፉት ሦስት ወራት ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች ዘላቂነት ያለው እርዳታ መስጠት አልቻሉም። ወደ 2 ሚሊዮን ሰዎች ገደማ አፋጣኝ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ብዙ የሰብአዊ እርዳታ ሰጪዎች ገብተዋል የሚባለው እውነት አይደለም። በተለይ በምዕራብና ማዕከላዊ ትግራይ ሰዎችን መድረስ አልቻልንም። እርዳታ መስጠት የተቻለው በመቀሌ ዋና ጎዳና ለሚገኙ እና በፌደራል መንግሥት ቁጥጥር ሥር ባሉ አካባቢዎች ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግራል።

ከወራት በፊት በሕወሓት ኃይሎች እና በፌደራሉ መንግሥት መካከል በተከሰተው ግጭት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማስታወቁ ይታወሳል።

የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ ትናንት በሰጡት መግለጫ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ሳይሆኑ የሰብዓዊ እርዳታ ሊደርሳቸው ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

ኮሚሽነሩ በኢትዮጵያ በነበራቸው ጉብኝት ጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ አሕምድን ጨምሮ ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር መገናኘታቸውን ገልጸዋል።

የሰላም ሚንስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ከኮሚሽነሩ ጋር ወደ ትግራይ መጓዛቸውን በፌስቡክ ገጻቸው ላይ አስፈረዋል።

ወ/ሮ ሙፈሪያት ተፈናቃይ ዜጎችን ከፊሊፖ ግራንዲ ጋር መጎብኘታቸውን ገልጸው “መሻሻል ያለባቸው የመሰረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ . . . ከተወካዮች ጋር ተወያይተናል። አገልግሎታችንን የበለጠ ለማሻሻል እንድንችል ከባለጉዳዮቹ ያሉ አዎንታዊ አፈፃፀሞችና ጉድለቶችን ለመረዳት እድሉን አግኝቻለሁ” ብለዋል።

ፊሊፖ ግራንዲኒ በበኩላቸው በጎበኟቸው በስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ያገኟቸው ስደተኞች ጾታዊ ጥቃቶች እንደደረሱባቸው ሪፖርት እንዳደረጉላቸው ተናግረው በአሁኑ ወቅት ጾታን መሠረት ያደረጉት ሪፖርቶችን በአሃዝ ማስቀመጥ እንደማይቻል ገልጸዋል።

ግራንዲ፤ መንግሥት ተፈጽመዋል የሚባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰተኞችን በገለልተኝነት አጣርቶ ጥፋተኞችን ተጠያቂ እንዲያደርግ እና የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ምንም አይነት ክልከላዎች እንዳይኖሩ ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል የሰላም ሚንስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት፤ “ከሚመለከታቸው ጋር ሆነን መልካም ተሞክሮዎቻችንና አቃፊ እሴቶቻችንን ይበልጥ እያጠናከርን ወገኖቻችን ያሉባቸውን ችግሮች ለማቃለል እንደሁልጊዜውም ሌት ተቀንእንተጋለን” ብለዋል።

“ሰዎችን መድረስ አልቻልንም”

የኖርዌጂያን ሬፊውጂ ካውንስል ዋና ጸሐፊ ጃን ኢግላንድ ትናንት ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ የሰብዓዊ ድጋፍ የሚሹ ሰዎችን ለመድረስ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም እርዳታ የሚሹ ሰዎችን መድረስ አለመቻላቸውን ተናግረዋል።

“ሰዎችን መድረስ እንድንችል በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበናል። አንዳንዴ በፌደራል አንዳንዴ በክልል ደረጃ ፍቃድ ያላገኘንባቸው ወቅቶች አሉ። እርዳታ የሚፈልጉት ሰዎች ከሁለት ሚሊዮን በላይም ሊሆኑ ይችላሉ። አናውቅም። ድህነት የተንሰራፋበትና እርዳታ የሚፈልግ አካባቢ ነው” ሲሉ ተናግራል።

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል እርዳታ የሚሹ ሰዎች ቁጥር 2.5 ሚሊዮን መሆኑን እና ለእነዚህምዜጎች አስፈላጊ የሆነ እርዳታ ለማድረስ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ሲያስታውቅ ነበር። የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራአመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ፤ "በትግራይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውሰዎች ቁጥር 4.5 ሚሊዮን ሳይሆን 2.5 ሚሊዮን ነው" ብለዋል።

ኮሚሽነሩ፤ 2.5 ሚሊዮን ሕዝብ ለመርዳት መንግሥት በቂ ዝግጅት አድርጓልም ብለዋል።

ጃን ኢግላንድ ግን “ጥቂት የጭነት መኪናዎችና እርዳታ ሰጪዎች እንዳሉ እንገነዘባለን። ያ ግን በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች በቂ ተደራሽ አይሆንም” ይላሉ።

“ሰብአዊ አርዳታ ሰጪዎችና መንግስት በጋራ ባደረጉት ግምገማ ወደ ምስራቅና ደቡባዊ ትግራይ ተጉዘዋል። ብዙ እርዳታ የሚፈልጉ እንዳሉ ታይቷል። የኖርዌጅያን ሬፊዩጂ ካውንስልን ጨምሮ ሌሎችም ድርጅቶች እርዳታ መስጠትይሻሉ። ከግጭቱ በፊት በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች እርዳታ ሰጥተናል። አሁን ደግሞ ከዚህም በላይ ለማድረግዝግጁ ነን።”

ጃን ኢግላንድ በትግራይ ክልል ከሚገኙ አራት ኤርትራውያን ከሚገኙባቸው መጠለያ ጣቢያዎች በሁለቱ እርዳታ ቁሶችን ማቅረባቸውን ይሁን እንጂ የተቀሩት ሁለት መጠለያ ጣቢያዎች መድረስ አለመቻላቸው እንዳሳሰባቸው ለቢቢሲተናግረዋል።

“ሁለት ካምፖች ውስጥ ለኤርትራውያን መጠነኛ እርዳታ ማድረግ ተችሏል። በኤርትራውያኑ ዘንድ የእርዳታ ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው። ሁለት ካምፖችን ግን መድረስ አለመቻሉ እጅግ ያሳስባል። የሰብዓዊ መብትና ግጭትን የተመለከቱ ዓለም አቀፍ ሕግጋት ጥሰት እንዳሉ ሪፖርቶች ደርሰውናል። ስደተኞች ጥቃት እንደደረሰባቸው ሰምተናል። ወደ ኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ሄጄ በርካታ ስደተኞች አግኝቻለሁ። አሰቃቂ ታሪኮች ነው የነገሩኝ።"