'ስሜ ጠፍቷል' ሲሉ የአውስትራሊያ ሚድያዎችን የከሰሱት ቻይናዊ ቢሊዬነር ረቱ

ዶ/ር ቻው ቻክ ዊንግ

የፎቶው ባለመብት, ABC

የምስሉ መግለጫ,

ዶ/ር ቻው ቻክ ዊንግ

ስሜን አጥፍታችኋል ሲሉ ሁለት የአውስትራሊያ መገናኛ ብዙሃንን የከሰሱት ቻይናዊ አውስታራሊያዊው ቢሊዬነር አሸንፈዋል።

ቢሊዬነሩ መገናኛ ብዙሃኑ ያለስሜ ስም ሰጥተውኝ ቻይናዊ ሰላይ ነው ብለውኛል ሲሉ ነበር የከሰሱት።

ዶ/ር ቻው ቻክ ዊንግ የተባሉት ነጋዴና የበጎ ምግባር ሰው በ2017 ነው ሰሜ ጠፍቷል የሚሉት።

ፍርድ ቤቱ ኤቢሲ የተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ የሰውዬውን ስም አጥፍቷል፤ ነገር ግን ሆን ብሎ ሰላይ ናቸው የሚል ስም አልሰጣቸውም ሲል በይኗል።

ኤቢሲ እና ናይን ኢንተርቴይንመንት የተሰኙት ተቋማት ውሳኔው የሚድያ ነፃነትን የሚጋፋ ነው ሲል ተደምጠዋል።

ሁለቱ የሚድያ ተቋማት ላደረሱት ጥፋት 590 ሺህ የአውስትራሊያ ዶላር [450 ሺህ የአሜሪካ ዶላር] ለዶ/ር ቻው እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል።

በአውስትራሊያዊያን ዘንድ በእርዳታቸው የሚታወቁት ዶ/ር ቻው ጠበቆች በውሳኔው መደሰታቸውን አሳውቀዋል።

ጠበቃዎቹ የደንበኛቸው ስም በጋዜጠኞች 'መሠረት በሌለው ሐሳብ' ጥቃት ደርሰቦት እንደነበር ተናግረው አሁን ግን ስማቸው ነፃ መሆኑ እንዳስደሰታቸው አሳውቀዋል።

የሰውዬው ክስ ሰፊ ሽፋን ሊያገኝ የቻለው ቻይናና አውስትራሊያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ያላቸው ግንኙነት እየሻከረ መምጣቱን ተከትሎ ነው።

ሰውዬው ስማቸው ጠፋ የተባለበት የቴሌቪዥን ፕሮግራምና የፅሑፍ ሃተታ ኤቢሲ በተሰኘው ጣቢያ ላይ የተላለፈ ነው።

ፕሮግራሙ አውስትራሊያ ውስጥ ያሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎችን የሚዳስስ ሲሆን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰው ተከታትሎታል።

ቢሊዬነሩ ሁለቱን የሚድያ ድርጅቶች የከሰሱት የቴሌቪዥን ፕሮግራሙ ከተላለፈ በኋላ ባሉት ቀናት ነበር።

በክሳቸው ላይ ፕሮግራሙ እሳቸውን ልጅ የቻይና ሰላይ አድርጎ እንደሳላቸውና ሃገሩን የከዳ እንዳስመሰላቸው ጠቅሰዋል።

የአውስትራሊያ ዜግነት ያላቸው ቢሊዬነሩ ክሳቸውን ሲያብራሩ በገንዘቤ ፖለቲከኞች በመግዛት ተፅዕኖ ለመፍጠር እንደሞከርኩ ተደርጌ ነው የቀረብኩት ሲሉ ወቅሰዋል።

ኤቢሲ የተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ምንም እንኳ ጥርጣሬ የሚጭር ነገር ቢኖርም ተመልካቹ ግን ይህን መለየት አያቅተውም ሲል ተከራክሯል።

ነገር ግን ፍርድ ቤቱ የቴሌቪዥን ጣቢያውን መከራከሪያ ውድቅ በማድረግ የሰውዬው ስም ጠፍቷል ሲል በይኗል።

አልፎም ፍርድ ቤቱ ቴሌቪዥን ጣቢያው የበሊዬነሩ ስም የጠፋበትን ፕሮግራም ከበይነ መረብ ማከማቸው ላይ እንዲያነሳ ብይን አስተላልፏል።

ቢሊዬነሩ ዶ/ር ቻው በፈረንጆቹ 2019 በተመሳሳይ የስም ማጥፋት ወንጀል ሲድኒ ሞርኒንግ ሄራልድ የተሰኘውን ጋዜጣ ከሰው 280 ሺህ የአውስትራሊያ ዶላር ክስ እንዲከፈላቸው ተበይኖላቸዋል።

የአውስትራሊያ መገናኛ ብዙሃን የስም ማጥፋት ጉዳይ የሚድያ ነፃነትን የሚጋፋ ነው ሲሉ አምርረው ይከራከራሉ።