ሩስያ የአሜሪካ ሰላዮችን በሚስጥር እየመረዘች ይሆን?

ማርክ ፖሊምሮፖለስ
የምስሉ መግለጫ,

ማርክ ፖሊምሮፖለስ

ማርክ ፖሊምሮፖለስ ካረፈበት ሆቴል አልጋ ላይ ራሱን ሲያገኘው ጭንቅላቱን አከባቢ አንዳች ንዝረት ይሰማው ነበር። ጆሮው ደግሞ ይሞዝቃል።

"ሽቅብ ሽቅብ ሲለኝ የማስመልስ መስሎኝ ነበር። መነሳት ሁላ አቅቶኝ ነበር" ሲል ያን ምቾት የነሳውን ጠዋት ያስታውሳል።

"ብዙ ጊዜ በጥይት ተመትቻለሁ። ይሄኛው ግን በጣም አስፈሪ ነበር።"

ማርክ ኢራቅ ውስጥ ለዓመታት አገልግሏል። ሶሪያና አፍጋኒስታን ውስጥም የአሜሪካው ስለላ ድርጅት ሲአይኤ መኮንን ሆኖ ሽብርተኝነትን ተዋግቷል።

ነገር ግን ያቺ በሞስኮው ያሳለፋት ምሽት የተለየች ናት። ምስጢራዊ በሆነ 'ማይክሮዌቭ' መሣሪያ ጥቃት ሳይደርስበት እንዳልቀረ ይጠረጥራል።

ሩስያ በአሜሪካ የ2016 ምርጫ ጣልቃ ገብታለች መባሉን ተከትሎ ሲአይኤ እንደ ማርክ ያሉ አሉኝ የሚላቸውን መኮንኖቹን አሰማርቶ ነበር።

ማርክ፤ በአውሮፓና በዩሬዥያ [አውሮፓና እስያ] ኃላፊ ሆኖ ከአሜሪካ አጋሮች ጋር የሩስያን ሥራ የማጋለጥ ሥራ መሥራት ጀመረ።

በፈረንጆቹ 2018 የቀድሞው የሩስያ ሰላይ ሰርጌ ስክሪፓል እንግሊዝ ውስጥ በሩስያ መመረዙን ከመረመሩ ሰዎች መካከል አንዱ ማርክ ነበር።

ታኅሣሥ 2017 [በፈረንጆቹ] ማርክ ወደ ሩስያ ዋና መዲና ሞስኮ አቀና። ነገር ግን ጉዞው ኦፌሴላዊ እንጂ ድብቅ አልነበረም።

የጉዞው ዓለም የአሜሪካና ሩስያ ሰላዮች የሚያደርጉትን ስብሰባ ታኮ ሩስያን መጎብኘት ነበር። 'ወደ ሞስኮ ያቀናሁት ለስለላ አልነበረም' ሲል ያስረግጣል፤ ማርክ።

ሩስያዊያውን ግን የማርክ ወደ ሞስኮ ብቅ ማለት አልተዋጠላቸውም።

ይሄኔ ነው ማርክ ካረፈበት ሆቴል አልጋ ላይ ራሱን እያጥወለወለው ያገኘው። ወደ አሜሪካ ሲመለስ የማጥወልወል ስሜቱ ጋብ ቢልለትም ሌሎች የሕመም ስሜቶች ግን ይታዩበት ነበር።

"ለሶስት ዓመታት ያክል 'ማይግሪን' [ከባድ ራስ ምታት] ነበረብኝ። በፍፁም ሊለቀኝ አልቻለም" ሲል ማርክ ለቢቢሲ ይናገራል።

በዚህም ምክንያት ለበርካታ ወራት ሥራውን ትቶ ሐኪም ቤት መመላለስ የለተ'ለት ተግባሩ ሆነ።

ማርክ ሩስያ ሳለ በማይክሮዌቭ መሣሪያ ተጠቅቶ ሊሆን እንደሚችል የገመተው የአሜሪካና የካናዳ ዲፕሎማቶች ወደ ኩባዋ ከተማ ሃቫና አቅንተው ተመሳሳይ ነገር እንደገጠማቸው ሪፖርት በማድረጋቸው ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

በኩባ ሃቫና የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ

'ሃቫና ሲንድረም'

ማርክ፤ አሜሪካዊያን ዲፕሎማቶች ኩባ ውስጥ የገጠማቸው ነገር እኔም ሩስያ ውስጥ ገጥሞኛል ብሎ ያምናል።

ማርክና ሌሎች ይህ ጉዳይ የገጠማቸው ሰዎች የሚሰማቸው ሕመም 'ሃቫና ሲንድረም' የተሰኘ ስያሜ ተሰጥቶታል።

ይህ የሕመም ስሜት በተለያዩ ሰዎች ላይ የተለያየ መልክ ይዞ ይመጣል። አንዳንድ ጊዜ ይህ ሕመም ስነ-ልቡናዊ ነው ተብሎ ይታመናል።

ማርክ ሕመሙ እንደተሰማው በሲአይኤ ሐኪሞች ተመርምሮ ነበር። ነገር ግን ከሃቫና ሲንድረም ጋር ግንኙነት የለውም ብለው ውድቅ አድርገውት ነበር። ማርክ ሐኪሞች ጉዳዩን ሲያጣጥሉበት ቅሬታ ተሰምቶት ነበር።

የሲአይኤ ቃል አቀባይ የሆኑ ሰው "የድርጅታችን የመጀመሪያው ኃላፊነት የመኮንኖቻችን ደኅንነት ነበር፤ ወደፊትም እሱ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ማርክ 2019 ላይ በሕመሙ ምክንያት ከሲአይኤ ሥራው እንዲገለል በመደረጉ ነው ማንነቱን ይፋ አድርጎ ስለ ጉዳዩ በግልፅ ለማውራት የወሰነው።

ማርክ እንደሚለው ሲአይኤ በዚህ ጉዳይ የተጠቃው እሱ ብቻ አለመሆኑን ሲረዳ ጉዳዩን በጥልቀት መመርመር ይዟል።

ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት ግማሽ ደርዘን የሚሆኑ ሌሎች የአሜሪካ ሰላዮች በዚህ ጉዳይ ተጠቂዎች ሆነዋል።

"በርካታ ነባር መኮንኖች ይህ ሕመም እንዳለባቸው እየተናገሩ ነው" ይላል ማርክ። እሱ እንደሚለው ሕመማቸውን ሳይናገሩ እየተሰቃዩ ያሉ መኮንኖችም አሉ።

ብዙዎቹ ሰዎች ይህ ሕመም የታየባቸው ሩስያና ኩባ እንዲሁም ቻይና ደርሰው ከመጡ በኋላ እንደሆነ ይናገራሉ።

ከእነዚህ ሃገሮች ባለፈ አውስትራሊያ፣ ፖላንድና ጆርጂያ ደርሰው የመጡ ሰዎች ይህ ሕመም እንዳጋጠማቸው ሪፖርት አድርገዋል።

አንድ የዋይት ሐውስ ባለሥልጣንም ሎንዶን ከተማ ካለ ሆቴላቸው ውስጥ ሳሉ ተመሳሳይ ነገር እንደገጠማቸው ተዘግቧል። የብሪቲሽ ደኅንነት ሰዎች ስለ ጉዳዩ መረጃው ቢኖራቸውም ምን እንደተፈጠረ እንደማያውቁ አሳውቀዋል።

የዩኬና ዩናይትድ ስቴትስ ስለዚህ ጉዳይ በጥምረት እየመከሩ እንደሆነ ቢሰማም የዩኬ ውጭ ጉዳይ ቢሮ ለቢቢሲ እንደተናገረው በዚህ ጉዳይ ስለተጠቃ እንግሊዛዊ የሚያውቀው ነገር የለም።

የሩስያ እጅ አለበት ይሆን?

ከሃቫናው ክስተት በኋላ የተሠሩ የሕክምና ምርምር ውጤቶች ጣታቸውን ወደ ሩስያ ይጠቁማሉ። አልፎም ሲአይኤ መኮንኖቹ በተጠቁባቸው ቦታዎች አቅራቢያ የሩስያ ሰላዮች እንደነበሩ የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉኝ ብሏል።

ነገር ግን እስካሁን ድረስ የተገኙት ማስረጃዎች አሜሪካ ሩስያን በይፋ እንድትከስ የሚያበቁ አይደሉም።

አንዳንዶች ምናልባት ሩስያ ከሌሎች ሃገራት ሰላዮች ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች መረጃ ለመመዝበር በምታደርገው ጥረት ነው ሰላዮቹ እንዲህ ዓይነት ሕመም የሚገጥማቸው ሲሉ ይከራከራሉ።

ይህ መንገድ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ጥቅም ላይ ይውል እንደነበር ይዘገባል።

ሌላኛው አሜሪካዊ የቀድሞ ሰላይ ጆን ሳይፈር የሩስያ ደኅንነት ኃይሎች በአሜሪካ ኤምባሲ ዙሪያ ያንዣብቡ ነበር ይላል። አልፎም ሞስኮው ውስጥ የሩስያ ሰላዮች በሽፍን መኪናዎች ሰዎችን ይከታተላሉ ይላል።

ጆን፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሳላዮች ላይ እየደረሱ ላሉ ጥቃቶች ሩስያን ተጠያቂ ያደርጋል። ሩስያ ይህንን ለምን እንደምታደርግ ግን አላውቅም ይላል።

አንድ ሌላ የቀድሞ ሰላይም ሩስያ ለዚህ ጥቃት ተጠያቂ ናት ይላል። ነገር ግን ሩስያ ይህን የምታደርገው ጥቃት ለማድረስ ሆን ብላ ይሁን አሊያም መረጃ ለመመዝበር ይሁን እርግጠኛ አይደለም።

ማርክ ግን ሩስያ ይህን የምታደርገው ሆን ብላ ሰላዮችን ለማጥቃት ነው ብሎ ያምናል።

ሃቫና ውስጥ ሩስያ አሜሪካዊን ዲፕሎማቶችን ልትመርዝ የቻለችው በዩናይትድ ስቴትስና በኩባ መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻክር በማሰብ ነው ተብሎ ይታሰባል።

ኩባ ለወትሮው ከአሜሪካ ይልቅ ለሩስያ ቅርበት አላት።

ነገር ግን በተለምዶ የስለላ ድርጅቶ የተቃናቃኝ ሃገራት ሰላዮችን ሆን ብለው ለመጉዳት አይንቀሳቀሱም። ቢሆንም የቀድሞ የሲአይኤና ኤምአይ6 [የእንግሊዝ ስለላ ድርጅት] ሰላዮች ሩስያ ይህን ልማድ ችላ በማለት ሆን መኮንኖችንን እየተከታተለች እየጎዳች ነው ይላሉ።

የሩስያ የ/ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 'ሩስያ መሰል መሠረተ-ቢስ ክሶችን ከቁም ነገር አትቆጥራቸውም' ሲል ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥቷል።

ሰላዮችና የሕክምና ሙያተኞች ግን ተጨማሪ ምርመራ እንዲካሄድ ይፈልጋሉ።

አዲሱ የባይደን አስተዳደር የሩስያ 'ጠብ አጫሪ' ባሕሪያትን ለመከለስ ቃል ገብቷል። አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንተኒ ብሊንከንም ስለ 'ሃቫና ሲንድረም' የበለጠ መረጃ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሩስያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩ አዲሱ የሲአይኤ አለቃም በዚህ ጉዳይ ላይ የበለጠ ሊሠሩ ይችላሉ ተብሏል።

ሩስያ በዚህ ጉዳይ ላይ እጇ እንዳለበት ከታወቀ እጅግ ትልቅ ዜና ሊሆን እንሚችል ባያጠራጥርም የሞስኮውን ተሳታፊነት ማረጋገጥ ግን ቀላል አይሆንም።

ማርክ፤ እውነቱን ማወቁ ከሕመሙ ጋር በየቀኑ ከመኖር ባይታደገው እፎይታ እንደሚሰጠው ይናገራል።