በሚየንማር ሳን ሱቺ ይለቀቁ የሚሉ ጥያቄዎች መበርታታቸው ተሰማ

ኦንግ ሳን ሱ ቺ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በትናንትናው ዕለት በቀድሞዋ በርማ በአሁኗ ሚየንማር ጦሩ በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን መቆጣጠሩን ተከትሎ የአገሪቷ መሪ ኦንግ ሳን ሱ ቺ ይለቀቁ የሚሉ ጥያቄዎች በርትተዋል።

የኖቤል ተሸላሚዋና በምርጫ ስልጣን የተቆናጠጡት ኦንግ ሳን ሱ ቺ በወታደሮች በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ አልታዩም ተብሏል።

ከሳቸው በተጨማሪ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፓርላማ አባላትም በመዲናዋ በሚገኘው መኖሪያ ስፍራቸው በወታደሮች ተከበው ነው የሚገኙት።

ምንም እንኳን ይኸንን ያህል ጠንከር ያለ ተቃውሞ በአደባባዮች ባይሰማም የህክምና ባለሙያዎች የስራ ማቆም አድማ መትተዋል ፤አንዳንድ እምቢተኝነትም እየተስተዋለ ነው።

በቅርቡ በምርጫ ማሸነፋቸው የታወጀውን ኦንግ ሳን ሱ ቺን ፓርቲ ምርጫውን አጭበርብሯል በማለት ጦሩ የሚወነጅል ሲሆን በትናንትናው ዕለት ስልጣን በእጁ ካስገባም በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።

ፓርቲያቸው ናሽናል ሊግ ፎር ዲሞክራሲ (ኤን ኤል ዲ) ኦንግ ሳን ሱቺ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጥያቄውን በዛሬው እለት አቅርቧል።

ከዚህም በተጨማሪ በዚህ አመት በህዳር ወር የተደረገውና 80 በመቶ አሸናፊነቱን ያገኘው ኤንልዲ ፓርቲ ውጤቱን በፀጋ እንዲቀበል ለጦሩ ጥያቄ አቅርቧል።

ምንያማር የሲቪል አስተዳደር በአውሮፓውያኑ 2011 ስልጣን እስኪይዝ ድረስ በጥምር ወታደራዊ ኃይል ትመራ ነበር።

ምንያማር በመፈንቅለ መንግሥቱ ማግስት

አገሪቷ በመፈንቅለ መንግሥቱ ማግስት ፀጥ ረጭ ያለች ሲሆን፤ ጎዳናዎቿም ነዋሪዎች አይታዩባቸውም። ወታደሮች በመኪና ተጭነው በተለያዩ ከተሞች በመዞር እየቃኙ ሲሆን የምሽት የሰዓት እላፊ አዋጅም ተጥሏል።

በትናንትናው ዕለት ተቋርጦ የነበረው የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ተመልሷል።

በዋነኛዋ ከተማ ያንጎን ጎዳናዎች ላይ አንዳንዶች ለአመታት የተዋጉለት ዲሞክራሲ መና ቀረ ማለታቸው ተሰምቷል።

የኦንግ ሱን ሱቺ መለቀቅ እየጠየቀ ያለው ፓርቲዋ ብቻ ሳይሆን በመንግሥት ሆስፒታሎች የሚሰሩ ዶክተሮች ካልተለቀቀች ከነገ ጀምሮ ስራ አንገባም ማለታቸው ተሰምቷል።

አንዳንዶችም ተቃውሟቸውን ለማሳየት ለየት ያለ ልብስ ለብው መጥተዋል። አንድ ዶክተር ከስራው መልቀቁ ተነግሯል።