ኮሮናቫይረስ፡ ደቡብ አፍሪካውያን አልኮል መጠጥ ላይ የተጣለባቸው ገደብ በመነሳቱ ተደስተዋል

በኬፕ ታውን የሚገኝ መጠጥ ቤት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በደቡብ አፍሪካ ወረርሽኙን ተከትሎ አልኮል መጠጦች ላይ ተጥሎ የነበረው ገደብ ተነሳ፡፡

የባሕር ዳርቻዎችም መከፈት ተጀምረዋል፡፡ ለመንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት መሰባሰብም እንዲሁ በተወሰነ መልኩ ተፈቅዷል፡፡

ይህ ጥብቅ ገደብ የመላላቱ ዜና የተሰማው ፕሬዝዳንት ራማፎሳ የአስትራዜኒካ ክትባት አገራቸው መድረሱን ባበሰሩበት ማግስት ነው፡፡

ደቡብ አፍሪካ የመጀመርያውን 1 ሚሊዮን ጠብታ ክትባት ከአስትራዜኒካ አግኝታለች፡፡

ደቡብ አፍሪካ ከአፍሪካ አገራት በሙሉ ብዙ ሰዎች በወርሽኙ የተያዙባት አገር ናት፡፡ በሟች ቁጥርም ከፍተኛውን የሰው ብዛት ነው ያስመዘገበችው፡፡

አንድ ሚሊዮን 400ሺ ዜጎቿ በተህዋሲው የተጠቁ ሲሆን 45ሺ የሚጠጉት ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡

በርካታ የዓለም አገራት ከደቡብ አፍሪካ የሚመጡ ዜጎች ወደ አገራቸው እንዳይገቡ አግደዋል፡፡ ይህም የሆነው የኮቪድ አዲስ ዝርያ በደቡብ አፍሪካ መኖሩ በመረጋገጡ ነው፡፡

በደቡብ አፍሪካ የተገኘው አዲሱ የኮቪድ ዝርያ በፍጥነት የመዛመት ባህሪ ስላለው ለብዙ አገራት ስጋት ሆኗል፡፡

ይህ አዲሱ ዝርያ ለክትባት እጅ አይሰጥ ይሆን የሚል ፍርሃት በባለሙያዎች ዘንድ ይሰማል፡፡

አሁንም ደቡብ አፍሪካ ደረጃ 3 በሚባለው የእንቅስቃሴ ገደብ ላይ ያለች ሲሆን ወሳኝ የሚባሉ ገደቦች ላይ ግን ማዕቀቦች እየላሉ ነው፡፡

መደብሮች አሁን አልኮል መጠጥ ከሰኞ እስከ ሐሙስ፣ ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት እስከ ማታ 12፡00 ሰዓት መሸጥ ይችላሉ፡፡

በመጠጥ ቤቶች ደግሞ ከጠዋት 4፡00 ሰዓት እስከ ምሽት 2፡00 ሰዓት ደንበኞች ቁጭ ብለው አልኮል መጠጥ መስተናገድ እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡

ከዚህ በኋላ የሰዓት እላፊ የሚሆነው ከምሽቱ 5፡00 ሰዓት እስከ ሌሊት 10፡00 ሰዓት ነው፡፡

ደቡብ አፍሪካ ወረርሽኙ ከተጀመረ ወዲህ ለ3ኛ ዙር አልኮል መጠጥ ላይ ገደብ መጣሏ ይታወቃል፡፡

በዚህ የተነሳ መጠጥ አምራቾች፣ አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች ሰራተኞቻቸውን ለመበተን እየተገደዱ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ ይህ በአልኮል መጠጥ ላይ የተጣለው ገደብ በብዙ ነዋሪዎች ዘንድም ቅሬታ ፈጥሮ ነበር፡፡

በአልኮል መጠጦች ላይ ከተጣለው ማዕቀብ መላላት ሌላ መስጊዶች ወይም አብያተ ክርስቲያናት ወይም ሌሎች የእምነት ተቋማት 50 ሰዎችን በውስጥ፣ እስከ 100 ምዕመናን በደጅ ማስተናገድ ተፈቅዶላቸዋል፡፡

ፓርኮችና የባሕር ዳርቻዎች ለተገልጋዮች ክፍት ሆነዋል፡፡

ራማፎሳ ከመድኃኒት አምራቾች ጋር ባደረግነው ድርድር 50 ሚሊዮን ጠብታዎችን ለማግኘት ተነጋግረናል ብለዋል፡፡

ደቡብ አፍሪካ በዚህ ዓመት 40 ሚሊዮን ዜጎችን ለመከተብ አቅዳለች፡፡ ይህም የሕዝቧን 2/3ኛ የሚሸፍን ነው፡፡