የመረጃ መረብ ሰርሳሪዎች የፎሎሪዳን ውሃ ለመመረዝ ሞክረው ነበር ተባለ

ውሃ ሲፈስ

በአሜሪካ የመረጃ መረብ ሰርሳሪዎች (ሃከርስ) የፍሎሪዳን የውሃ ሲስተም ዒላማ በማድረግ አደገኛ ኬሚካል ሊጨምሩ እንደነበር የአገሪቱ ባለሥልጣን ገለፁ።

እነዚህ የመረጃ መረብ ሰርሳሪዎች ፍሎሪዳ በሚገኘው ኦልድስማር የውሃ ማጣሪያ ውስጥ የጨመሩት አደገኛ ኬሚካል ሶዲየም ሃይድሮ ኦክሳይድ (lye) ሲሆን የድርጅቱ ሰራተኞቹ በፍጥነት የተከሰተውን በማስተዋል እርምጃ መውሰዳቸው ተገልጿል።

ሶዲየም ሃይድሮ ኦክሳይድ (lye) በውሃ ውስጥ ያለውን አሲድ ለመቆጣጠር በአነስተኛ መጠን የሚጨምር ሲሆን ነገር ግን ከመጠን በላይ ከተጨመረ የጤና እክል ያስከትላል።

የኦድስማር ከንቲባ የሆኑት ኤሪክ ሴይደል "መጥፎ ሰዎች አሉ" ብለዋል።

ድርጊቱን ፈጽመዋል ተብለው ከተጠረጠሩ መካከል እስካሁን ድረስ በቁጥጥር ሥር የዋለ የሌለ ሲሆን የመረጃ መረብ መንታፊዎቹም መቀመጫቸውን አሜሪካ ይሆኑ በሌላ አገር የታወቀ ነገር የለም።

የኦልድስማር የውሃ ማጣሪያ ቁጥጥር የሚደረግለት በኮምፒውተር በተደራጀ ስርዓት ሲሆን አርብ ዕለት ከርቀት ይህንን ስርዓቱን ዒላማ ያደረጉ መንታፊዎች ነበሩ ተብሏል።

አርብ ማለዳ የማጣሪያው ሰራተኛ ከሆኑ ሰዎች መካከል አንዱ ይህንን በሌላ አካል የተደረገ ሙከራ ሲያስተውል የድርጅቱ ተቆጣጣሪዎች መስለውት እንደነበር ታምፓ ቤይ ታይምስ የተሰኘ መገናኛ ብዙኀን ዘግቧል።

ነገር ግን ከሰዓት ሌላ ሙከራ የተካሄደ ሲሆን በዚህ ወቅት የመረጃ መረብ ሰርሳሪዎቹ የማጣሪያውን ሶፍትዌር ውስጥ በመግባት የሶዲየም ሃይድሮኦክሳይድ ይዘቱን እጅግ በጣም ከፍ እንዲል አድርገዋል።

ወድያውኑ በወቅቱ ሥራ ላይ የነበሩ ተቆጣጣሪዎች መጠኑን ወደ መደበኛው እንዲቀንስ አድርገውታል።

ሶዲየም ሃይድሮኦክሳይድ በዋነኛነት ፈሳሽ ማጽጃዎችን ለማምረት ያገለግላል።

ይህ ኬሚካል በጣም አደገኛ ሲሆን ከተዋጠ አፍ፣ ጉሮሮ እና ሆድ እቃ ላይ ጉዳት በማድረስ ማስመለስ፣ ማቅለሽለሽ እንዲሁም ተቅማጥን ያስከትላል።

በተጨማሪም ቆዳ እና አይንን የማቃጠል ባህሪ አለው።

የፒኔላስ ካውንቲ ፖሊስ የሆኑት ቦብ ጉዋልቲየሪ " እኔ የኬሚስትሪ ባለሙያ አይደለሁም። ነገር ግን የማውቀውን እነግራችኋለሁ. . .ከፍተኛ መጠን ያለው ኬሚካል [ሶዲየም ሃይድሮኦክሳይድ] ውሃ ውስጥ ከጨመራችሁ ለጤና ጠንቅ ነው" ብለዋል።

የኦልድስማር ውሃ ማጣሪያ ለ15 ሺህ ነዋሪዎች እንዲሁም ለተለያዩ የንግድ ተቋማት ውሃ ያቀርባል።

በአሁኑ ወቅት በጊዜያዊነት የውሃውን ስርዓት ከርቀት መቆጣጠር የሚያስችለው ስርዓት እንዳይሰራ ተደርጓል።

በ2016 ቨሪዞን የተሰኘ ተቋም ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው በአሜሪካ አንድ ስሙ ያልተገለፀ የውሃ ማጣሪያ ላይ ተመሳሳይ ጥቃት ተሰንዝሮበት ነበር።

በ2020 ደግሞ በእስራኤል የውሃ ማጣሪያዎች ላይ የመረጃ መዝባሪዎች ተደጋጋሚ ሙከራ አድርገዋል።

አሁን በፍሎሪዳ የደረሰው ጥቃት ለዓመታት "ወሳኝ በሆኑ የሕዝብ መገልገያዎች ላይ" ጥንቃቄ እንዲደረግ ሲወተውቱ ለነበሩ የመረጃ ደህንነት ተቋማትና ባልደረቦችን የበለጠ የሚያስጨንቅ ነው።

ውሃ፣ መብራት፣የኒውክለር ማብላሊያዎች እና መጓጓዣዎች ጊዜያቸው ያለፈባቸው የኢንፎርሜሽን ቴክነሎጂዎችን በብዛት ስለሚጠቀሙ የመረጃ መረብ ደህንነታቸው ደካማ እና ተጋላጭ ነው፤ ይህ ደግሞ በእንድ ጊዜ የአገልግሎት መቋረጥ እንዲገጥም ያደርጋል ተብሎ ተሰግቷል።