ኤለን መስክ 1.5 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ ቢትኮይን መግዛቱን ተከትሎ መገበያያው ከፍተኛ ጭማሪ አሳየ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኤለን መስክ የመኪና ኩባንያ ቴስላ 1.5 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ ቢትኮይን በታህሳስ ወር መግዛቱን አስታወቀ። ኩባንያው ገንዘቡን ወደፊት መቀበል እንደሚጀምርም ጨምሮ ይፋ አድርጓል።
ይህ ዜና እንደተሰማ የቢትኮይን ዋጋ በ 17 በመቶ ወደ 44 ሺህ 220 አሻቅቧል ተብሏል።
ቴስላ ኩባንያው በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው የማይጠቀምበትን ጥሬ ገንዘብ ዳጎስ ያለ ትርፍ ለማግኘት በማሰብ ይህንን ማድረጉን ገልጿል።
መስክ በትዊተር ገፁ ላይ "#bitcoin" የምትል ቃል ማኖሩን ተከትሎ ዋጋው ማሻቀቡ ተሰምቷል።
ከቀናት በኋላ ከሰሌዳው ላይ ያጠፋው ቢሆንም ስለ ቢትኮይን እና ሌላ ክሪፕቶከረንሲ፣ ዶጅኮይንን ጨምሮ፣ ግን ማውራቱን ቀጥሎበታል።
መስክ ስለ ዶጅኮይን ማውራቱን ተከትሎ ዋጋው በ50 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ቴስላ በታሕሳስ ወር ላይ " የኢንቨስትመንት ፖሊሲዬ ላይ ማሻሻያ አድርጌያለሁ" ያለ ሲሆን ማንም ግለሰብ "በተቀማጭ ንብረቶች (digital assets)" ማለትም ዲጂታል ከረንሲዎች (የመገበያያ መንገዶች)፣ በወርቅ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት የለውም ብሎ ነበር።
ኩባንያው 1.5 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ ቢትኮይን መግዛቱን ያስታወቀ ሲሆን ወደፊትም " ዲጂታል ንብረቶችን ሊገዛ እና ሊያስተዳድር" እንደሚችል ገልጿል።
"በተጨማሪም ወደፊት በሥራ ላይ ባሉ ሕጎች ላይ ተመስርተንና መጀመሪያ ላይ ውሱን በሆነ መልኩ ምርቶቻችንን በቢትኮይን መሸጥ እንጀምራለን ብለን አንጠብቃለን" ብሏል።
መስክ ከሳምንት በፊት በትዊተር ሰሌዳው ላይ ቢትኮይን በኢንቨስተሮች ከፍተኛ ተቀባይነት ለማግኘት "ጫፍ ላይ ደርሷል" ብሎ ጽፎ ነበር።
ይህ የቴስላ እርምጃ ለክሪፕቶከረንሲ "ማርሽ ቀያሪ" ነው ሲሉ ባለሙያዎች ተናግረዋል።
ክሪፕቶከረንሲ ላይ ምርምር የሚያደርገው ሜሳሪ የተሰኘው ተቋም ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ኤሪክ ተርነር " የቴስላ ወደ ቢትኮይን መግባትን ተከትሎ ኩባንያዎች ቢትኮይን ለመግዛት ሲሽቀዳደሙ ልናይ እንችላለን" ብለዋል።
"አሁን በዓለም ላይ ትልቁ ኩባንያ ቢትኮይን አለው ማለት ቴስላ ላይ ኢንቨስት ያደረገ ባለሃብት በሙሉ . . .ተጋልጦ አለው ማለት ነው።"
ነገር ግን የMarkets.com አናሊስት የሆነው ኒይል ዊልሰን ግን ቢትኮይን "በጣም የሚዋዥቅ" ክሪፕቶከረንሲ ነው ሲል ያስጠነቅቃል።
"ቴስላ አሁን ከፍተኛ የሆነ አደጋን ሊወስድ ነው፤ ይህ በርካታ ባለሃብቶችን ላያስጨንቃቸው ይችላል። ነገር ግን አንዳንድ ወግ አጥባቂዎችን ግድ ይላቸዋል" ብሏል።
የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከቅርብ ወራት ወዲህ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ያሳየው ቢትኮይን በዚህ ዓመት ከፋይናንስ ተቋማት ድጋፍ እያገኘ መጥቷል።
የዓለማችን ግዙፉ የገንዘብ አስተዳዳሪ ብላክሮክ የተወሰኑ ፈንዶቹ በከረንሲው (በመገበያያው) ኢንቨስት እንዲያደርጉ ውሳኔ አሳልፏል።
ነገር ግን አሁንም ማዕከላዊ ባንኮች ክሪፕቶከረንሲን በአይነ ቁራኛ ነው የሚመለከቱት።
በጥቅምት ወር የባንክ ኦፍ ኢንግላንድ ገዢ አንድሪው ቤይሊ፣ ቢትኮይንን እንደ ክፍያ ለሚጠቀሙ አካላት ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል።
ቢትኮይንን በክፍያ የሚጠቀሙ ሰዎችንም ሲመክሩ ዋጋው በጣም የሚዋዥቅ መሆኑን ባለሃብቶች ሊያውቁ ይገባል ብለዋል።
ቢትኮይን ምንድነው?
ቢትኮይን ማለት በቀላል ቋንቋ፤ ዲጂታልገንዘብ+መገበያያ በማለት ማጠቃለል ይቻላል።
ይህ መገበያያ በኪሳችን ተሸክመን እንደምንዞረው የብር ኖት ወይም ሳንቲም ሳይሆን 'ኦንላይን' የሚቀመጥ ዲጂታል ገንዘብ ነው።
ሌላው የቢትኮይንና የተቀሩት የክሪይፕቶከረንሲዎች ልዩ ባህሪ በመንግሥታት እና በባንኮች አለመታተማቸው እንዲሁም ቁጥጥር አለመደረጉ ነው። ቢትኮይን የሚፈጠረው 'ማይኒንግ' በሚባል ሂደት ነው። በመላው ዓለም በኔትወርክ በተሳሰሩ ኮምፒውተሮች ቁጥጥር ይደረግበታል።
ቢትኮይንን የፈጠረው ግለሰብ/ቡድን በዓለም ላይ 21 ሚሊዮን ቢትኮይኖች ብቻ እንዲፈጠሩ ገደብ እንዳስቀመጡ ይታመናል። የብሎክቼይን መረጃዎች እንደሚያሳዩት እስካሁን 17 ሚሊዮን ያህል ቢትኮይኖች ማይን ተደርገዋል።