ኔዘርላንድስ ከሌሎች አገራት የሚመጡ የማደጎ ልጆችን ከልክያለሁ አለች

የፎቶው ባለመብት, AFP
ኔዘርላንድስ ዜጎቿ ልጆችን በማደጎ አምጥተው እንዳያሳድጉ ክልከላ አስቀመጠች።
በኔዘርላድስ በይፋ በተሰራ አንድ ምርመራ በርካታ የመብት ጥሰቶች ተፈጽመው በመገኘታቸው ምክንያት ከሌሎች አገራት ህጻናትን በማደጎ ማምጣት ልትከለክል እንደሆነ ተገልጿል።
ምርመራው በተለይ ከአውሮፓውያኑ 1967 እስከ 1998 ባሉት ዓመታት ውስጥ ከብራዚል፣ ባንግላዲሽ፣ ኮሎምቢያ፣ ኢንዶኔዢያ እና ስሪ ላንካ ወደ ኔዘርላንድ በመጡ ህጻናት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
የአገር ውስጥ ጥበቃ ሚኒስትሩ ሳንደር ዴከር እንዳሉት የደች መንግስት ለብዙ ዓመታት በጉዳዩ ላይ ጣልቃ ባለመግባቱ ስህተት ሰርቷል ብለዋል።
ተፈጽመዋል የተባሉት የመብት ጥሰቶችና ጥቃቶች መካከል የወለዱ እናቶች ልጃቸውን አሳልፈው እንዲሰጡ ገንዘብ መስጠትንም እንደሚያካትት የተሰራው ጥናት አመላክቷል።
የምርመራ ኮሚቴው እንዳስታወቀው የደች መንግስት ኃላፊዎች ጭምር የሚሰራውን ስህተት እያዩ ዝም ብለዋል፤ አንዳንዶች ደግሞ እንደውም በተግባሩ ላይ ተሳትፈዋል። ነገር ግን ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሙስና ስለመፈጸሙ ግን መረጃ እንዳልተገኘ ተገልጿል።
ሚኒስትር ሳንደር ዴከር ''ኃላፊዎች ለዓመታት ጉዳዩን እያዩ እንዳላዩ ሆነው አልፈዋል'' ብለዋል።
''መንግስት ማድረግ የሚገባውንና የሚጠበቅበትን ነገር ማድረግ አልቻለም። በጉዳዩ ላይ የነቃ ተሳትፎ ሊኖረው ይገባ የነበረ ቢሆንም በመከታተልም ሆነ በመቆጣጠር ላይ ቸልተኝነት ተስተውሏል። በዚህ ምክንያት መንግስት ይቅርታ ይጠይቃል። በካቢኔው ስም በተመሳሳይ መልኩ በማደጎ ሂደት ወደዚህ የመጡትን በሙሉ ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ'' ብለዋል ሚኒስትሩ።
ኢንዶኔዢያ የሚገኙ ወላጅ እናትና አባቷን በማፈላለግ ላይ የምትገኝ አንዲት የደች ዜግነት ያላት ሴት ለቢቢሲ በሰጠችው ቃል የመንግሥትን ውሳኔ እንደምትቀበለውና በተግባር ላይ ሲውል የነበረው ስርአት ለህገወጥ የህጻናት ዝውውር ምቹ እንደነበር ገልጸለች።
'' ሌላው ቀርቶ በኔዘርላለንድው ውስጥ የሚካሄዱ ልጅ የማሳገድ አካሄዶች ለሙስና እና ለህገወጥ የህጻናት ዝውውር የተመቸ ነው'' ብላለች የ45 ዓመቷ ዊድያ አስቱቲ።
''በአሁኑ ሰአት የአገር ውስጥ ማደጎ ልጆች የሚፈልጉ ወላጆች ላይ ነው ትኩረቱን ያደረገው፤ ነገር ግን መሆን ያለበት በተቃራኒው ነው። አሳዳጊ የሚፈልጉ ህጻናት የመምረጥ እድሉ ሊሰጣቸው ይገባል''
የቢቢሲው የኢንዶኔዢያ ዘጋቢ ጀሮም ዊራዊን እንደሚለው እንደ አውሮፓውያኑ እስከ 1984 ባሉት ዓመታት 3 ሺ ኢንዶኔዢያውያን ህጻናት የደች ዜግነት ባላቸው ሰዎች በማደጎ የተወሰዱ ሲሆን ከዚህ ዓመት በኋላ ግን ኢንዶኔዢያ ማደጎ ከልክላለች።
በቀድሞ ስሟ ደች ኢስት ኢንዲስ በመባል የምትታወቀው ኢንዶኔዢያ ከኔዘርላንድስ ነጻነቷን ያገኘችው በአውሮፓውያኑ 1945 ነበር።
በታዋቂው የሲቪል አገልጋይ ጂቤ ጆስትራ የሚመራው የምርመራ ኮሚቴ ከ1967 እስከ 1998 ባሉት ዓመታት በፊትና በኋላ በርካታ ስህተቶች መፈጸማቸውንና የምርመራው ዋነኛ ትኩረትም ይሄው እንደሆነ ተገልጿል።
የማደጎ ስርአቱ ለማጭበርበር ምቹ ነበር በዚህም ምክንያት በርካታ የመብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል፤ እነዚህ ነገሮች እስከ አሁንም ድረስ እየተፈጸሙ ነው ይላል ኮሚቴው ያወጣው ሪፖርት።
ሚኒስትሩ እንዳሉት ካቢኔው ከዚህ በኋላ ከውጭ አገራት የሚደረጉ የማደጎ ሂደቶች እንዴት መከናወን እንዳለባቸው ውሳኔ ያሰስተላልፋል ብለዋል።
በተለይ የዘር ግንዳቸው ከኢንዶኔዢያ የሚመዘዝ የደች ዜጎች መንግስት ያስተላለፈውን ውሳኔ እንደሚደግፉትና ይቅርታውን እንደሚቀበሉት ገልጸዋል። ነገር ግን ለበርካታ ዓመታት የተሰራውን ስህተት ለማረም ገና የመጀመሪያው እርምጃ እንደሆነ በርካቶች እየገለጹ ነው።
የ45 ዓመቷ ዊድያ አስቱቲ በአምስት ዓመቷ ነበር በማደጎ ወደ ኔዘርላንድስ የተወሰደችው። ላለፉት በርካታ ዓመታት ወላጆቿን ስታፈላልግ ቆይታለች። በጣም ከባድና አስቸጋሪ ሂደት ነበር ትላለች።
ምክንያቱም በማህደሯ ላይ ስለወላጆቿ የተጻፈው በሙሉ ሃሰት ነው። እናቷ ሊሆኑ እንደሚችሉ የተገመቱ ሁለት ሴቶችም በዘረመል ምርመራ እናቷ እንዳልሆኑ ማረጋገጥ ችሏል።
'' የደች መንግስትን የምወቅስበት አንደኛው ምክንያት ወላጆቼ ስለእኔ ምንም አይነት ነገር እንዲነገራቸው ባለማድረጉ ነው። ምን እንደሆንኩኝ እንኳን አያውቁም። ምናልባትም የህገወጥ ህጻናት አዘዋዋሪዎች እጅ ላይ ልወድቅ እችል እንደነበር እንኳን አያውቁም'' ትላለች።
''ያሳደጉኝ ቤተሰቦቼ ከአንዲት ኢንዶኔዢያዊት እናት ወስደው እንዳሳደጉኝ ባሰቡ ቁጥር የጥፋተኝነት ስሜት ውስጥ ይገባሉ። ነገር ግን እነሱ ምን ማድረግ አይችሉም ነበር። የተነገራቸው አንዲት ልጅ ከኢንዶኔዢያ እንደሚያሳድጉ ብቻ ነው''
ሌላኛዋ ከኢንዶኔዢያ በማደጎ የተወሰደችው ዴዊ ዲጀሌ ደግሞ ላለፉት ዓመታት ለተሰራው ስህተት ካሳ ሊከፈል ይገባል። ''እኔ እንደሚመስለኝ የደች መንግስት ሕገወጥ ማደጎዎችን በተመለከተ ቸልተኝነት ታይቶበታል። ስለዚህ ለተጎጂዎች መንግስት ካሳ ሊከፍል ይገባል'' ብላለች።