ግብፅ ውስጥ ጥንታዊ የቢራ ፋብሪካ ተገኘ

5 ሺህ ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረ የቢራ ፋብሪካ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ,

5 ሺህ ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረ የቢራ ፋብሪካ

የሥነ-ቅርስ ምርምር ተመራማሪዎች [አርኪዮሎጂስትስ] በዓለም ጥንታዊ ነው ያሉትን የቢራ ፋብሪካ ቆፍረው አግኝተዋል።

የቢራ ፋብሪካው 5 ሺህ ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረ ነው ተብሏል።

አሜሪካዊያንና ግብፃዊያን ተመራማሪዎች በትብብር ያገኙት ይህ ፋብሪካ አቢዶስ በተሰኘችው የግብፅ በራሃማ ሥፍራ የተተከለ ነው።

የሥነ-ቅርስ ሙያተኞቹ ያገኙት ጥንታዊ ፋብሪካ 40 ጉድጓዶች ያሉት ሲሆን ብቅል እና ውሃ ተደባልቆ ቢራ የሚጠመቅበት ነው።

የቢራ መጥመቂያ ፋብሪካው በንጉሥ ናርመር ዘመን የተተከለ እንደሆነ ከጠቅላይ ጥንታዊ ዕቃዎች ካውንስል የተገኘው መረጃ ያሳያል።

መረጃው ይህ ፋብሪካ በዓለማችን ጥንታዊና ግዙፍ የቢራ ፋብሪካ ነው ይላል።

ንጉሥ ናርመር ከ5 ሺህ ዓመታት በፊት የነበረ ንጉሥ ነው።

ንጉሡ የመጀመሪያውን አገዛዝ የመሠረተና ግብፅን አንድ ያደረገ እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ይናገራሉ።

የቢራ መጥመቂያው እያንዳንዳቸው 20 ሜትር ርዝመት ያላቸውና 40 ጉድጓዶች ያዘሉ ስምንት ግዙፍ ክፍሎች አሉት ይላሉ የካውንስሉ መሪ ሙስጠፋ ዋዚሪ።

ፋብሪካው በሥራ እያለ በርካታ ሺህ ጋሎን ቢራ እንደተጠመቀበት ይታመናል።

ለቢራ የሚሆን ብቅል እና ውሃ ተደባልቆ በተዘጋጀለት ጋን ውስጥ ይቀመጥና እንዲግል ይደረጋል ሲሉ መሪው አጠማመቁን ያስረዳሉ።

ከፋብሪካው ተጠምቀው የሚወጡ መጠጦች በጊዜው ለነበሩ ንጉሣዊ አከባበሮች ጥቅም ላይ ይውሉ እንደነበር ይታመናሉ ሲል የግብፅ ቱሪዝም ሚኒስትር ያወጣው መግለጫ ይናገራል።

መግለጫው፤ እኒህ አከባበሮች በግብፅ ነገሥታት የቀብር ሥፍራ ውስጥ ይከናወኑ እንደነበር የቆፋሪዎቹ ቡድን አጋር መሪ የሆኑትና በኒው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩት ማቲው አዳምስን ዋቢ አድርጎ ያትታል።

በወቅቱ ፋብሪካው ቢራ በገፍ ያመርት እንደነበርና እስከ 5 ሺህ ጋሎን ቢራ ሳይጠመቅ እንዳልቀረ ተመራማሪዎቹ ይናገራሉ።

በወቅቱ የነበሩ ግብፃዊያን በተለያዩ ዝግጅቶች ወቅት ቢራ ይጠቀሙ እንደነበር በቁፋሮው ሊታወቅ እንደቻለም ነው የቱሪዝም ሚኒስቴሩ የሚያስረዳው።

አቢዶስ ግብፅ ውስጥ ያለች እጅግ ጥንታዊ ከተማ ስትሆን ሺህ ዓመታት ያስቆጠሩ ቤቶችና ቤተ-መንግሥቶች መገኛ ናት።

አቢዶስ በላይኛው ግብፅ በሶሃግ ግዛት ስትሆን የምትገኘው ሥፍራው ሉክዞር የተሰኘውና በቱሪስቶች ዘንድ ታዋቂ የሆነው ቦታ መገኛም ነው።

በያዝነው ወር መጀመሪያ አካባቢ አሌክዛንድሪያ ውስጥ 2 ሺህ ዓመት ዕድሜ ያላቸውና ምላሳቸው ወርቅ የሆነ የደረቁ ሬሳዎች [ማሚ] መገኘታቸው ይታወሳል።