ናይጄሪያዊቷ የዓለም ንግድ ድርጅትን እንዲመሩ ተመረጡ

ናይጄሪያዊቷ ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢውያላ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ናይጄሪያዊቷ ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢውያላ የመጀመሪያዋ ሴት እንዲሁም የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት የዓለም ንግድ ድርጅት ኃላፊ ሆነው ተመርጠዋል።

ደብልዩ ቲ ኦ በተሰኘው ቅፅል ስሙ የሚታወቀው የዓለም ድርጅትን እንዲመሩ የተመረጡት ናይጄሪያዊት ከዚህ ቀደም የፋይናንስ ሚኒስትር ነበሩ።

የድርጅቱ ጠቅላይ ምክር ቤት ባደረገው ልዩ ስብሰባ ነው ናይጄሪያዊቷ በዳይሬክተር ጄኔራልነት እንዲመሩ የመረጠው።

የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ዶ/ር ኦኮንጆ የዓለም ባንክ 'ማኔጂንግ ዳይሬክተር' ሆነው አገልግለዋል።

የዓለም ንግድ ድርጅት የተለያዩ ፈተናዎች የተጋረጡበት ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው።

ከእነዚህ መካከል የንግድ አለመግባባቶችን መፍታት፣ የገቢ ንግድ የማያበረታቱ ሃገራትን ማግባባትና በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተከሰተውን መላሸቅ መግታት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

ተቺዎች ድርጅቱ በብዙ ችግር የተተበተበ ነው ሲሉ ይገልፁታል።

ንጎዚ ማናቸው?

የ66 ዓመቷ ናይጄሪያዊት የድርጅቱ ኃላፊ በመሆን የተመረጡ የመጀሪያዋ አፍሪካዊት ናቸው።

ምንም እንኳ በቅርቡ የአሜሪካ ዜግነት ቢያገኙት ለሃገራቸው ናይጄሪያ ከፍተኛ ፍቅር እንዳለቸው ይናገራሉ።

በናይጄሪያ ሕብረ ቀለማዊ ልብስ አጊጠው የሚታዩት ንጎዚ የአራት ልጆች እናት ሲሆኑ የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ናቸው።

ከቢቢሲ ሃርድ ቶክ ዝግጅት ጋር ባለፈው ሐምሌ ቆይታ የነበራቸው አዲሷ ኃላፊ ድርጅቱ ፈርሶ መሠራት ያለበት ነው ሲሉ ያምናሉ።

በሥራ አጋሮቻቸው ዘንድ እጅግ ትጉህና ፀባየኛ ባሕሪ እንዳላቸው የሚመሰክርላቸው ንጎዚ በዓለም ባንክ ለ25 ዓመታት ሠርተዋል።

በዓለም ባንክ ቆይታቸው አነስተኛ ገቢ ላላቸው ሰዎች በርካታ ፈንድ በማሰባሰብ ይታወቃሉ።

በተለይ በፈረንጆቹ 2010 ከተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች 50 ቢሊዮን ዶላር ሰብስበው አነስተኛ ገቢ ላላቸው መለገሳቸው ሁሌም የሚወሳላቸው ተግባር ነው።

ነገር ግን ወደ ሃገራቸው ናይጄሪያ ተመልሰው ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ያልቆፈሩት እንደሌላቸው ይነገርላቸዋል። እሳቸውም በዚህ ድርጊታቸው ይኮራሉ።

በፕሬዝደንት ኦሌሴጉን ኦባሳንጆና በጉድላክ ጆናታን ዘመነ ሥልጣን የፋይናንስ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።

በዚህ ሥልጣን ዘመናቸው ወቅት ሃገራቸውን ከ18 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ማስወጣት ችለዋል።

በናይጄሪያ የነዳጅ ገበያ ያለውን ሥር የሰደደ ሙስና ለማስወገድ ባደረጉት ድርጊት ብዙዎች ያነሷቸዋል።

ቀልድ የማያውቁት

የማሕበረሰብ ትምህርት [ሶሲዮሎጂ] ፕሮፌሰር የሆኑት የሕክምና ዶክተር እናታቸው በፈረንጆቹ 2012 ታፍነው ተወስደው ነበር።

ሰዎች እንደቀልድ ታፍነው በሚወሰዱባት ናይጄሪያ የሳቸውን እናት አፍነው የወሰዱ ሰዎች ገንዘብ ከመጠየቃቸው በፊት ንጎዚ ሥልጣን እንዲለቁ ጠይቀው ነበር።

ነገር ግን የፈለገ ቢሆን አፋኞቹ የሚፈልጉትን ነገር ላለማድረግ ወስነው ነበር።

እናታቸው ዝርዝሩ ባልታወቀ ሁኔታ ከአምስት ቀናት በኋላ ሊለቀቁ ችለዋል።

ብዙዎች እናታቸው የተለቀቁት በሴትዬዋ ጠንካራ ስብዕናና 'ቀልድ የማያውቁ' በመሆናቸው ሊሆን ይችላል ሲሉ ይገምታሉ።

ሴትዬዋ በአዲሱ የሥልጣን ዘመናቸው ለሴቶች ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚችሉ ብዙዎች ይገምታሉ።