ኮሮናቫይረስ፡ የኮቪድ-19 ክትባትን ለማቅረብ የሃብታምና ድሃ አገራት ፍጥጫ

ክትባት

ስለ ኮቪድ-19 ክትባት ስናወራ አንድ ጥያቄ ብዙዎቻችንን ሰቅዞ መያዙ አያጠራጥርም - መቼ ይሆን እኔ የምከተበው? የሚለው።

ጥቂት አገራት የኮቪድ-19 ክትባት ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባ የማሕበረሰብ ክፍሎች ብለው ለይተዋል።

የዓለማችንን ሰዎች ፀረ-ኮሮናቫይረስ መከተብ የሞትና የሕይወት ጉዳይ ነው። ነገር ግን እንዲህ ቀላል አይደለም።

ጉዳዩ በርካታ ግዙፍና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት፣ መንግሥታት የማይፈፅሙትን ቃል የሚገቡበት፣ በቢሮክራሲ የታጠረና ቁጥጥር የበረታበት ነው።

ኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት የተሰኘው ተቋም ባልደረባ የሆኑት አጋተ ዳማራይስ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ጥናት ሠርተዋል።

ተቋሙ ዓለማችን ምን ያክል ክትባት ማምረት እንደምትችልና ያለው የጤና መሠረተ ልማት ምን ያህል በቂ ነው? የሚለውን አጥንቷል።

የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየው ፍጥጫው የሃብታምና የድሃ ነው።

ዩናይትድ ኪንግደምና ዩናይትድ ስቴትስ በአሁኑ ወቅት በቂ የሆነ የክትባት አቅርቦት አላቸው። ምክንያቱም ክትባቱን መግዛት የሚያስችል ገንዘብ አላቸውና።

ሌሎች እንደ ካናዳና የአውሮፓ ሕብረት አባላት ያሉ አገራት የመግዛት አቅሙ ቢኖራቸውም ክትባት ላይ ብዙ እየተሯሯጡ ያሉ አይመስሉም።

ካናዳ ሕዝቧ ከሚያስፈልገው የክትባት መጠን አምስት እጥፍ ከፍ ያለ ክትባት ብታዝም ክትባቱ በታሰበው ጊዜ የደረሰላት አይመስልም።

ካናዳ ክትባቱ በፈለገችው ሰዓት ያልደረሰላት ምናልባት የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የውጭ ገበያን እንዳይከለክል በመፍራት ፊቱን ወደ አውሮፓውያን ክትባት አምራቾች በማዞሯ ነው።

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት አሜሪካ ሳትሆን የአውሮፓ ሕብረት ነው ክትባት ወደ ውጭ መላክ የለበትም የሚል አቋም እያንፀባረቀ ያለው።

አብዛኛዎቹ ገቢያቸው አነስተኛ የሆኑ አገራት ገና ዜጎቻቸውን መከተብ አልጀመሩም። ነገር ግን በተለይ መሃል ላይ አንዳንድ ሃገራት አስደናቂ ውጤት እያስመዘገቡ ነው።

ለምሳሌ ሰርቢያ በአሁኑ ወቅት ከሕዝቧ በመቶኛ ሲቆጠር በርካታ ሰው በማስከተብ ከዓለም ስምንተኛ ናት።

እርግጥ ሰርቢያ ከቻይናና ሩስያ ብዙ ተጠቅማለች። ሁለቱ ሃያላን አገራት በምስራቅ አውሮፓ ያላቸውን የበላይነት ለማስጠበቅ ሰርቢያን ወዳጅ አድርገው ይዘዋል።

የሩስያ ስፓትኒክ 5 የተሰኘው ክትባትና የቻይናው ሲኖፋርም ሰርቢያ ውስጥ እንደልብ ይገኛሉ።

ምንም እንኳ ሰርቢያዊያን የክትባት ቅፅ ሲሞሉ ከፋይዘር፣ ስፓትኒክ አሊያም ሲኖፋርም ምረጡ ቢባሉም በርካቶች ሲኖፋርም ነው የሚሰጣቸው።

ዩናይትድ አራብ ኤሜሬትስም ሲኖፋርም በተሰኘው የቻይና ክትባት ላይ ጥገኛ ናት።

አገሪቱ ለዜጎቿ እየሰጠችው ካለው ክትባት 80 በመቶው ሲኖፋርም ነው። አልፎም በአገሯ የሲኖፋርም ማምረቻ ፋብሪካ እየገነባች ትገኛለች።

አንድ አገር የዓለማችን ከፍተኛ የክትባት አምራች ሆነች ማለት ዜጎቿን በሙሉ ቀድማ ትከትባለች ማለት አይደለም።

አይኢዩ የተሰኘው ተቋም ሠራሁት ባለው ጥናት መሠረት የዓለማችን ከፍተኛ ክትባት አምራች የሚባሉት ቻይናና ሕንድ እስከ ፈረንጆቹ 2022 ድረስ ዜጎቻቸውን በበቂ ሁኔታ ላይከትቡ ይችላሉ።

ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት አገራቱ ያላቸው የሕዝብ ብዛትና የጤና ሠራተኞች ቁጥጥር አለመመጣጠኑ ነው።

ሕንድ የዓለማችን ከፍተኛው የክትባት አምራች ኩባንያ የሆነችው በአንድ ሰው ምክንያት ነው። አንዳር ፑንዋላ።

የዚህ ሰው ኩባንያ የሆነው ሴረም በዓለማችን ከፍተኛው የክትባት አምራች ድርጅት ነው።

ነገር ግን ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት አጋማሽ ቤተሰቦቹ ሰውዬው አብዷል እስኪሉ ድረስ በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች እየመዠረጠ ለክትባት ምርምር ያውል ነበር።

ቢሆንም ቁማሩ ተሳክቶለት ክትባቶቹ ውጤታማ መሆን ችለዋል።

አሁን የዚህ ሃብታም ኩባንያ በቀን 2.4 ሚሊዮን ክትባቶች ያመርታል።

የፑንዋላ ኩባንያ ለሕንድ፣ ብራዚል፣ ሞሮኮ፣ ባንግላዴሽ እና ደቡብ አፍሪካ ክትባት በዋናነት በማቅረብ ላይ ይገኛል።

የዚህ ሰው ኩባንያዎች ከሌሎች የሚለያቸው የኮቪድ-19 ክትባት ማምረት የጀመሩት ቀድመው መሆኑ ነው። ለምሳሌ የኮቪድ-19 ክትባት አሁን ማምረት የጀመሩ ፋብሪካዎች ክትባቱ ታሽጎ እስኪወጣ ወራት ሊፈጅባቸው ይችላል።

ፑናዋላ መጀመሪያ የምሰጠው ለሕንድ ነው ይላል። ቀጥሎ ደግሞ ለአፍሪካ። ይህ የሚሆነው በኮቫክስ አማካይነት ነው።

ኮቫክስ በዓለም ጤና ድርጅት አማካይነት የተቋቋመ ፕሮግራም ሲሆን ለዓለማችን አገራት ዋጋው ተመጣጣኝ የሆነ ክትባት ለማቅረብ ያልማል።

ክትባት የመግዛት አቅም የሌላቸው አገራት ደግሞ በነፃ እንዲያገኙ ይመቻችላቸዋል።

የኮቫክስ ፕሮግራም በሚቀጥለው ወር ለአገራት ክትባት ማድረስ ለመጀመር አቅዷል።

ነገር ግን የመግዛት አቅም የሌላቸው አገራት በጎን በኩል ከኃያላኑ ጋር ውል ለመፈፀም ደፋ ቀና ማለታቸው የዚህን ፕሮግራም ተፈፃሚነት አጠራጣሪ አድርጎታል።

ፑናዋላ እንደሚለው አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት መሪዎች እርሱን በአንድ በሌላም መንገድ አግኝተውት ክትባት እንዲሰጣቸው ጠይቀውታል።

ባለፈው ሳምንት ዩጋንዳ ከሴረም ኩባንያ 18 ሚሊዮን ክትባት በ7 ዶላር ሒሳብ ማግኘቷን አሳውቃለች። 4 ዶላር የሚችለው ኮቫክስ ነው።

ሴረም የተሰኘው ተቋም ከዩጋንዳ ጋር ንግግር ላይ እንደሆነ ቢያሳውቅም ስምምነት ላይ ግን አልደረስንም ብሏል።

የፑናዋላ ተቋም ከዓለም ጤና ድርጅት ፈቃድ ካገኘ 200 ሚሊዮን የአስትራዜኔካ ክትባቶችን ለኮቫክስ ፕሮግራም ለማቅረብ ዝግጁ ነው።

ሃብታሙ ሕንዳዊ ለኮቫክስ ፕሮግራም 900 ሚሊዮን ተጨማሪ ክትባቶች ለማቅረብ ቃል ገብቷል።

ጥናቱን የሠራው ተቋም አንዳንድ አገራት በፈረንጆቹ 2023 እንኳ ሙሉ በመሉ ክትባት ላያገኙ ይችላሉ ሲል ይተነብያል።

በተለይ ደግሞ በርካታው የሕዝብ ክፍል ወጣት የሆነባቸውና የቫይረሱ ተፅዕኖ ጎልቶ ያልወጣባቸው አገራት ክትባቱ በጊዜ ላይደርሳቸው ይችላል ይላል ግምቱ።

እርግጥ ነው ክትባቶች ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መጠን እየተመረቱ ነው። ነገር ግን እኛስ መች ይደርሰናል? የሚል ጥያቄ ምላሽ በብዙ ኹነቶች ላይ የተመሠረተ ነው።