ቻይና ዝናብ ለማዝነብና የተፈጥሮ ሂደትን ለመቆጣጠር የምታደርገው ጥረት

ሲልቨር አዮዳይድ የተባለ ንጥረ ነገር ወደ ደመና በመላክ የአየር ሁኔታ የሚለወጥበት ሂደት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ሲልቨር አዮዳይድ የተባለ ንጥረ ነገር ወደ ደመና በመላክ የአየር ሁኔታ የሚለወጥበት ሂደት ነው።

እንደ ቻይናዋ ቤይጂንግ የአየር ብክለት የሚፈትነው ከተማ የለም። የቤይጂንግ ሰማይ በመጠኑም ቢሆን ጠርቶ ፀሐይ የምትታየው በከተማዋ የሚካሄድ ዓለም አቀፍ ውይይት ሲኖር ነው።

ይህ የሚሆነው በተፈጥሯዊ ሂደት ሳይሆን መንግሥት በቀየሰው ስልት አማካይነት ነው። የቻይና መንግሥት የአገሪቱን የአየር ሁኔታ ለመለዋወጥ ሰው ሠራሽ መንገድ መጠቀም ጀምሯል።

ይህ ሰው ሠራሽ ሂደት በጥቂት የቻይና ከተሞች ብቻ ይተገበር ነበር። ከጥቅምት ወዲህ ግን አገር አቀፍ እንደሚሆን ተነግሯል።

ሂደቱ በሰው ሠራሽ መንገድ ዝናብ እንዲጥል ማድረግ፣ በረዶ ማዝነብ ወዘተ. . . ያካትታል። እአአ በ2015 ይህን ሂደት በቻይና 5.5 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር ማለትም የአገሪቱን 60 በመቶውን ለማዳረስ ታቅዷል።

እቅዱ እንደ ሕንድ ላሉ ጎረቤት አገሮች አልተዋጠላቸውም። ቻይና እና ሕንድ ከድሮውም ውጥረት ውስጥ ናቸው።

ቻይና የአየር ሁኔታን የምትለውጠው እንዴት ነው?

በእንግሊዘኛው ክልውድ ሲዲንግ (cloud seeding) በሰው ሰራሽ መንገድ ዝናብ እንዲጥል የሚደረግበት ቴክኖሎጂ ነው። ለዚህም ሲልቨር አዮዳይድ የተባለ ንጥረ ነገር ወደ ደመና በመላክ የአየር ሁኔታ የሚለወጥበት ሂደት ነው።

በሕንድ የአየር ሁኔታ ባለሙያው ዳናስሪ ጃይራም "ይህንን ቴክኖሎጂ ብዙ አገሮች ይጠቀሙበታል። ቻይናና ሕንድም ይጠቀሳሉ" ይላሉ።

ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራትም ይህ ሂደት ይተገበራል። እንደ አውስትራሊያ ያሉ አገሮች ድርቅን ለመከላከል ይጠቀሙታል።

ሂደቱ በተለይም በአሜሪካ ከ1940ዎቹ ወዲህ ነው እየታወቀ የመጣው። ውጤቱ ላይ ጥያቄ ያላቸው ባለሙያዎች ግን አሉ።

በቤይጂንግ ዩኒቨርስቲ የሚሠሩት ጆን ሲ ሙር "ውጤታማነቱን የሚጠቁሙ ጥቂት ሳይንሳዊ ጽሑፎች ብቻ ናቸው ያሉት። ያለ ሳይንሳዊ ማረጋገጫ የተተገበረ ሂደት ነው" ይላሉ።

ሳይንቲስቱ እንደሚሉት፤ 50 ሺህ የቻይና ከተሞችና ወረዳዎች ይህንን መንገድ ተጠቅመው የእርሻ መሬታቸውን ለማዳን ይሞክራሉ።

ዝናብን በማስቆም ማዕበል ሰብላቸውን እንዳያጠፋው ለመከላከል ይጥራሉ።

ሆኖም ግን ተመራማሪዎች እንደሚሉት ይህ ሂደት ቻይና ውስጥ የሚሠራው ለአንድ ወይም ለሁለት ወራት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዝናብ የማነው?

ቻይና የአየር ሁኔታን በመቆጣጠር ተፈጥሯዊ አደጋ እንዳይከሰት የመከላከል እቅድ እንዳላት አስታውቃለች።

ሰብል እንዳይበላሽ፣ ሰደድ እሳት እንዳይስፋፋ፣ ከፍተኛ ሙቀትን ለመቆጣጠር፣ ድርቅን ለመግታት ወዘተ. . . ይውላል።

ቤይጂንግ ውስጥ የምትሠራው ጋዜጠኛ ይትሲንግ ዋንግ እንደምትለው ቻይና የአየር ሁኔታን ለመቆጣጠር ያወጣችው መርሃ ግብር ሲተገበር ከግዛት ግዛት ይለያያል።

ሂደቱ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ቻይናን አላሳሰቧትም።

የቻይና ውሳኔ ከጎረቤት አገሮቿ ጋር ያላትን የፖለቲካ ፍጥጫ ሊያባብሰው ይችላል።

"የቻይና የአየር ሁኔታ የመለወጥ ሂደትደ የሕንድ የክረምት ዝናብ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል የሚል ስጋት አለ" ሲሉ የሕንዱ ተመራማሪ ያስረዳሉ።

በቻይና እና ሕንድ የድንበር ግጭት ሳቢያ ሕንድ ውስጥ ለቻይና ያለው አመለካከለት እየጠለሸ ነው። የአየር ሁኔታ ለውጡም ከዚሁ ጋር ተያይዞ ይታያል።

በታይዋን ዩኒቨርስቲ በ2017 የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው፤ የአየር ሁኔታ ለውጥ ሲደረግ ከጎረቤት አገራት ጋር ውይይት ካልተደረገ ግጭት ሊነሳ ይችላል።

የአንድ አገር የዝናብ መጠን ሲቀንስ ሌላውን አገር ተጠያቂ የማድረግ ሁኔታ ይፈጠራል።

"ይህ ስጋት ሳይንሳዊ አይደለም። ሆኖም ግን የቲቤት ተራራ የአየር ሁኔታ የተለያየ መሆኑ ከግምት መግባት አለበት። ስለዚህ አንድ አካባቢ የአየር ንብረት ለውጥ ሲከሰት ሌላው ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም" ሲሉ ሳይንቲስቱ ጆን ሲ ሙር ያስረዳሉ።

ቻይና የተለጠጠ እቅድ በማንገብ ሌሎችም ዘርፎች ላይ ለውጥ ልታካሂድ እንደምትችል ባለሙያዎች ይሰጋሉ። ይህም በሰው ሠራሽ መንገድ የፀሐይ ጨረራን ለመቆጣጠር መሞከርን ያካትታል።

እነዚህ ውሳኔዎች የሚተላለፉት ከጎረቤት አገሮች ጋር ባለው ውጥረት ሳቢያ ሊሆን ይችላል የሚል መላ ምትም አለ።

ሳይንቲስቱ በበኩላቸው "ቴክኖሎጂው ችግር አለው እያልኩ አይደለም። ነገር ግን በቴክኖሎጂው አንዳች ችግር ቢከሰት በምን መንገድ ይፈታል? ኃላፊነቱንስ የሚወስደው ማን ነው? ለሚለው መልስ ሊኖር ይገባል" ይላሉ።

በተጨማሪም የአየር ሁኔታን መለወጥን የመሰሉ ሂደቶች ዓለም አቀፍ ውይይት እና ስምምነት እንደሚፈልጉ ባለሙያው ያስረዳሉ።

ሂደቱ የሚተገበርበት ወጥ አሠራር እንዲሁም ሂደቱን ተከትሎ ግጭት ቢነሳ በምን መንገድ መፈታት እንደሚችል አስቀድሞ መታሰብ አለበት ሲሉም ያክላሉ።