ኮሮናቫይረስ፡ ክትባቱን ከወሰዱ በኋላ ኮቪድ-19ን ሊያስተላልፉ ይችላሉ?

ክትባት ከወሰዱ በኋላ ኮሮናቫይረስ ሊያስተላልፉ ይችላሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እንደ አውሮፓውያኑ በ2009 አንድ የ11 ዓመት ታዳጊ ከዩናይትድ ኪንግደም ወደ አሜሪካ ተመለሰ።

ኒውዮርክ ውስጥ የአይሁድ ትምህርት ይማር የነበረው ታዳጊ ምንነቱ ያልታወቀ ህመም ገጥሞት ሰውነቱ ያብጥ ነበር።

ወደ 400 ከሚጠጉ የእድሜ እኩዮቹ ጋር የሐይማኖት ትምህርት ይወስድ የነበረው ታዳጊ ህመሙን ለ22 ልጆችና ለሦስት ጎልማሶች አስተላልፏል።

ልጆቹ ወደ ቤታቸው ሲሄዱ በሽታውን ለቤተሰቦቻቸው አስተላልፈው ህመሙ በብሩክሊን እና ሮክላንድ ተሰራጨ። ወረርሽኙ ለአንድ ዓመት ቆይቶ 3,502 ሰዎች ታመዋል።

ኋላ ላይ ሳይንቲስቶች ሲመራመሩ፤ ህመሙ የተስፋፋው ታዳጊዎቹ በጣም ተቀራርበው የሃይማኖት ትምህርት ሲወስዱ መሆኑን ደረሱበት።

ታዳጊው የኩፍኝና ሌሎችም በሽታዎች ክትባት ወስዷል። እናም ሰውነቱ በሽታ የመከላከል አቅም አዳብሯል። ምንነቱ ባልታወቀው በሽታ ሲያዝ እምብዛም ምልክት ያላሳየውም በክትባቶቹ እገዛ ነው።

ታዳጊው ምንም እንኳን ክትባት ቢወስድም በሽታውን ወደ ሌሎች ሰዎች አጋብቷል።

ብዙ ክትባቶች የህመም ምልክትን ቢያጠፉም ሙሉ በሙሉ ከበሽታ አይከላከሉም። ክትባት የወሰዱ ሰዎች ሳይታወቃቸው ቫይረስ ሊያስተላልፉ ይችላሉ ማለት ነው።

በሽታን የመከላከል አቅም

ከክትባት የሚገኝ በሽታን የመከላከል አቅም በሁለት ይከፈላል። አንደኛው ቫይረስ ሰውነት ውስጥ ከገባ በኋላ ከፍተኛ ጉዳት እንዳያስከትል የሚከላከል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ሙሉ በሙሉ በበሽታ መያዝን የሚገታ ነው።

ማጅራት ገትርን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። የዚህን በሽታ የተለያዩ ዝርያዎች የሚከላኩ ክትባቶች አሉ። ክትባቶቹ ከ85 እስከ 90 በመቶ የበሽታውን ስርጭት ይገታሉ።

ሆኖም ግን ሰዎች ክትባት ከተሰጣቸው በኋላ ባክቴርያውን ሊያስተላልፉ ይችላሉ። ባክቴርያው አፍንጫና ጉሮሮ ውስጥ ተደብቆ ሰዎች ሲያስነጥሱ፣ ሲያስሉ ወይም ሲሳሳሙ ወደሌላ ሰው ይሸጋገራል።

ክትባቶች ሰውነታችን በሽታን የመከላከል አቅም እንዲያዳብር ይረዳሉ። የኮቪድ-19 ክትባት ቫይረሱን ለይቶ የሚያጠቃና ሰውነትን የሚከላከል አንቲቦዲ (ጸረ እንግዳ አካላት) ያመርታል።

የኮሮናቫይረስ ክትባት ሰውነት ውስጥ እንዴት ይሠራል?

ኒል የተባሉት ተመራማሪ እንደሚሉት፤ የኮሮናቫይረስ ክትባቶች በምን መንገድ በሽታን የመከላከል አቅም እንደሚያዳብሩ ለማወቅ ጊዜው ገና ነው።

አንድ ሰው ክትባቱን ከወሰደ በኋላ ቫይረሱን ሊያስተላልፍ ይችላል? የሚለው ጥያቄ በተደጋጋሚ ይነሳል።

እስካሁን ገበያ ላይ የቀረቡት የኮሮናቫይረስ ክትባቶች የተፈተሹት ሰዎች በሽታውን እንዳያስተላልፉ በማድረግ አቅማቸው አይደለም።

የተመራማሪዎች ዋነኛ ትኩረት ክትባቶች ቫይረሱን መከላከል ይችላሉ ወይ የሚለው ነው።

ፕሮፌሰር ዳኒ አልትማን የተባሉ የኢምፔሪያል ኮሌጅ ለንደን ተመራማሪ፤ ሰውነት የሚያመርተው ጸረ እንግዳ አካላት ሰዎች በድጋሚ በቫይረሱ እንዳይያዙ የመከላከል አቅማቸው ደካማ እንደሆነ ያስረዳሉ።

በአንድ ጥናት ላይ ክትባት ከወሰዱ ሰዎች መካከል 17 በመቶው ለሁለተኛ ጊዜ ቫይረሱ ይዟቸዋል። ከእነዚህ 66 በመቶው የበሽታውን ምልክት አላሳዩም።

ሰዎች የበሽታውን ምልክት ባያሳዩም ወደ ሌሎች ሰዎች ሊያስተላለፉ የሚችሉበት እድል አለ።

በሌላ በኩል አንዳንድ የክትባት አይነቶች ሰዎች በሽታውን ወደ ሌላ ሰው እንዳያስተላልፉ የማድረግ አቅም እንዳላቸው ታይቷል።

ይህን ማድረግ የሚችሉት በሰውነት ውስጥ ያለውን የቫይረስ ቅንጣት መጠን በመቀነስ ነው።

አሁን ገበያ ላይ የሚገኙት ክትባቶች ሰዎች ቫይረሱን ወደሌላ ሰው እንዳያስተላልፉ በማድረግ ረገድ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆኑ እንመልከት። ከኦክፎርድ-አስትራዜኒካ ክትባት እንጀምር።

ኦክፎርድ-አስትራዜኒካ

አምና ሐምሌ ላይ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው፤ ክትባቱ በበሽታው የመያዝ እድልን በእጅጉ ቢቀንስም በሽታውን ወደ ሰው ባለማስተላለፍ ረገድ ሙሉ በሙሉ ውጤታማ ላይሆን ይችላል።

ይህ ውጤት የተገኘው በዝንጀሮዎች ላይ በተደረገ ሙከራ ሲሆን፤ ክትባቱ በሰዎች ላይ ሲሞከር የተለየ ውጤት ታይቷል።

የኦክስስፎርድና አስትራዜኒካ ክትባት ሲሞከር በሁለት ዙር ጠብታ አልነበረም። በጥናቱ የተሳተፉ ሰዎች በየሳምንቱ ከአፍንጫቸው እና ከጉሮሯቸው ናሙና ተወስዷል።

የጥናቱ ውጤት በያዝነው ዓመት ሲታተም እንደጠቆመው፤ ከፊል ክትባቱን ከወሰዱ ሰዎች 59 በመቶ ያህሉ በበሽታው የመያዝ እድላቸው ቀንሷል። ከእነዚህ ሰዎች አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው።

በሌላ በኩል ሙሉ ክትባቱን የወሰዱ ሰዎች በበሽታው የመያዝ እድላቸው 55 በመቶ ቀንሷል።

አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ ክትባቱ በአንድ ጠብታ ለቫይረሱ የመጋለጥ እድልን 67 በመቶ ቀንሷል። ይህም ክትባቱን የወሰዱ ሰዎች ቫይረሱን ወደ ሌላ ሰው እንዳያስተላልፉ የማድረግ አቅም እንዳለ ያሳያል።

ፋይዘር-ባዮንቴክ

ክትባቱ ሰዎች በቫይረሱ እንዳይያዙ በማድረግ ስርጭቱን ስለመግታቱ ገና ባይረጋገጥም፤ ተስፋ ሰጪ ምልክቶች አሉ።

ታኅሣሥ ላይ የፋይዘር ዋና ኃላፊ አልበርት ቦርላ እንዳሉት፤ በእንስሳት ላይ የተደረገ ሙከራ እንደሚያሳየው ክትባቱ በሽታውን ወደ ሌላ ሰው የማስተላለፍ መጠንን ይቀንሳል። ሆኖም በሰዎች ላይ ያለው ውጤታማነት አልተረጋገጠም።

እስራኤል ውስጥ የተሠራ ጥናት የክትባቱ ሁለት ጠብታ ከተሰጣቸው 102 የሕክምና ባለሙያዎች፤ ጠንካራ በሽታ የመከላከል አቅም ያላዳበሩት ሁለቱ ብቻ ናቸው። ይህ ማለት 98 በመቶ ጸረ እንግዳ አካላት አምርተዋል ማለት ነው።

አጥኚዎቹ እንዳሉት፤ ሰዎች ጠንካራ ቫይረሱን የመከላከል አቅም ሲያዳብሩ በሽታውን የማስተላለፍ እድላቸው ይቀንሳል።

በእርግጥ የእስራኤሉ ጥናት የተሠራው በጥቂት ሰዎች ላይ መሆኑ ውጤቱ ላይ ጥያቄ ያስነሳል።

ሞደርና

ሞደርና በሽታውን ወደ ሌላ ሰው እንዳይተላለፍ ስለማድረጉ የሚፈትሽ ሙከራ አልተደረገም።

የመጀመሪያውን ዙር ጠብታ ከወሰዱ ሰዎች 14ቱ በቫይረሱ ተይዘዋል። ሁለተኛውን ዙር ጠብታ ከወሰዱት አንጻር ይህ ቁጥር ዝቅ ይላል።

ሙከራው የሚያሳየው ክትባቱ ከአንድ ጠብታ በኋላ የበሽታውን ምልክት የማሳየት እድልን ሦስት ሁለተኛ እንደሚቀንስ ነው።

ጥናቱ ሲሠራ ሙከራ የተደረገባቸው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ውስን ነበር። እናም የጥናቱ ውጤት ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ ላይሆን ይችላል።

ኖቫክስ

እስካሁን ይህ ክትባት የትም አገር ጥቅም ላይ እንዲውል ፍቃድ አላገኘም። ሰዎች በበሽታው እንዳይያዙ ወይም ቫይረሱን እንዳያስተላልፉ የማድረግ ብቃቱ ገና አልተፈተሸም።

በእርግጥ ጥቅምት አካባቢ ይፋ የተደረጉ ውጤቶች ለሳይንቲስቶች ተስፋ ሰጥተዋል።

ክትባቱ ለዝንጀሮዎች በከፍተኛ መጠን ከተሰጠ ቫይረሱ እንዳይተላለፍ እንደሚረዳ የሚጠቁሙ ውጤቶች ታይተዋል። በተጨማሪም የበሽታውን ምልክት የማያሳዩ ሰዎችን የማስተላለፍ መጠን እንደሚቀንስ ተደርሶበታል።

ክትባቱ በሰዎች ላይ ተሞክሮ ውጤታማነቱ እስከሚረጋገጥ ተመራማሪዎች እየጠበቁ ይገኛሉ።

የጋርዮሽ በሽታን የመከላከል አቅም

ብዙ ሰዎች በሽታውን የመከላከል አቀም ሲያዳብሩ የጋራ በሽታን የመከላከል አቅም (ኸርድ ኢምዩኒቲ) ይፈጠራል።

ክትባቶች የጋራ በሽታ የመከላከል አቅምን ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና አላቸው።

በሳውዝሀምተን ዩኒቨርስቲ የሚሠሩት ማይክል ሄድ "የጋራ በሽታን የመከላከል አቅም ለማዳበር ክትባቶች የበሽታውን ስርጭት መግታት ይጠበቅባቸዋል" ይላሉ።

የጋራ በሽታን የመከላከል አቅም እንዲፈጠር አብዛኛው ማኅበረሰብ ቫይረሱን መከላከል መቻል አለበት።

የጋራ በሽታን የመከላከል አቅም ዳብሯል የሚባልበት ቁጥር እንደየአገሩ ቢለያይም፤ አማካዩን የሚጠቁሙ ጥናቶች ተሠርተዋል።

ለምሳሌ በአንድ አገር ከ60 አስከ 72 በመቶ ያህል ሕዝብ ክትባት ሲወስድ የጋርዮሽ በሽታ የመከላከል አቅም ወደማዳበር ይሄዳል።

ይህ ቁጥር አንድ ክትባት ምን ያህል ቫይረሱን መከላከል ይችላል የሚለው ላይ ይወሰናል።

አሁን ላይ የዓለም ትኩረት የቫይረሱን የስርጭት መጠን መቀነስ ቢሆንም፤ የመጨረሻ ግቡ ወረርሽኙን ማስወገድ ነው።