አሜሪካ የቀድሞ የናዚ ማጎሪያ ካምፕ ጠባቂን በ95 አመታቸው አሳልፋ ሰጠች

ፍሬዲሪክ ካርል በርገር

የፎቶው ባለመብት, US DOJ

አሜሪካ የአንደኛው ናዚ ማጎሪያ ካምፕ ጠባቂ የነበሩትን የ95 አመቱን ግለሰብ ሰሞኑን ለጀርመን ኣሳልፋ ሰጥታለች።

ፍሬዲሪክ ካርል በርገር የተባሉት የቀድሞ ጥበቃ ከአውሮፓውያኑ 1959 ጀምሮ ነዋሪነታቸውን በአሜሪካ አድርገው የነበረ ሲሆን በትናንትናው ዕለትም ነው ወደ ፍራንክፈርት የበረሩት።

በርገር፣ ኑንጋሜ ተብሎ በሚጠራው የማጎሪያ ካምፕ በጥበቃነት ይሰሩ እንደነበር ቢያምኑም ምንም አይነት ግድያም ሆነ የእስረኞችን ስቃይ አልተመለከትኩም ብለዋል።

የጀርመን አቃቤ ህጎችም እንዲሁ በግለሰቡ ላይ ጠንከር ያለ ማስረጃ ባለማግኘታቸው ክሱን እንደተውት ተሰምቷል።

ሆኖም የጀርመን ፖሊስ ግለሰቡን ለምርመራ እፈልገዋለሁ ያለ ሲሆን ከሰሞኑም ፖሊስ ጥያቄ እንደሚያቀርብለት ተነግሯል።

ክሱ እንደገና ይከፈታል የሚለው ጉዳይም አዛውንቱ በሚሉት የሚወሰን ይሆናል።

በባለፈው አመት የስደተኞችን የጥገኝነት ጥያቄ የሚመለከት የአሜሪካ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት ሬቤካ ሆልት የማጎሪያ ካምፑ ውስጥ የነበሩ እስረኞች አስከፊ በሚባል ሁኔታ እንደነበሩና በርካቶችም በድካም እስኪሞቱ ድረስ ለበዝባዥ የጉልበት ስራ ተዳርገዋል በሚል ግለሰቡ በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ጀርመን እንዲላኩ ውሳኔው የተላለፈው።

በነበረው ችሎት ሲሰማ አዛውንቱ በርገር ከካምፕ ለማምለጥ ይሞክሩ የነበሩ እስረኞችን ሲመልሱ እንደነበር አምነዋል። የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሞንቲ ዊልኪንሰን ከሰሞኑ እንዳሉት በርገር ለጀርመን ተላልፈው መሰጠታቸው አገራቸው ለፍትህ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።

"አሜሪካ በናዚ ማጎሪያ ካምፖች በሰብዓዊነት ላይ የሚፈፀም ወንጀል ለተሳተፉ፣ ሌሎች ጭፍጨፋዎችንም ሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ላደረሱ ግለሰቦች መደበቂያ አይደለችም" በማለት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ተናግረዋል።

በርገር ከዋሽንግተን ፖስት ጋር ባደረጉት ቆይታ በካምፑ የጥበቃ ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩት ለአጭር ጊዜ እንደሆነና መሳሪያም ይይዙ እንዳልነበር አስረድተዋል።

ለዘመናት አሜሪካ የኖሩት አዛውንቱ በርገር የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ "ከ75 ዓመታት በኋላ፣ ይህ የሚገርም ነው ለማመንም ይከብደኛል። ከቤቴ እኮ ነው በግድ እያስወጣችሁኝ ያላችሁት" ብለዋል።

የጀርመን አቃቤ ህግ በናዚ ማጎሪያ ካምፕ ተሳትፎ አላቸው የተባሉ ግለሰቦችን ከማደን አላቆመም።

ከሰሞኑ በናዚ የማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ፀሃፊ ነበሩ ነበሩ የተባሉ የ95 አመት አዛውንት በሰሜን ጀርመን ውስጥ በጅምላ ግድያ ወንጀል ተወንጅለዋል።

ኢምግራንድ ኤፍ የተባሉት አዛውንት ሃምበርግ በሚገኝ የአረጋውንያን እንክብካቤ ማዕከል የሚኖሩ ሲሆን ከአስር ሺህ በላይ ክሶች ቀርበውባቸዋል።

ስተትሆፍ በተባለው አሰቃቂ የማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ፀሃፊ የነበሩ ሲሆን በካምፑ ውስጥ በነበረው የጅምላ ግድያና ጭፍጨፋ አስተባብረዋል በሚልም ነው እየተወነጀሉ ያሉት።

በሁለተኛው አለም ጦርነት ወቅት በዚሁ ማጎሪያ ካምፑም 65 ሺህ ሰዎች እንደሞቱ ተገልጿል።