የሳዑዲው ልዑል ጋዜጠኛ ኻሾግጂ እንዲገደል ፈቃድ ሰጥተዋል- አሜሪካ

የሳዑዲው አልጋ ወራሽ ልዑል መሃመድ ቢን ሳልማን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሳዑዲው አልጋ ወራሽ ልዑል መሃመድ ቢን ሳልማን በአሰቃቂ ሁኔታ በግዞት የተገደለውን ጋዜጠኛ ኻሾግጂ ግድያ እንደፈቀዱ አንድ የአሜሪካ ደህንነት ሪፖርት አጋልጧል።

ጋዜጠኛው የተገደለው በአውሮፓውያኑ 2018 መሆኑ ይታወሳል።

በአዲሱ ባይደን አስተዳደር ይፋ የሆነው ይህ ሪፖርት እንደሚያሳየው ልዑሉ ጋዜጠኛው ኻሾግጂ እንዲያዝ ወይም እንዲገደል መፍቀዳቸውን ነው።

"የሳዑዲው አልጋ ወራሽ ልዑል መሃመድ ቢን ሳልማን ጋዜጠኛው ኻሾግጂ በኢስታንቡል እንዲያዝ ወይም እንዲገደል ዘመቻ ማካሄዳቸውን ደርሰንበታል" ይላል የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ቢሮ ዳይሬክተር ያወጣው መረጃ።

የደህንነት ቢሮው የጋዜጠኛ ኻሾግጂ የግድያ ዘመቻን ልዑሉ በበላይነት መርተዋል የሚላቸውንም ሶስት ምክንያቶች አስቀምጧል።

እነዚም በዋነኝነት ልዑሉ በግዛታቸው ላይ ከ2017 ጀምሮ የሚወሰኑ ውሳኔዎችን በሙሉ በበላይነት መቆጣጠራቸው፣ በተለያዩ ዘመቻዎች ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆናቸው እንዲሁም በውጭ አገራት ተቃዋሚ ናቸው የሚሏቸውን ድምፆች ዝም ለማሰኘት ጥቃቶችን ማካሄዳቸውን ጠቅሷል።

ሪፖርቱ በጋዜጠኛው ግድያ በቀጥታ እጃቸው አለባቸው እንዲሁም በተዘዋዋሪ ተሳትፈዋል ያላቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር አስቀምጧል።

የጋዜጠኛውን ግድያ ተከትሎ አሜሪካ በተለያዩ የሳዑዲ ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ ብትጥልም ልዑሉን ግን መንካት አልፈለገችም።

ሳዑዲ አረቢያ በበኩሏ ሪፖርቱን ያጣጠለችው ሲሆን "ጨለምተኛ፣ ሃሰተኛና ተቀባይነት የሌለው" ስትል ፈርጃዋለች።

የሳዑዲ መሪ ልዑል መሃመድ ቢን ሳልማን እንዲሁ በግድያው ላይ እጄ የለም፤ ከደሙ ንፁህ ነኝ በማለት በተደጋጋሚ ተናግረዋል።

የሳዑዲን መንግሥት በሰላ ትችቱ የሚታወቀው ጋዜጠኛ ኻሾግጂ በቱርክ፣ ኢስታንቡል የሚገኘውን የሳዑዲ ቆንስላ በጎበኘበት ወቅት ነው የተገደለው። በወቅቱም የወጡ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ጋዜጠኛው ተቆራርጦ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሉን ነው።

የ59 አመቱ ጋዜጠኛ በአንድ ወቅት የሳዑዲ መንግሥት አማካሪ እንዲሁም ከንጉሳዊው ስርዓት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ነበረው።

በኋላም የአገሪቱን ሁኔታ በመተቸትም በአውሮፓውያኑ 2017 ለግዞት ተዳርጓል። ከሳዑዲ መንግሥት ጋር ከተጣላም በኋላ በዋሺንግተን ፖስት የሳዑዲውን ልዑል ፖሊሲዎች በመተቸት ወርሃዊ ፅሁፎችንም ያበረክት ነበር።