ህጻናት መብት፡ በናይጄሪያ ከ300 በላይ ተማሪዎች መታገታቸው ተሰማ

ሰዎች ከትምህርት ቤቱ ውጭ ወደ ቤታቸው ሲሄዱ

የፎቶው ባለመብት, Sanusi Jangebe

በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ ከሚገኝ ትምህርት ቤት ከ300 በላይ ሴት ተማሪዎች ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች ተጠልፈው መወሰዳቸው ተገለፀ።

ፖሊስ ተማሪዎቹ አርብ ዕለት ጠዋት ዛምፋራ ግዛት ጃንገቤ ከሚገኘው አዳሪ ትምህርት ቤታቸው ከተጠለፉ በኋላ ወደ ጫካ እንደተወሰዱ እምነት አለው።

ይህ በቅርብ ሳምንታት ከተፈፀሙ የተማሪዎች የጅምላ ጠለፋ መካከል በቅርቡ የሆነ ነው።

በናይጀሪያ ታጣቂ ቡድኖች በገንዘብ ተደራድረው ለመልቀቅ ሲሉ ተማሪዎችን ያግታሉ።

አንድ የትምህርት ቤቱ መምህር እንደተናገሩት ታጣቂዎቹ ወደ ቅጥር ግቢው ሲገቡ የመንግሥት የፀጥታ ኃይል የደንብ ልብስ ለብሰው እንደነበርና ሴት ተማሪዎቹን ተሽከርካሪ ላይ እንዲወጡ እንዳስገደዷቸው ተናግረዋል።

ሌላ የዓይን እማኝ ደግሞ ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ ታጣቂዎቹ ትምህርት ቤት ውስጥ የገቡት በእግራቸው ነው ብለዋል። የታጣቂዎቹ ቁጥርም 100 እንደሚሆን የዓይን እማኙ ምስክርነታቸው ሰጥተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ፤ ድርጊቱን 'ጭካኔ የተሞላበት' እና 'የህጻናትን መብት የጣሰ' ሲል በተማሪዎቹ ጠለፋ ማዘኑን ገልጿል።

ፕሬዚደንት ሙሃመዱ ቡሃሪ አሁን የተፈፀመውን የተማሪዎች እገታ " ኢ ሰብዓዊ እና ተቀባይነት የሌለው" ሲል አውግዘውታል።

ፕሬዚደንቱ በሰጡት መግለጫ ፤ አስተዳደራቸው በርካታ ገንዘብ ለማግኘት ብለው ንጹሃን ተማሪዎችን በሚያግቱ አደገኛ ቡድኖች ተግባር አይሸነፍም ብለዋል።

ዋነኛ ዓለማቸውም የታገቱ ተማሪዎች በሕይወትና ጉዳት ሳይደርስባቸው ማግኘት እንደሆነም ተናግረዋል።

ቡሃሪ አክለውም ምንም እንኳን ባለሥልጣናት ከፍተኛ ኃይል ማሰማራት ቢችሉም፤ ታጣቂዎቹ ተማሪዎቹን እንደ ጋሻ ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ የሚል ስጋት መኖሩን ገልጸዋል።

ባለፈው ሳምንት በኒጀር ግዛት አጎራባች በምትገኘው ካጋራ ተጠልፈው የተወሰዱ 27 ተማሪዎችን ጨምሮ 42 ሰዎች እስካሁን ድረስ አልተለቀቁም።

እአአ በ2014 በአገሪቷ ሰሜን ምስራቅ ከተማ ችቦክ 276 ተማሪዎች በእስላማዊ ታጣቂ ቡድኑ ቦኮ ሃራም ታግተው ነበር።

ይህ በናይጀሪያ በትምህርት ቤቶች ላይ የደረሰው ጥቃት ዓለም አቀፋዊ ትኩረት አግኝቶ ነበር።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚፈፀሙ ጥቃቶች የሚፈፀሙት በአደገኛ ወንበዴዎች እንደሆነ ጥርጣሬ አለ።

እስካሁን በጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደ ቡድን የለም።

በዛምፋራ ግዛት ታጣቂ ቡድኖች ብዙ ጊዜ ተማሪዎችን የሚያግቱት ጠቀም ባለ ገንዘብ ለመደራደር ሲሉ ነው።

ነገር ግን ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር፤ ታጣቂዎች ከአጎራባች ሲና ግዛት ካንካራ ከ300 በላይ ወንድ ተማሪዎችን ሲወስዱ ከሰሜን ምስራቅ የአገሪቷ ክፍል በመቶዎች ማይሎች በሚርቅ ቦታ ላይ የሚንቀሳቀሰው ቦኮሃራም ከጥቃቱ ጀርባ እንዳለ የሚያሳዩ መረጃዎች ወጥተዋል።

በኋላ ላይ በተደረገ ድርድርም ተማሪዎቹ መለቀቃቸው ይታወሳል።